9 ጥቅምት 2020

አቶ ይማም መሐመድ በራያ ቆቦ ወረዳ የ024 ያያ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው።
በአካባቢው ጤፍ፣ በቆሎ፣ ማሽላ፣ አተርና ሽንብራ የሚመረት መሆኑን ጠቅሰው አብዛኛው ማሳ የተሸፈነው በማሽላ እንደሆነ ይናገራሉ።
ቀደም ሲል በአፋር ክልል የአንበጣ መንጋ መከሰቱን እንደሰሙ እና ወደ አካባቢያቸው ሳይመጣ ለመከላከል እንዳልተቻለ ጠቁመዋል።
መስከረም 6 ጀምሮ ወደ አካባቢው መግባት የጀመረው የበረሃ አንበጣ መንጋን ለመከላከል ጥረት ቢያደርጉም መከላከል አልቻልንም ብለዋል።
“አንዱን ንዑስ ቀበሌ ሲያጠናቅቅ [እኛም] እያፈገፈግን ስንከላከል አሸነፈን። አሁን ሙሉ በሙሉ [ሰብሉን] አጠናቀቀ” ሲሉ የለፉበት ሰብል መውደሙን ይናገራሉ።
”[አሁን] ዝም ብለን ቆመን እያየን ነው። ተዓምር ነገር ነው የምናየው።”
“ከመስከረም 6 እስከ አሁን አርሶ አደሩ ቤቱ ሳይገባ ታገለ። ምንም ማድረግ አልተቻለም. . . የሚበላብንን ነገር ጨርሷል፤ ከእንግዲህ ወዲያ ተስፋ የለንም” ብለዋል።
በቀበሌው ያለውን ሰብል ሙሉ ለሙሉ ከመጨረስ ባለፈ ወደ አጎራባች ቀበሌዎች እየገባ መሆኑንም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የዘንድሮ አዝመራ ‘ጥሩ እና ቆንጆ’ የሚባል እንደነበር የሚናገሩት አቶ ይማም፤ ሆኖም የአንበጣው መንጋ እንዳወደመውና መንግሥት ኬሚካል አቅርቦ፣ አርሶ አደሩ ደግሞ ጅራፍ እና ቆርቆሮ በመጠቀም በዘመናዊ እና ባህላዊ መንገድ ለመከላከል የተደረገው ጥረት አልተሳካም ብለዋል።
እህል ከኅዳር አጋማሽ ጀምሮ ነበር መሰብሰብ የነበረበት ያሉት አርሶ አደሩ ለመሰብሰብ ያልደረሰ በመሆኑ በአንበጣ መንጋው መበላጡን ጠቁመዋል።
- በአማራ ክልል 80 ሺ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ላይ የአንበጣ መንጋ ተከስቷል
- በኢትዮጵያ የጸረ አንበጣ ኬሚካል በመርጨት ላይ የነበረ ሄሊኮፕተር ተከሰከሰ
- አሳሳቢው የአንበጣ መንጋ ስጋት በኢትዮጵያና በአካባቢው አገራት
- የአንበጣ ወረራ በምስራቅ አፍሪካ አገራት ሊዛመት እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት አስጠነቀቀ
የአንበጣ መንጋው ባደረሰው ጉዳት ግራ የተጋቡት አርሶ አደሩ ምንም ማድረግ እንዳልቻሉ ይናገራሉ። “ዝም ብለን ቁጭ ብለናል። ከባድ ነው በጣም። ዝናብ ከጣለ ለበልግ እናርሳለን ብለን ቁጭ ብለናል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
አርሶ አደር ሙስጠፋ አሸብርም የራያ ቆቦ ነዋሪ ናቸው።
ከመስከረም መጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ አንበጣውን በኬሚካልም ሆነ በባህላዊ መንገድ ለመከላከል ባለመቻላቸው አካባቢውን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥሮታል ብለዋል።
“ቀደም ብሎ ሁለት ቀበሌዎች ገባ። ቀዳሚዎቹ ንዑስ ቀበሌ 2 እና 3 ናቸው። አዚያ አሁን ሰብሉ አልቋል። አሁን ወደ ንዑስ ቀበሌ አንድ አቀንቷል። አዚያ አዳርሶ ወደ ቀበሌ 023 ሊገባ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
“ጥይት ቢተኮስ፣ እሪ ቢባል እና መርዝ ቢረጭ አንዴ ከገባ አይነሳም” ሲሉ የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል እንደተቸገሩ ይናገራሉ።
አንበጣው ባለባቸው አካባቢዎች ሰብል ላይ ጉዳት ማድረሱንም ጠቀሙዋል።
“ተስፋችን ምናልባት የበልግ ዝናብ ከጣለ በልግ እንዘራለን ነው እንጂ ምን ተስፋ አለን?” ሲሉ ማሳ ላይ የነበረው ሰብል መውደሙን አመልክተዋል።
መንግሥት ዝናብ አግኝተው ለበልግ እስኪዘሩ ድረስ ድጋፍ እንዲያደርግላቸውም ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋሁን መንግሥቴ የአንበጣው መንጋ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ጉዳት ማድረሱን አረጋግጠዋል።
ጉዳቱ በምሥራቅ አማራ ሦስት ዞኖች መከሰቱን ጠቁመው መጠኑ ግን በባለሙያዎች ተጠንቶ ይፋ ይደረጋል ብለዋል።
የአንበጣ መንጋው በደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎ እና ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞኖች መከሰቱን ገልጸው፤ በተጨማሪም ጉዳቱ የከፋ ባይሆንም በሰሜን ሸዋ ዞን ቀወት ወረዳ በቅርቡ የአንበጣ መንጋው መከሰቱንም ያብራራሉ።
በእነዚህ አካባቢዎች ከ151 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ አሰሳ ተደርጎ በ78 ሺህ 800 ሄክታር ላይ የአንበጣ መንጋው መከሰቱ መረጋገጡን ምክትል ቢሮ ኃላፊው ገልፀዋል።
የአንበጣ መንጋውን ለመከላከልም በሰው ኃይል እና በአውሮፕላን በመታገዝ ቢያንስ ከ51 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነውን መሬት ማጽዳት ተችሏል ብለዋል።
ነገር ግን አሁን አንበጣው መብረር ስለጀመረ ከእስካሁኑ የከፋ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ይገመታል ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
እንድ ምክትል ኃላፊው ከሆነ ችግሩን ለመቅረፍ ኅብረተሰቡን በማሳተፍ እና በአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት በማካሄድ እየተሠራ ነው።
በአንዳንድ ቦታዎች ያለውን የአንበጣ መንጋ በአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት ካልሆነ መቆጣጠር የማይቻል ነው ሲሉ የችግሩን ጥልቀት ያስረዳሉ።
የመከላከል ሥራው ካልተጠናከረ ወደ ሌሎች አካባቢዎች በንፋስ ኃይል እየተገፋ ሊሠፋ ይችላል ያሉት አቶ ተስፋሁን ለዚህም እየተሠራ ነው ነው ብለዋል።
ከወራት በፊት ጀምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በመከሰት በእጸዋት ላይ ጉዳት እያደረሰ ያለው የአንበጣ መንጋ፤ በአሁኑ ጊዜ በሰሜና፣ በሰሜን ምሥራቅና በመካከለኛው የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው።
በአንበጣ መንጋው ሳቢያ በሰብል ላይ በደረሰ ጉዳት በብዙ ቦታዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች ለችግር ሊጋለጡ እንደሚችሉ እየተነገረ ነው።
አንበጣ መንጋ፡ በአማራ ክልል 80 ሺ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ላይ የአንበጣ መንጋ ተከስቷል
6 ጥቅምት 2020

በአማራ ክልል ከመስከረም ወር መጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን የክልሉ ባለስልጣናት ለቢቢሲ ተናገሩ።
የአንበጣ መንጋው በአንዳንድ ቀበሌዎች የተዘራ ሰብልን ሙሉ በሙሉ ያወደመ ሲሆን በአንዳንዶቹ ደግሞ የጉዳት መጠኑ ከ50 በመቶ በላይ መሆኑ ተገልጿል።
በአማራ ክልል በሚገኙ ሦስት ዞኖች፣ በስምንት ወረዳዎች እና በ66 ቀበሌዎች የአንበጣ ወረርሽኝ መከሰቱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋሁን መንግስቴ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
በክልሉ ከሚገኙት የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ደቡብ ወሎ እና ሰሜን ወሎ ዞኖች በተጨማሪ ጉዳቱ ያን ያክል የከፋ ባይሆንም በሰሜን ሸዋ ዞን ቀወት ወረዳ በቅርቡ ወረርሽኙ መከሰቱንም ያብራራሉ።
በእነዚህ አካባቢዎች ከ151 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ አሰሳ ተደርጎ በ78 ሺህ 800 ሄክታር ላይ የአንበጣ መንጋው መከሰቱ መረጋገጡን ምክትል ቢሮ ኃላፊው ገልፀዋል።
የአንበጣ መንጋውን ለመከላከልም በሰው ሃይል እና በአውሮፕላን በመታገዝ ቢያንስ ከ51 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነውን መሬት ማጽዳት ተችሏል ብለዋል።
ነገር ግን አሁን አንበጣው መብረር ስለጀመረ ከእስካሁኑ የከፋ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ይገመታል ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
አቶ ተስፋሁን ይህንን ከግንዛቤ በማስገባት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ይናገራሉ።
የአማራ ክልል ከአፋር ክልል ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች ከሰሜን ሸዋ ዞን ቀወት እስከ ሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳ ድረስ ባለው አካባቢ የአንበጣ መንጋው በስፋት መከሰቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
- የአንበጣ ወረራ በምስራቅ አፍሪካ አገራት ሊዛመት እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት አስጠነቀቀ
- ሶማሊያዊያን የአንበጣውን መንጋ ለምግብነት በማዋል እየተዋጉት ነው
- ኢትዮጵያ የአንበጣ መንጋ ስጋት ከደቀነባቸው አገራት መካከል ናት
- የአንበጣ መንጋው እስካሁን በሰብል ላይ ጉዳት አላደረሰም
በየአካባቢው በተለያየ ጊዜ አንበጣው የተከሰተ ሲሆን፤ በአብዛኛው ግን ከመስከረም ወር የመጀመሪያው ሳምንት ጀምሮ የተከሰተ መሆኑንም ጨምረው ያስረዳሉ።
በራያ ቆቦ ወረዳ የአንበጣ መንጋው ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተው በመስከረም ስድስት ነው ያሉት የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ መንገሻ አሸብር፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሕብረተሰቡ በተለያዩ የመከላከያ መንገዶች ለመከላከል ጥረት ቢያደርግም በየቀኑ ከአፋር ክልል እየተፈለፈለ የሚመጣው አዲስ የአንበጣ መንጋ ከአቅም በላይ እየሆነ መምጣቱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአንበጣ መንጋው በወረዳው ከአፋር ክልል ጋር በሚዋሰኑ ዘጠኝ ቀበሌዎች የተከሰተ መሆኑን የተናገሩት አቶ መንገሻ፤ ወርቄ እና ያያ የሚባሉ ቀበሌዎች ላይ በሰብል ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ብለዋል።
በእነዚህ ቀበሌዎች እስከ 500 ሄክታር ድረስ በሰብል የተሸፈነ መሬት በአበንጣው መጎዳቱንም ገልጸዋል።
የጉዳት መጠኑም ከ50 እስከ 100 በመቶ መድረሱን አስተዳዳሪው በማስረዳት፤ እስካሁን ከ20 ሺህ ሄክታር በላይ ቅኝት በማድረግ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን መከላከል መቻሉንም ገልጸዋል።
በሃብሩ ወረዳ በተመሳሳይ በዘጠኝ ቀበሌዎች ላይ የአንበጣ መንጋው ጉዳት ማድረሱን የሚናገሩት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዮሃንስ ተሰሜ እንደገለጹት፤ አንድ ቀበሌ ሙሉ በሙሉ የወደመ ሲሆን፤ በሌላ አንድ ቀበሌ ላይ ደግሞ ከ50 እስከ 100 በመቶ የሚሆን ሰብል ላይ ጉዳት ደርሷል ብለዋል።
እስከሁን በባህላዊ መንገድ እና በኬሚካል ርጭት የመከላከል ስራው እየተሰራ ነው። በአውሮፕላን የታገዘ ርጭት የተደረገ ቢሆንም አካባቢው ካለው መልከዓ ምድራዊ ስፋት አንጻር በቂ ርጭት አለመደረጉን አቶ ዮሃንስ ያነሳሉ።
በሃብሩ ወረዳ በአውሮፕላን የታገዘ ርጭት የተደረገው ሦስት ጊዜ ብቻ መሆኑንም ያስረዳሉ።
አንበጣው በየጊዜው የሚጨምር እና የወረራ መጠኑም ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚሰፋ በመሆኑ የአደጋውን አስቸጋሪነት ከፍ እንዳደረገው አቶ ዮሃንስ ገልጸዋል።
- በኢትዮጵያ የጸረ አንበጣ ኬሚካል በመርጨት ላይ የነበረ ሄሊኮፕተር ተከሰከሰ
- አሳሳቢው የአንበጣ መንጋ ስጋት በኢትዮጵያና በአካባቢው አገራት
- በአንበጣ መንጋ ስጋት ሶማሊያ ብሔራዊ አደጋ አዋጅ አወጀች
አቶ ዮሃንስ አውሮፕላኑ ለርጭት ስምሪት የሚሰጠው ከሰመራ መሆኑን በማንሳት ይህም መጓተት ማስከተሉን ተናግረዋል። ይህ በቅርበት ለመወያየት አመች ስለማይሆን ወደ ኮምቦልቻ ቢቀየር የተሻለ መሆኑንም አመላክተዋል።
ሰመራ ላይ የነበረው አውሮፕላን መነሻው ከ25/01/13 ዓ. ም. ጀምሮ ወደ ኮምቦልቻ ተዛውሮ ሌላ አንድ ተጨማሪ አውሮፕላን መጨመሩንም የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋሁን መንግስቴ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የግብርና ሚንስትርም የመርጫ መሳሪያ የተገጠመላቸው ተሽከርካሪዎች እንደሚያቀርብ ቃል ገብቶ ነበር ያሉት አቶ ዮሃንስ፤ እስካሁን አለመላኩን ያነሳሉ።
በግብርና ሚንስትር በኩል “አብዛኛው ድጋፍ እየተደረገልን ነው፣ እርሱን ወደየአካባቢዎቹ የማሰራጨት ሥራ እንሰራለን” ያሉት ምክትል ቢሮ ሃላፊው፤ አሁንም ግን አንበጣው መብረር ስለጀመረ ከሰው ኃይል ይልቅ በአውሮፕላን ርጭት መከላከል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ተጨማሪ አውሮፕላን እንዲመደብ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገርን ነውም ብለዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሃብሩ እና የራያ ቆቦ ወረዳ አስተዳዳሪዎች ችግሩ በየቀኑ እየጨመረ መሆኑን ገልጸዋል።
የሚያነሱት ምክንያት ደግሞ የአንበጣው ዋና መፈልፈያው አፋር ክልል በመሆኑ በየወረዳቸው የሰፈረውን የአንበጣ መንጋ መቀነስ ቢቻልም በየጊዜው ከክልሉ እየተፈለፈለ ወደ አማራ ክልል እየገባ መሆኑን ነው።
ርጭቱ የአንበጣ መንጋው የተከሰተበት ቦታ ላይ መካሄድ አለበትም ብለዋል።
ከአሁን በፊት የአንበጣ መንጋው በተከሰተበት አካባቢ የሚኖሩ አፋሮች፤ ኬሚካሉ ለከብቶቻችን ስጋት ይሆናል በሚል ፈቃደኛ እንዳልነበሩ የተናገሩት የራያ ቆቦ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ መንገሻ አሸብር፤ አሁን ግን እነሱም የችግሩ ሰለባ እየሆኑ በመምጣታቸው በቅርቡ ባደረጉት ውይይት ርጭቱ መካሄድ እንዳለበት መስማማታቸውን ይናገራሉ።
ምክትል ቢሮ ኃላፊው አቶ ተስፋሁን፤ እስካሁን ቅድሚያ ተሰጥቶት የነበረው በሰብል ላይ ጉዳት ሲያደርስ የነበረውን አንበጣ መከላከል መሆኑን በማስታወስ፤ በዚህም የተነሳ ወደ አፋር ሂዶ መፈልፈያው ላይ መርጨት አለመቻሉን ገልጸዋል።
አሁን ግን ሁለት አውሮፕላኖች ስለተመደቡ አንደኛውን ወደ አፋር በመላክ አንበጣውን ከመፈልፈያው የማክሰም እና የመከላከል ስራው እንደሚሰራ ገልጸዋል።
