የአውሮፓ ሕብረት ምክር ቤት በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች በሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ላይ የሚፈጸመውን አስከፊ አያያዝና የሰብአዊ መብት ጥሰት በጽኑ የሚያወግዝ የውሳኔ ሐሳብ አሳለፈ።
ፓርላማው ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው በሳዑዲ አረቢያ፣ በኤርትራና በኒካራጓ ውስጥ ያሉ የሰብአዊ መብት ጉዳዮችን በተመለከተበት ጉባኤ ላይ ሲሆን፤ በዚህም በሳዑዲ ያሉ ኢትዮጵያዊያን አያያዝ ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ በማንሳት ነው የውሳኔ ሐሳብ ያሳለፈው።
የአውሮፓ ሕብረት ምክር ቤት አሁን ድረስ በሳዑዲ እስር ቤቶች ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ተይዘው ሰብአዊ መብቶቻቸው ተጥሶ እንደሚገኝ ጠቅሶ ሁኔታውን አውግዞታል።
ሕብረቱ ያስተላለፈው የውሳኔ ሃሳብ ተከትሎ የአውሮፓ ሕብረት ልዑኮች በሳኡዲ አረቢያ ማጎሪያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች እንደሚጎበኙ የአውሮፓ ሕብረት ፓርላማ አባል የሆኑት ሰሚራ ራፋኤላ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የሰብዓዊ መብቶች ሳይከበሩ ቀርተው ስንመለከት ለእኛ ሁሌም አሳሳቢ ነገር ነው የሚሉት ሰሚራ፣ የሰብዓዊ መበት ጥሰት በማንም ላይ የትም ቦታ ሲከሰት ድምጻችንን ከፍ አድርገን እንናገራለን ሲሉ ያስረዳሉ።
ሕብረቱ ለምን አስቸኳይ የውሳኔ ሃሳብ እንዲሰጥ እንዳደረገ ሲያብራሩም፣ ከሳኡዲ አረቢያ እስር ቤቶች እየወጡ ያሉ ምስሎችን እንዲሁም ሪፖርቶችን መመልከታቸውንና የስደተኞቹ ጉዳይም እጅግ አሳሳቢ ሆኖ ማግኘታቸውን ገልፀዋል።
የሂውማን ራይትስ ዎች ሪፖርትን የጠቀሰው ፓርላማው ከባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር አንስቶ በግድ ከየመን ተገፍተው እንዲወጡ የተደረጉ ነፍሰጡር ሴቶችና ህጻናት የሚገኙባቸው 30 ሺህ የሚደርሱ ኢትዮጵያዊያን ያለፍርድ በአሰቃቂ ሁኔታ ሳዑዲ ውስጥ ባሉ እስር ቤቶች እንደሚገኙ አመልክቷል።.
ስለዚህም የአውሮፓ ሕብረት ምክር ቤት አባላት የሳዑዲ አረቢያ ባለስልጣናት ሴቶችና ህጻናትን ጨምሮ ለችግር የተጋለጡትን ቅድሚያ በመስጠት በአስቸኳይ እንዲለቁ ጥሪ አቅርቧል።
ጨምረውም የሳዑዲ ባለስልጣናት በጦርነት ውስጥ ከምትገኘው ጎረቤት የመን ሸሽተው ወደ ግዛታቸው የሚገቡ ሰዎችን ደኅንነታቸው በተጠበቀ ሁኔታ ተቀብለው ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን ወደጠበቁ የማቆያ ማዕከላት እንዲገቡ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
በምክር ቤቱ የተላለፈው የውሳኔ ሐሳብ በማጠቃለያው ላይ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት በእስር ቤት ውስጥ በሚገኙት ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ላይ የሚፈጸሙ ሰቆቃዎችና አስከፊ አያያዞች በአስቸኳይ እንዲቆሙና ለታሳሪዎቹ ተገቢው ሥነ አእምሯዊና አካላዊ እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ጠይቋል።
የሕብረቱ ፖርላማ አባል ሰሚራ ራፋኤላ እንደሚሉት የሕብረቱን የውሳኔ ሳኡዲ አረቢያ ስደተኞችን ይዛ የምትገኝበትን ሁኔታ በአፋጣኝ እንድታሻሽል ይጠይቃል።
የአውሮፓ ሕብረት ልዑኮቹን ወደ ስፍራው ልኮ ስደተኞች ያሉበትን ሁኔታን ይጎበኛል። ስላሉበት ሁኔታም ስደተኞቹን ያነጋግራል። በዚህም በማጎሪያ ቤቶች ውስጥ እየሆነ ያለውን መረዳት ይቻላል። የሳኡዲ አረቢያ መንግሥት በፍጥነት ስደተኞች ተይዘው ያሉበትን ሁኔታ እንዲያሻሽልም ይፋዊ ጥሪ ቀርቦለታል።
ከኢትዮጵያ እና ሳዑዲ አረቢያ መንግሥታት ጋር በአንድም ሆነ በሌላ መንግድ አብረን እንሰራለን የሚሉት ሰሚራ፣ በስደተኞቹ ላይ የሚደርሰውን በደል አይተን ዝም ብለን ማለፍ እንደማይችሉ ሁለቱም አገራት የስደተኞቹ ሰብዓዊ መበት እንዲከበር እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ለቢቢሲ አክለው ተናግረዋል።
በሳዑዲ አረቢያ በአስከፊ ሁኔታ በእስር ቤት የሚገኙትን ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን በሚመለከት የተለያዩ መገናኛ ብዙሃንና የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች ተደጋጋሚ ሪፖርቶችን ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
ኢትዮጵያውያን ስደተኞቹ ለጤናና ለህይወት አስጊ በሆነ ሁኔታ በተጨናነቁ እስር ቤቶች ለወራት ከመቆየታቸው የተነሳ ለተለያዩ ህመሞች መጋለጣቸውና ህይወታቸው ያለፈም እንዳለ ቢቢሲና የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን መዘገባቸው ይታወቃል።
ምክር ቤቱ በተጨማሪም በኤርትራ የሚገኙ የህሊና እስረኞች በተለይም ከዛሬ 19 ዓመት በፊት ለእስር የተዳረገውን ስውዲናዊውን ዳዊት ይስሃቅን ጨምሮ በርካታ ጋዜጠኞች እንዲለቀቁ ጠይቋል።
ቢቢሲ