10 ጥቅምት 2020, 08:00 EAT

እንደ ዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ከሆነ ከኮሮናቫይረሰ ወረርሽኝ መከሰት በኋላ በአፍሪካ የአእምሮ ጤና መታወክ እየተከሰተ መጥቷል።
ድርጅቱ ባለፈው ሐሙስ እለት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተባለው፤ በአፍሪካ የአእምሮ ጤና መታወክ ከኮቪድ-19 በኋላ መጨመር አሳይቷል። የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የሕክምና አገልግሎቶችን በማስተጓጎሉ ሁኔታውን የበለጠ ፈታኝ አድርጎታል።
በዛምቢያ የአእምሮ ጤና ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ሪም ዳላል እንዳሉት፤ በአህጉሪቱ ከወረርሽኙ በኋላ የአእምሮ ጤና ችግሮች ስለመባባሳቸው መረጃዎች አሉ።
በዚህ ሳምንት በአፍሪካ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ1.5 ሚሊዮን ያለፈ ሲሆን ቢያንስ ከ36,787 በላይ ሰዎች ደግሞ ሞተዋል።
በኢትዮጵያም በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች 82,662 የደረሱ ሲሆን የሟቾች ቁጥር 1,271 ደርሷል።
ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የአእምሮ ህክምና ትምህርት ክፍል መምህር እና ሐኪም ናቸው።
ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ሊከሰቱ የሚችሉ የአእምሮ ህመሞች በጣም ሰፊ መሆናቸውን ይናገራሉ።
ወረርሽኙ በራሴ፣ በቤተሰቤና በአካባቢዬ ላይ ይከሰታል የሚለው ስሜት ከፍተኛ ፍርሃት፣ ጭንቀት፣ ድብርት እንዲያም ከፍተኛ ወደ ሆነ የአእምሮ መረበሽ ሊያደርስ ይችላል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ኮቪድ-19 በአካል ላይ በሚያደርሰው ጉዳት ምክንያት በአካባቢያችንና በቤተሰባችን ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ከዚህም ጋር በተያያዘ የሚከሰተው ሰርቶ ያለማደርና ቤት ውስጥ ተዘግቶ መዋል ከፍተኛ ጭንቀትና ድብርት እንደሚያስከትል ይናገራሉ።
ሕጻናት እና የአእምሮ ጤና
ሕጻናትና ሴቶች በቤት ውስጥ ወይንም በአንድ አካባቢ ብቻ መዋላቸው ከሚያደርስባቸው የአእምሮ ጤና ችግር በላይ በተቃራኒ ጾታ የሚደርስባቸው ጥቃት መስተዋሉን ፕሮፌሰሩ ያነሳሉ።
ላለፉት ሰባት ወራት ከመዋዕለ ሕጻናት ጀምሮ እስከ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ድረስ ከትምህርት ገበታ ርቀው በቤት ውስጥ መቆየታቸውን በማስታወስም፤ ይህ የአእምሮ ጤና ላይ ጫና እንዳለው ያብራራሉ።
ልጆች እየተሯሯጡ፣ ከእኩዩቻቸው ጋር ሲጫወቱ አካላቸው ብቻ ሳይሆን ማኅበራዊ መስተጋብራቸውም እያደገ እንደሚመጣ የሚያስረዱት ፕሮፌሰሩ፤ እነዚህ ሕጻናት በጋራ ሲጫወቱ አንዳቸው ከሌላኛቸው የሚማሩት እውቀትና ክህሎት ከፍተኛ መሆኑን በማንሳት፤ ለረዥም ወራት በአንድ አነስተኛ ግቢ ወይንም ቤት ውስጥ ተገድቦ መቀመጥ ለሕጻናቱ ከፍተኛ ጫና መሆኑን ያነሳሉ።
ከዚህም የተነሳ ሕጻናቱ በከፍተኛ ሁኔታ ሊሰላቹ፣ ሊጨናነቁ፣ ሊወጣጠሩ ይችላሉ ብለዋል።
ሕጻናቱ እንደ አዋቂዎች የሚሰማቸውን መናገር አለመቻላቸው ሌላው ችግር በመሆኑ ለተለያዩ የሕጻናት የአእምሮ ጤና ችግር ሊጋለጡ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
በተለይ በከተማ የሚኖሩ እና የተማሩ የሚባሉት ወላጆች ልጆችን ከኤሌክትሮኒክስ ጋር ስለሚያጋፍጧቸው ለኮምፒውተር ጌም ሱስ እንደሚያጋልጧቸው ይገልፃሉ።
በዚህም የተነሳ ትምህርት በሚከፈትበት ወቅት ከእኩዮቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት በከፍተኛ ሁኔታ ሊጎዳ እንደሚችል ጨምረው አብራርተዋል።
ወረርሽኞች የአእምሮ ጤና ችግር ያስከትላሉ?
“የሚገድሉ ሕመሞች በጣም ያስጨንቃሉ” የሚሉት ፕሮፌሰር መስፍን፤ ተላላፊ በሽታዎች ግለሰቦች ላይ ባይደርስ እንኳን ገና ለገና ‘ይመጣብኛል’ የሚለው ስጋት እንደሚያሳቅቅ ይናገራሉ።
እንደ ኮሌራና ኢቦላ ያሉ ወረርሽኞች ተመሳሳይ ተጽዕኖ እንዳላቸው የሚገልፁት ፕሮፌሰሩ፤ የኮሮናቫይረስ ባህሪ በየጊዜው ይበልጥ በታወቀ ቁጥር የሚፈጥረው ስጋትና ጭንቀት እየጨመረ እንደሚመጣ ገልፀዋል።
መጀመሪያ ላይ በእድሜ የገፉ ሰዎች ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው የሚለው መረጃ ከተሰማ በኋላ፣ ወጣቶችና ሕጻናትም ተጋላጭ መሆናቸው መታወቁ፣ ተጓዳኝ በሽታ ያለባቸው ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው የሚለው መረጃ ከተሰራጨ በኋላ፣ የሌለባቸውም ተጋላጭ መሆናቸው መታየቱ፤ “ጭንቀት በሰው ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ እንዲመጣ” ማድረጉን ይናገራሉ።
ገና ለገና በሽታው ይመጣብኛል የሚለው አስጨናቂ መሆኑን ተናግረው፤ ጭንቀትን የሚያባብሰው ከራስ አልፎ ለቅርብ ቤተሰብ የሚኖረው ስጋት ነው ይላሉ።
ቤተሰቦቼ ይያዙ ይሆን? ምልክት ሳላሳይ ቫይረሱን ይዤ እየዞርኩ ይሆን? በእድሜ የገፉ ወላጆቼን፣ ታማሚ ቤተሰቦቼን፣ ልጆቼን አስይዝ ይሆን? የሚሉት የበለጠ ያስጨንቃሉ።
- ኮሮናቫይረስ ሲጠፋ እንጨባበጥ ይሆን? ሳይንቲስቶች “በፍጹም!” ይላሉ
- “ሴቶች የታሪክ አካል ተደርገው አይቆጠሩም፤ በታሪክነትም አናወሳቸውም” መዓዛ መንግሥቴ
- የአእምሮ ምጥቀት (IQ) ምንድን ነው?
ከዚህ በሽታ ጋር ተያይዞ መጀመሪያ የሚከሰተው የጤና ችግር ጭንቀት የሚባለው መሆኑን ፕሮፌሰር መስፍን ይናገራሉ። ይህ ከቀላል ጭንቀት ጀምሮ እስከ ከፍተኛው እንደሚደርስ ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል።
በኮቪድ-19 የተያዘ ሰው በቤተሰብ ውስጥ ሲገኝ ደግሞ ሕመሙ በመከሰቱ ለበለጠ ጭንቀት መጋለጥ እንደሚኖር እንዲሁም ሊባባስ እንደሚችልም ያብራራሉ።
በቫይረሱ የተያዘ የቤተሰብ አባል በሞት ሲታጣ ደግሞ ወደ ተራዘመ ሐዘንና ጭንቀት፣ ባስ ሲልም ወደ ድብርት ሊያስገባ ይችላል ይላሉ።
ፕሮፌሰር መስፍን፤ ቫይረሱ በአካል ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት በተጨማሪ አንጎል ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖና ሊከሰቱ የሚችሉ አእምሮ ጤና ችግሮች ገና እየተጠኑ መሆኑን ይናገራሉ።
ኮቪድ-19 በአእምሮ ላይ የሚያሳድረው ዘላቂ ጫና
አንዳንድ ጊዜ አንጎል ሲመረዝ ከፍተኛ የሆነ የመርሳት ችግር (ዲሜንሺያ) ወይንም ከፍተኛ የአእምሮ ሕመሞች ሊከሰቱ የሚችሉበት እድል አለ ይላሉ ፕሮፌሰሩ።
እንደ አእምሮ ጤና ባለሙያ፤ “ኮቪድ 19 በአካል ላይ ከሚያደርሰው ችግር በላይ፤ ከወረርሽኙ መረጋጋት በኋላ የሚመጣው የአእምሮ ጤና ችግር ለብዙ ዓሥርት ዓመታት ይቀጥላል ብለን እናምናለን” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በኮቪድ -19 ተይዘው ሕመም የጠናባቸውና የትንፋሽ ማገዣ መሣሪያ ላይ ያሉ ሰዎች በአብዛኛው የመትረፍ እድላቸው አነስተኛ መሆኑን ያስታወሱት ፕሮፌሰር መስፍን፤ በመተንፈሻ ታግዘው ጤናቸው ሲመለስ ደግሞ ለከፍተኛ ጭንቀት እንደሚዳረጉ ማስተዋላቸውን ገልፀዋል።
እነርሱ በመሣሪያ እየታገዙ ተንፍሰው ሲድኑ፤ ሌሎች ግን ከጎናቸው በመሣሪያ እየተረዱም መትረፍ ሳይችሉ ቀርተው ሲመለከቱ የሚደርስባቸው ሥነ ልቦናዊ ጫና እንዳለ ገልፀዋል።
እነዚህ ሰዎች በመትረፋቸው ተመስገን ቢሉም ጭንቀትም ሆነ ድብርት ሊታይባቸው እንደሚችል ከልምዳቸው በመነሳት ያስረዳሉ።
ፕሮፌሰሩ አክለውም በተለይ የሕክምና ባለሙያዎች ራሳቸውን መስዋዕት አድርገው ስለሚሠሩ ከራሳቸው አልፎ በእድሜ ለገፉ ወላጆቻቸው፣ ለቅርብ ቤተሰቦቻቸው ተጨንቀው ማስተዋላቸውንም ገልፀዋል።