5 ጥቅምት 2020

በሳሙና የምትታጠብ ሴት እጅ

ውሃን ሳሙና እንደ ዘንድሮ ከብረው አያውቁም ብንል ማጋነን አይሆንም። በውሃና ሳሙና መሪነት ስንቱ ኮሮናቫይረሰን ከመዳፉ ጠራረገ።

እርግጥ ነው ሳሙናና ውሃ ለመዳፋችን ብርቅ አይደሉም። እንዲህ በሕይወታችን አስፈላጊ ይሆናሉ ብሎ የተነበየ ካለ ግን እሱ ሐሰተኛ ነው። ውሃና ሳሙና አሁን ከነርቫችን ጋር ተናኝተዋል። ሳናስበው ሁላ መታጠብ ጀምረናል።

ኮሮናቫይረስን ለመዋጋት ብዙ መሣሪያ ታጥቀናል። ጭምብል ቢሉ ጓንት፤ ራስን ማግለል ቢሉ በጸረ ተህዋስ ቫይረስን መግደል። ከሁሉም በላይ ቀላሉ መሣሪያ ግን እጅን በሳሙና እሽት አድርጎ መታጠብ ነው።

ኮሮናቫይረስ ገዳይ ወረርሽኝ ነው ተብሎ ወርሃ የካቲት ላይ ሲታወጅ የጤና ሰዎች አዲሱን ቫይረስ እንዴት እንደምትከላከከሉ እንንገራችሁ ብለው ብቅ አሉ።

እንዲህም አሉ፤ የመጀመሪያውና የመጀመሪያው እጅን መታጠብ ነው። ለዚያውም በሳሙና። ከተገኘ ሞቅ ባለ ውሃ። ቢያንስ ለ20 ሰከንድ መታጠብ።

በኢትዮጵያዊው ዶ/ር ቴድሮስ የሚመራው የዓለም ጤና ድርጅት እጃችን እንዴት መታጠብ እንደምንችል የሚያሳይ ምስል ሠራ።

ይኸው ይህ በቫይረስ የሚተላለፈውን ወረርሽኝ ስድስት ወር አለፈው።

በርካታ ከተሞች ተዘግተው ተከፈቱ። እንደገና የተዘጉም አሉ። ሰዓት እላፊም ያወጁም መቶዎች ናቸው። ቫይረሱ ግን እንዲህ በቀላሉ አልተበገረም። ለዚህም ነው አሁንም እጃችሁን ታጠቡ እየተባለ የሚመከረው።

ነገር ግን እጃችንን በአግባቡ እየታጠብን አይደለም የሚሉ ቅሬታቸው አሁንም ይደመጣሉ። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ የተሠራ አንድ ጥናት የሕክምና ማዕከሎችን ከሚጎበኙ 1 ሺህ ሰዎች 1 በመቶ ብቻ ናቸው በአግባቡ እጃቸውን የታጠቡት ይላል።

የሳሙና አረፋ ስዕል
የምስሉ መግለጫ,ሳሙና ቫይረሱን ቅባታማ ሽፋን ስለሚሰባብረው በቀላሉ እንዲወገድ ያደርገዋል

እውን ውሃና ሳሙና ቫይረሱን ሙልጭ አድርገው ያጠፋሉ?

በደንብ ነዋ! ይላሉ የቦስተን ማሳቹሴትስ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ቶማስ ጊልበርት።

ባለሙያው እንደሚሉት ኮሮናቫይረስ የተሠራበት የኬሚካል ውህድ በትንሽ ሳሙናና ሙቅ ውሃ ብትንትኑ ይወጣል።

“ቫይረሶች ቅባታማ ባህሪ ያለው ሽፋን ያላቸው ናቸው። ይህ ቅባትነት ያለው ሽፋን ውስጥ ያለውን ዋና ቫይረስ የሚከላከል ነው። ይህ ሽፋን በሳሙናና ውሃ መሰበር ይችላል። ሽፋኑ ተሰበረ ማለት ውስጥ ያለው ቫይረስ ተጋለጠ ማለት ነው። ይህ ደግሞ ቫይረሱን ያጠፋዋል” ይላሉ ባለሙያው።

“ከዚህ በኋላ በውሃና ሳሙና መታጠብ አያስልፍግም የሚባልበት ጊዜ ቅርብ ነው ብዬ አላስብም።”

“መጀመሪያን እጅዎን ያርጥቡ፤ ከዚያ ሳሙናው አረፋ ከሰራ በኋላ ቢያንስ ለ20 ሰከንዶች ያህል እጅን ማሸት ነው“ ሲሉ ባለሙያው ይመክራሉ። ጊልበርት እንደሚሉት ሳሙናው የቫይረሱን ሽፋን ሰብሮ ለመግባት 20 ሰከንድ ይበቃዋል። ሙቅ ውሃ ከታከለበት ደግሞ ሳሙናውን ሥራውን በፍጥነት እንዲያከናውን ያግዘዋል።

በኬንት ዩኒቨርሲቲ የሞለኪዩላር ሳይንስ ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር ማርቲን ሚካየሊስ ደግሞ ውሃ ብቻውን የቫይሱን ሽፋን ለመስበር በቂ አይደለም ይላሉ።

“ኩሽና ውስጥ ስናበስል ዘይት እጃችንን ከነካው በውሃ ብቻ ለማስለቀቅ እንደሚከብደን ሁሉ የኮሮናቫይረስን ለማግኘት ሳሙና የግድ ነው።“

ነገር ግን የውሃና ሳሙና ድል በእንግሊዝኛው ሳኒታይዘር እየተባለ ከሚጠራው ፀረ-ተህዋስ ፈሳሽ ጋር ሲምታታ ይስተዋላል።

ዘንድሮ ሳኒታይዘርና ጭምብል ረስቶ ከመውጣት ሞባይል ስልካችንን ረስቶ መውጣት የተሻለ ነው።

ነገር ግን ባለሙያዎቹ ሳኒታይዘር ለችግር ጊዜ ነው መሆን ያለበት ይላሉ። ቤት ውስጥ ውሃና ሳሙና ካለ ሳኒታይዘር መጠቀም አይመከርም።

ጊልበርት በትንሽዬ ብልቃጥ ሳኒታይዘር ይዞ መንቀሳቀስ አይከፋም ይላሉ። ነገር ግን እኔን ብትጠይቁኝ ይላሉ ባለሙያው “እኔን ብትጠይቁኝ የምመርጠው ውሃና ሳሙና ነው።”

የእጃችን የፊትና የጀርባ ክፍል

እጃችንንምንያክልእንታጠብ?

ወረርሽኙ የጀመረ ሰሞን በርካታ አገራት ዜጎቻቸው በየጥቂት ሰዓቱ እጃቸውን እንዲታጠቡ ይመክሩ ነበር። ቤት ብትውሉ እንኳ እጃችሁን መታጠብ እንዳትረሱ የሚል መልዕክት መስማት የተለመደ ነበር።

ፕሮፌሰር ጊልበርት ግን ቤት የምንውል ከሆነ አስር ጊዜ እጅን መታጠብ አስፈላጊ አይደለም ባይ ናቸው። ቢሆንም ሽንት ቤት ከተጠቅምን በኋላም ሆነ ማዕድን ከማዘጋጀትችንና ከመቁረሳችን በፊትና በኋላ እጅን መታጠብ ግድ ይላል።

ባለሙያው በጭራሽ እንድነዘጋ አይፈልጉም።

እጃቸውን በተደጋጋሚ መታጠብ ያለባቸው ሰዎች አሉ። ለምሳሉ ቤታቸው ውስጥ የኮቪድ-19 ታማሚ የሚንከባከቡ ሰዎች ውሃና ሳሙና ወዳጃቸው ሊሆን ይገባል።

አሊያም ቫይረስ ሊኖርባቸው ይችላሉ የተባሉ ዕቃዎችን የነኩ ሰዎችን በጣም ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። መኖሪያ ቤታችሁ ብዙ ሰዎች ካሉም እጅን በተደጋጋሚ መታጠብ ይመከራል።

አንድ ጥናት ሰዎች ቫይረሱ ያለበት ሰው ወይም ዕቃ ከነኩ ወዲያውኑ እጃቸውን መታጠባቸው በጣም አዋጭ መሆኑን ይጠቁማል።

አንዳንድ ሰዎች ከዚህ በፊት ከምንጠቀመው ሳሙና ይልቅ ፀረ-ተህዋስ ሳሙናዎች የበለጠ ኮቪድ-19ኝን ይከላከላል በማለት ሲጠቀሙ ይስተዋላሉ።

ይሁንና እንደ ሚካየሊስ ከሆነ የትኛውም ሳሙና የኮሮናቫይረስ አምጪ ተህዋስን የመግደል አቅም አለው።

ሁለቱም ባለሙያዎች ኮሮናቫይረስን ከመዳፋችን ጠራርጎ ለማጥፋት የግድ ለመጠጥ የሚሆን ንፁህ መጠቀም እንደሌለብን ይመክራሉ። የውሃ አቅርቦት በቂ ባልሆነባቸው የዓለማችን ክፍሎች በውሃና በሳሙና በቀላሉ እጅን መታጠብ ቀላል ላይሆን ይችላል።

የዶክተር ቴድሮስ መሥሪያ ቤት በቅርቡ ያወጣው አንድ ጥናት እንደሚያሳየው በዓለማችን ከአምስት ትምህርት ቤቶች ሁለቱ ብቻ ናቸው በቂ የውሃ አቅርቦት ያላቸው። ይህ ጥናት የተሰራው ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በፊት ነው።

ሌላው አስገራሚ የኮሮናቫይረስ ተፅዕኖ ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን መቀነሱ ነው። ለምሳሌ የኢንፍሉዌንዛ በሽታ ከሌላው ጊዜ በተለይ ዘንድሮ እጅግ ቀንሷል።

ባለፈው ዓመት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ መጋቢትና ነሐሴ ወር ላይ ቢያንስ 700 ሰዎች በጉንፋን ነክ በሽታዎች በጠና ይታመሙ ነበር። ዘንድሮ ግን አንድ ሰው ብቻ ነው መሰል በሽታ የታየበት። ለዚህም ደግሞ ዋነኛው ምክንያት ሰዎች አካላዊ ንክኪ መቀነሳቸው ነው።

ወጣም ወረደ ኮሮናቫይረስ ክትባት እስኪገኝለት ድረስ እጅ መታጠባችን፤ ንክኪ መቀነሳችንን መቀጠሉ አዋጭ ነው።

መቼም ሚሊዮኖች የተጠቁበት፤ አእላፍ ያለቁበትን በሽታ በዓይናችን እያየን መዳፈሩ አዋጭ አይደለም።