አንዱ ዓለም ተፈራ

ሰኞ መስከረም ፳ ፭ ቀን ፳ ፫ ዓ.

(10/5/2020)

 አገራችን በቅጡ ሊቀመጥ በሚያስቸግር የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ነች። ፈጦ አግጦ የመጣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ፣ በትግራይ የሰፈረው ሕገ ወጥ የትግራይ ገዢ ቡድን፣ አዲስ አበባ ውስጥ የዶለተና እያተራመሰ ያለ አፈንጋጭ ፅንፈኛ አገር አጥፊ ቡድን፣ ሊደረግ የታቀደ ሕዝባዊ ምርጫ፤ ከብዙዎቹ በጥቂቱ፤ እኒህ ማዕከላዊ የፖለቲካ ማሕደሩን ቦታ አሳፍተው ይዘውታል። በሥልጣን ላይ ያለው የብልፅግና ፓርቲ፤ አሁንም ለውጡ በመጣበትና ቦታውን እንዲለቅ በተደረገው ሕገ መንግሥትና አስተዳደራዊ መዋቅር፤ አገሪቱን እየገዛ ይገኛል። አሁንም አትለያዩን ብሎ ሕዝቡ በተነሳበት የቋንቋና የትውልድ ክልልን መሠረቱ ባደረገው የኢሕአዴግ የፖለቲካ ፍልስፍና እየገዛ ነው። የክልሎቹ ቁጥር እየበዛ፣ በክልሎች መካከል ያለው ልዩነቱ እየበረታ፣ ብቸኝነቱ እየጠነከረ ነው። ባጠቃላይም፤ ከፍተኛ መስዋዕት የተከፈለበት የለውጥ ሂደት፤ ትርጉም አልባ እየሆነ መጥቷል። ለዚህ ደግሞ ተጠያቂው ብልፅግና ፓርቲ ብቻ ሳይሆን፤ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶችና በአነስተኛ ደረጃ ቢሆንም፤ እያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያን በያለንበት ነን። ከነመዘዙ ላስረዳ፤

የኢትዮጵያ ሕዝብ በያለበት ተነስቶ ለውጡ አይቀሬ በሆነበት ሰዓት፤ በኢሕአዴግ ውስጥ ያሉ ለውጥ ፈላጊዎች የመሪነቱን ቦታ ጨብጠው፤ ለውጡ የማይቀለበስበት ደረጃ ላይ ደረሰ። በዚህ ወቅት፤ ይህ ለውጡን የሚመራው ክፍል፤ በምን መንገድ የሕዝቡን ጥያቄ እንደሚያስተናግድ የጠራ ዕቅድ አልነበረውም። ሕዝቡ እንዲለወጥ የፈለገውና ለውጡን እመራዋለሁ ብሎ የተነሳው ክፍል ማድረግ የያዘው፤ የተለያዩ ሆኑ። ለውጡን እየመራ ያለው ክፍል፤ የቀድሞ ገዥዎችን አባሮ፤ በቦታቸው ሆኖ፤ ኢትዮጵያ የሚል ምልክት በራሱ ላይ ለጥፎ፣ መንግሥታዊ መዋቅሩን፣ ወታደራዊ ኃይሉን፣ የሀገሪቱን ንብረት፣ በሙሉ በቁጥጥሩ ሥር ይዞ፤ እነሱ ያደረጉትን ነው እያደረገ ያለው። ሕዝቡ ደግሞ፤ መሠረታዊ የሆነ የፖለቲካ ፍልስፍና፣ የሕገመንግሥትና የአስተዳደር መመሪያ ለውጥ ነው የፈለገው። ለምን መጣጣም አልተገኘም? እንመርምረው፤

በመጀመሪያ፤ ለውጡን ይፈልጋሉ ብለን ባንድ ፊት የመደብነው ክፍል፤ በውስጡ የተለያየ ግብ ያላቸው አካላት አሉበት። አብዛኛው ለውጥ ፈላጊ ክፍል፤ በአገር ውስጥ ያለውም ሆነ በውጪ ሆኖ የታገለው፤ ለውጡን የፈለገው፤ ባለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር አገራችንን የገዛበትን መስመር ለመለወጥ ነበር። ሕዝቡን ከፋፍለው የገዙበትን ሂደት ለመቀየር ነበር። ሕዝቡ የተነፈገውን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማስፈን ነበር። በሕግ ፊት ሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል የሚቀርብበትን ስርዓት ለማንገሥ ነበር። አነስ ያለው ክፍል ደግሞ፤ የለም ለውጡ የነበረውን አሰራር ይዘን፤ የነበረው ገዢ ክፍል ሕገመንግሥቱን በትክክል በሥራ ላያ አላዋለምና፤ እሱ ወርዶ እኔ በሥራ ላይ አውለዋለሁ! እናም እኔ ልግዛ ባይ ነበር። ይህ ክፍል የነበረውን ስርዓት ሳይሆን፤ የነበሩትን የስርዓቱ ቁንጮዎችና የነሱን ወገን መለወጥ፤ ነበር ግቡ። በመሐል ቤት፤ በኢሕአዴግ ውስጥ አድገው፣ በዚሁ ስርዓት ተጠምቀው፣ ሕገመንግሥቱን አክብረውና ለተተግባሪነቱ ቆመውለት የኖሩ የተወሰኑ ግለሰቦች፤ ለውጡ ባስነሳው ነፋስ ሾፌርነቱን ጨብጠው፤ ለለውጡ ተነሱ። አቋማቸው ያኔም ሆነ አሁንም ግልጥ አይደለም። ከሕዝቡ ጋር መሠረታዊ ለውጡን ደግፈው ነው የተነሱት? ወይንስ ሕገመንግሥቱ ትክክል ነው! ነገር ግን፤ በነባሮቹ ገዥዎች በትክክል አልተከበረምና እኛ እናስከብረዋለን ብለው! ነው? ይሄ ግልጥ አይደለም።

የነበረው ስርዓት አገራችንን ወደ መፈራረስ በሚወስድ ጎዳና እየነዳት ነበር። ኢትዮጵያ፤ ብዙ የተለያዩ ቋንቋዎች የሚነገርባት፣ ብዙ የተለያዩ ባህላት የሚከበርባት፣ የተለያዩ የእምነት መስመሮችን የሚከተሉ ዜጎች ያሉባት፤ አንድ አገር ናት። በአገርና በነኚህ የተፈጥሮ ክፍፍሎች መካከል ትልቅ ልዩነት አለ። በሰው ውስጥ የሚዘዋወረው ደም የተገኘበት የትውልድ ሀረግ ወገንተኝነትና፤ በአንድነት በአንድ አገር ያለ ዜግነት፤ የተለያዩ ናቸው። በዚህ መካከል ሌላ ቦታ የለም። የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር፤ አገራችንን በዚህ የግል የትውልድ ምንጭ መሠረት ከፋፍሎ፤ የአገራችንን አስተዳደር በብሔር ክልሎች አዋቀረ። ለምን ይሄን እንዳደረገ መተረኩ፤ ለቀባሪው ማርዳት ይሆንብኛል። ይህ የክልል አወቃቀር ከፍተኛ የሆነ አደጋ ነበረው። 

በቀላሉ ለማስቀመጥ፤ መከፋፈል እንጂ፤ እኩልነትና መብት የሚባሉት ጉዳዮች ቦታ ሊኖራቸው አይችልም ነበር። አንድነትና ኢትዮጵያዊነት ቦታ አጡ። ፈጣሪና ተፈጣሪ፣ ታጋይና ታጋይ ያልሆነ፣ ትግሬና ሌሎች፣ እኩይ የልዩነት መስመሮች ነበሩ። ለሁሉም ነገር ተጠያቂ የሆነ ጨቋኝ አማራና፤ ሌሎች በሙሉ ተሰባስበው ተጨቋኝ ብሔሮች! የሚለው ትርክት፤ ማዕከላዊ መግዣ በትራቸው ሆነ። በክልሎች መካከል ልዩነትን አጎሉት። በክልሎች መካከል ፉክክርን አስፋፉት። እናም ተፎካካሪ ክልሎች እንጂ፤ የአንድ አካል የተለያዩ ክፍሎች ሆነው አልተገኙም። ቢመረመር፤ በነበረው አሠራር፤ ከዚያ የተለየ ሊሆኑ አይችሉም ነበር። በየክልሉ ውስጥ፤ የፓርቲ አባል በሆነና ባልሆነ መካከል የተጠቃሚነት ልዩነቱን ወደ ላይ ጦዘ። እናም አዳዲስ ሀብታሞችንና ብዙዎች ከጥቅም ውጪ እንዲሆኑ የተደረጉበትን ሁኔታ ተፈጠረ። ይህ በበኩሉ በሀብታሙና በደሃው መካከል ያለውን ልዩነት እየከፋ እንዲሄድ አደረገው። የድሃው ብዛት አገራችንን አጥለቀለቃት። በየክልሉ ያሉ ትምህርት ቤቶች ከመድከማቸው ባሻገር፤ የግል ትምህርት ቤቶች እንዳሸን እንዲፈሉ በማድረግ፤ በመካከላቸው ያለው ልዩነት እንዲያሻቅብ ሆነ። በዚህ ብቻ ሳይሆን፤ በሕክምና ባጠቃላይም በኑሮ ደረጃ ልዩነቱ አደገ። ከመሪዎቹ የተነሳው፤ “እኛ!” እና “እነሱ!”፤ በክልሎችን ደረጃ ተዛምቶ፤ ኢትዮጵያዊ መሆን ትርጉም እንዲያጣ ተደርጎ ተጣለ። ይህ ሄዶ ሄዶ፤ በሁሉም ነገር በጠላትነት የሚተያዩ፣ ፍጹም የተለያየ ማንነት ያላቸው ክልሎችን ብሎም አገሮችን የሚፈጥር ሂደት ነበር። ይህ፤ ቀድሞውንም ትግራይን ነፃ ለማውጣት ግብ ለነበራቸው መሪዎቹ፤ አስሊ ዘዴ ነበር። አሁንም መቀሌ መሽገው እየገፉ ያሉት ይሄንኑ ነው።

ለውጡን ስንመለከት፤ ዋናው ድክመቱ፤ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በፈለገው የለውጡ ማጠንጠኛ አጀንዳ መሪ ድርጅት አለመኖሩ ነው። የዚህ ለውጥ መሪ ድርጅት፤ ለውጡን ለመተግበር፤ እምነቱም ጉልበቱም ያለው ክፍል ሆኖ አለመገኘቱ ነው። ለሃያ ስድስት ዓመታት ሲሰበክ የኖረው ልዩነት፤ በቀላሉ የሚፈርስ ግንብ አልሆነም። ይልቁንም ሥልጣን የናፈቃቸው አስሊዎች፤ በየጎራቸው ተሰግስገው፤ የየራሳቸውን ወገን ማደንደን ያዙ። በሥልጣን ላይ ያለው ክፍል ብቻ ሳይሆን፤ ሥልጣን እናገኛለን ባዩ ሁሉ፤ በየራሱ ላይ ዘውድ ደፋ። እኒህ ሁሉ ለውጡን ሳይሆን፤ ራሳቸውን ሥልጣን ላይ ማውጣቱ ሆነ አጀንዳቸው። አገራዊ አጀንዳ፣ አገራዊ ራዕይ፣ አገራዊ ድርጅትና አገራዊ መሪ ጠፋ። ለዚህ ነው በዚህ ሂደት ተጠያቂው ብልፅግና ብቻ ሳይሆን፤ እኛም ነን ያልኩት። ከነበርንበት የተከፋፈለ አገርና አምባገነን ስርዓት፤ ወደ አገራዊ አንድነትና ሕዝባዊ ስርዓት ለመሸጋገር፤ አገራዊ አንድነት፣ አገራዊ ራዕይ፣ አገራዊ ድርጅትና አገራዊ መሪ ያስፈልግ ነበር። ይሄ ባንድ ቀን የሚፈጠር ጉዳይ ሳይሆን፤ ጊዜን የሚወስድ፤ የአለሁ ባዮችን ሁሉ ትብብር የሚጠይቅና፤ ቆራጥ ውሳኔዎችን ለመሥጠትና ለመተግበር የተዘጋጀ መሪና ተመሪ ይጠይቃል። ሥልጣን የያዘው ክፍል፤ ሥልጣኑን ከጁ መልቀቅ አልፈለገም። የቋመጠውም፤ “በኔ ሃሳብ መሠረት!” ብሎ ባልያዘው ሥልጣን ደነፋ። በመሐል ቤት ሕዝቡ ተስፋው መነመነ። እናም ራሴን ላድን በቦታው ነገሠ። ችግርን መዘርዘሩ የትም አይወስድም። ባለንበት መርገጥ ነው። እስኪ ወደ መደረግ ያለበት የምለው እንሂድ።

የለውጥ ፈላጊዎች የመጀመሪያ መነሻ፤ እንዲለወጥ የተፈለገው ጉዳይ ነው። ምንድን ነው እንዲለውጥ የተፈለገው? ከዚያ ተከትሎ የሚመጣው፤ ተለውጦ ምን በቦታው ይተካ? የሚለው ነው። በዚህ ላይ፤ በሶስተኛ ደረጃ፤ እንዴት ለውጡ እንደሚካሄድ ማሰብ ያስፈልጋል። ከሕዝቡ አኳያ፤ የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ የተጨበጡ ናቸው። ልዘርዝራቸውና፤ መነሻው፤ የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ቡድን አገዛዝ፤ ከነፍልስፍናውና አሰራሩ፣ ከነሕገመንግሥቱና አወቃቀሩ መፍለሱ ነበር። ግቡ፤ እያንዳንዱ ኢትዮጵያ፣ በትውልድ ቦታው ወይንም በቋንቋው፣ በፆታው ወይንም በሀብቱ፣ በትምህርት ደረጃው ወይንም በሙያ መስኩ፣ በእምነቱ ወይንም በሚኖርበት አካባቢ የተነሳ አድልዖ ሳይደረግበት፤ በኢትዮጵያዊነቱ፤ በየትኛውም የኢትዮጵያ ምድር፤ ሠርቶ የመኖርና ሀብት የማፍራት መብቱ መከበሩ ነው። ለዚህም መሠረታዊ የሆኑት፤ የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶቹ የተከበሩባትና የሕግ የበላይነት የሰፈነባት ኢትዮጵያ መኖሯ ነው። እዚህ ላይ ሕግ ስል፤ አንደኛ ሕዝቡ ያጸደቀው ትክክለኛ ሕገመንግሥትና መተዳደሪያ ደንብ መኖሩ ሲሆን፤ ሁለተኛ ደግሞ ይህ ሕግ ለያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እኩል የሚሠራ ሆኖ መገኘቱ ነው። ሶስተኛውና ግልጥ ያልሆነው፤ ይሄ ካለንበት ወደምንፈልግበት የሚደረገውን ሽግግር አስመልክቶ ነው።

እዚህ ላይ፤ በሥልጣን ላይ ካለው ከብልፅግና ጀምሮ፣ ብዙ አባላት ያሏቸው ፓርቲዎችና ጥቂት አባላት ያሏቸው፣ በግል ታታሪ አገር ወዳዶችና ተቆርቋሪዎች አንድነት ባልፈጠርንበት እሳቤ፤ ለየብቻችን እየዳከርን ነው። ባንድ በኩል፤ “ምርጫ!” “ምርጫ!” እንላለን። ብልፅግና ብቻውን ሳይሆን፤ ከዚህ ድርጅት ውጪ ያሉት ድርጅቶችም፤ በየጎራቸው ባሉት ቆጥረው በያዟቸው አባላት በመመርኮዝ፤ “ምርጫ!” ብለዋል። ምርጫ ስለተካሄደ፤ ትክክለኛ መንግሥት አይከትልም። ዴሞክራሲም አይነግሥም። በመሠረቱ፤ ባሁኑ ሰዓት ምርጫው ምንድን ነው? አሁንኮ፤ ከተለያዬ ግንዛቤ፤ እያንዳንዳችን፤ ኢትዮጵያዊ ነኝ! እንድንል የመሸጋገሪያ ወቅት ላይ ነን። ታዲያ ይሄ በሌለበት ወቅት፤ እንዴት ያለ ምርጫ ነው የሚካሄደው? እንዴት የተካሄደ ምርጫ? ለምርጫው የተደረገው ዝግጅት ምንድን ነው? የጉዳዩ ባለቤቶች ሙሉ ተሳትፎ እንዲያደርጉ አሸጋጋሪው ክፍል ያስቀመጠው ትክክለኛ መድረክ ምንድን ነው? ባጠቃላይም፤ ሁኔታው ገዥ ነው። ለምርጫ በሚደረገው ሩጫ፤ ብዙ ኢትዮጵያዊያን የግፍ በደል ይደርስባቸዋል! የሚል ስጋት አለኝ። ምርጫ አለመካሄዱ ትክክል ነው ማለቴ አይደለም። ነገር ግን፤ ምርጫው እንዲካሄድ ብቻ ሳይሆን፤ መራጩና ተመራጩ፤ ሁለገብ ክንውኖቹ ትክክል ናቸው! ብሎ ማመኑ ወሳኝ ነው።

ባሁኑ ሰዓት፤ ሰማይ ተሰብሮ ካልወደቀ በስተቀር፤ ምርጫው ይካሄዳል። ውጤቱ ማንን ያስደስት ይሆን? ይህ ሌላ ጥያቄ ነው። “ሊታይ አይደል!” አለች ሴትዬዋ። ነገር ግን ምርጫ ትርጉም የሚኖረው፤ መጀመሪያ እያንዳንዱ ዜጋ በኢትዮጵያዊነቱ አምኖ፣ ሁሉም የሚቀበለው ሕገመንግሥት ኖሮ፣ ባለው ሕገመንግሥት ተገዢ ለመሆን ሁሉም ተስማምቶ፣ ለምርጫው በተደረገው ዝግጅት መተማመን ሲገኝ ነው። ይሄ እንዳልሆነ ሁላችንም እናውቃለን። ታዲያ ምርጫው ለይስሙላና ነው ወይንስ እውነትን ለማንገሥ? ሌሎች በተደጋጋሚ ያስቀመጡት ቢሆንም፤ አሁንም እኔ ላስምርበት የምፈልገው፤ የመሸጋገሪያ ጊዜ እንደሚያስፈልግና፤ የሽግግር መንግሥት የግድ መቀመጥ እንዳለበት ነው። ካለንበት አስቸጋሪ ሁኔታ ለመውጣት የማያዳግመው መፍትሔ፤ ሁላችን በአንድነት የምንስማማበት ምርጫ ብቻ ሳይሆን፤ በምርጫው ውጤትም የምናምንበት መሆኑ ነው።

አሁን አገራችን ላፈጠጠባት ችግር፤ ከኛ በስተቀር፤ ሌላ ከሰማይ ወርዶ የሚፈታው አካል የለም። ወደድንም ጠላንም እኛው የፈጠርነውና፤ እኛው የግድ መፍታት ያለብን፤ የኛው የራሳችን ኃላፊነት ነው። ምንድን ነው ችግራችን?

የመጀመሪያው፤ በዘር ከፋፍሎ ሲገዛን የነበረውን መንግሥት፤ ከሥልጣን እንዳስወገድን ሁሉ፤ ያ መንግሥት ሲገዛበት የነበረውን ሕገመንግሥት፣ የፖለቲካ ፍልስፍናና የአስተዳደር መመሪያ፤ አብረን ማስወገድ ነው። ያለፈው መንግሥት ባደረገው ያላባራ ፀረኢትዮጵያዊነት ሰበካ፤ ለረጅም ጊዜ የተፈታተነው ወገናችን፤ ኢትዮጵያዊነትን ወደ ማዕከል በማምጣት፤ አንድነትን የኑሯችን ምሰሶ ማድረግ አለብን። ለዚህ የሽግግር ወቅት ያስፈልጋል። ብልፅግና ይሄን እያደረገ አይደለም ያለው። እኔ አሻግራችኋለሁ በሚል ዘይቤ፤ የሥልጣን ኮርቻውን በማደላደል ላይ ሰንብቷል። ለውጡ ከዋዘበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን፤ የመሸጋገር ሂደት አልተከናወነም። በሚቀጥለው ምርጫ ማንም ያቸንፍ ማን፤ ውጤቱ አብዛኛዎቻችንን አያረካም። በ “ብሔር” ክፍፍሉ ላይ የተመሠረተ አገዛዝ ቀጣይ ነው። ብልፅግና ከብሔር ድርጅትነት ፈጽሞ ሊነጻ አይችልም። ነገም በየጎራው ያለው ብልፅግና፤ “ከኔ ውጪ፤ ሌላ ድርጅት፤ በኔ ብሔር ውስጥ ድርሽ አይልም!” ብሎ ይዘምታል! የሚል ስጋት አለኝ። መተማመንና መሿሿም አሁንም በዚሁ መሠረት ይቀጥላል! ባይ ነኝ። ኢትዮጵያዊነት መጀመሪያ እስካልነገሠ ድረስ፤ ነገም እንደዛሬው ጥያቄው፤ እነማን ናቸው በሥልጣን ላይ ያሉት? የሚለው ይቀጥላል። ይህ ደግሞ እንቅልፍ ይነሳናል።

የፌዴራል መንግሥቱን የባለሥልጣናትንና የተቀጣሪዎችን ስብጥር በየራሳችን መነፅር መመልከታችን አይቀሬ ነው። ማነው በጦር ሠራዊቱ ክፍል የበላይነቱን የያዘ? በትምህርትና በአስተዳደርስ? እያልን ማንጎራጎራችን አያባራም። በኢሕአዴግ አገዛዝ መሠረት፤ የፌዴራል መንግሥት ሥራ አመዳደብ ምን ይመስል ነበር? ስንቱ ነው የራሱን ወገን አባላት፤ ምንም ችሎታውና ብቃቱ የሌላቸውን ያግበሰበሰው? ስንቱ ነው የራሱን ኪስ ለማሳበጥና የዛሬን ልኑር በሚል ዘይቤ አገር የበደለው? ስንቱ ነው፤ የዚህ ወይንም የዚያ ብሔር አባል በመሆኑ ባንድ ቀን አዳር ልኬየለሽ ባለፀጋ የሆነው? ይህ ደግሞ ስንቶቹን ነው፤ ራሳቸውን ከማሻሻል ይልቅ፤ ገንዘብ ማግበስበሱ ላይ ተጠምደው፤ የአገራችንን ሀብት መዝረፉ ላይ የተሰማሩት? በዚህ ሂደት፤ ምን ያህል ነው፤ ብቃትና ጥራት መስዋዕት የተደረጉት? በዚህ ሂደት ስንቶቹ ናቸው አገር ለቀው የተሰደዱት? ይህ ሊቆረቁረን ይገባል። ከ66 እስከ 84 የነበረውን የመንግሥቱ ኃይለማርያም የደርግ መንግሥት፣ ከ84 እስከ 2009 የነበረውን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት፣ አልነበረም ብለን ዓይኖቻችንን ጨፍነን ልንክድ አንችልም። እኒህ መንግሥታት ደግሞ አሻራቸውን፤ በሕገመንግሥቱ፣ በመንግሥታዊ አወቃቀሩ፣ በሰዎች አዕምሮ ውስጥም ጭምር ጥለው አልፈዋል። ታዲያ መንግሥታቱን ካስወገድን በኋላ፤ የስርዓቶቻቸው መሠረት የሆኑትን አሰራሮቻቸውን ማስወገድ የለብንም? ለዚህ የሽግግር መንግሥት የግድ ያስፈልጋል።

የብዙዎች የተለያዩ ቋንቋዎች መነገሪያ በሆነችው አገራችን፣ ብዙ የተለያዩ ባሕሎች በሚፍነሰነሱባት አገራችን፣ በጣም ረጅም የሆነ አኩሪ ታሪክ ባላት አገራችን፣ ብዙ አስቸጋሪ የሆኑ ፈተናዎችን ባሳለፈችው አገራችን፤ የዚህ ሁሉ ባለቤት የሆነው እኛ፤ አገራችንን በተራችን አሁን ካለንበት አንጻራዊ እንቅፋት ማውጣት እንችላለን። ዴሞክራሲያዊ አሰራርን የሀገራችን የሥልጣን መመሪያ ማድረግ እንችላለን። ይቺ አገራችን ከምትችለው በላይ ሠጥታናለች። እኛ ምን መለስንላት? በአገራችን ላይ ያለው ድህነት፤ በፖለቲካው ሂደት ምን ያህል እየተጫወተ ነው? በመካከላችን ያለው የባህል የቋንቋና የሃይማኖት ልዩነት፤ ለዜግነት አንድነታችንን ምን ያህል እንቅፍት እንዲሆን እንፈቅዳለታለን?

የግል ደህንነትንና ብልፅግናን፤ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ብልፅግናና ደህንነት ጋር አያይዘን፤ ራሳችንን የአገራችንና የመላ ኢትዮጵያዊያን አካል በማድረግ፤ ለጋራ ብልፅግናችን የምንሠራበትን እውነታ ማብሰር እንችላለን። ይሄን ማድረግ እንችላለን። ይሄን ማድረግ አለብን። ቢያንስ ከብልፅግና ውጪ ያለን፤ በፖለቲካው ዓለም ኢትዮጵያዊነትን የምናስቀድም ድርጅቶችና ግለሰቦች፤ ለዚህ ዓላማ ቆርጠን መቆም ይኖርብናል። ሀቁ እንደዘረዘርኩት ቀላል አይደለም። ነገር ግን፤ የሚከተለውን አደጋ ተረድተን ይሄን ካላደረግን፤ ነገ ራሳችንን ወቃሾች ነን። አሁን ዋናው ጥያቄ መሆን ያለበት፤ የሽግግር መንግሥት ማቋቋም ነው።