16 ጥቅምት 2020, 12:24 EAT

የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ለሦስተኛ ጊዜ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ በተሳታፊነት በተገኙበት ትናንት ውይይት አካሂደዋል።
በውይይቱ ከተሳተፉት አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በውይይቱ የተነሱ አራት ዋነኛ ጉዳዮች እንደነበሩ ይናገራሉ።
ሕገመንግሥት
የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ውይይት ከተደረጋበቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ መሆኑን ፐሮፌሰር በየነ ይናገራሉ።
አሁን በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት መሻሻል ያለባቸው አንቀጾች ላይ ውይይት ተደርጓል።
መሻሻል ያለባቸው ነጥቦች ላይ ውይይት እንደሚያስፈልግ ሆኖ፤ ሕገ መንግሥቱ ግን ማሻሻያ እንደሚያስፈልገው በአብዛኛው ከስምምነት ተደርሷል።
. ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ቀጣዩ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ እንደሚሆን ተናገሩ
. “ማንም ቢሆን ኢትዮጵያን ለብቻዬ ሰራኋት ሊል አይቻለውም” ጠ/ሚ ዐብይ
መቼ ይሻሻል? በሚለው ላይ ተአማኒነቱ እና ነጻነቱ የተረጋገጠ ምርጫ ከተከናወነ በኋላ በሕጉ መሠረት እንዲሻሻል ተስማምተናል ይላሉ።
የፖለቲካ ፓርቲዎች አደረጃጀት
ሁለተኛው በስፋት ውይይት የተካሄደበት ጉዳይ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች አደረጃጀት ምን ይመስላል? የሚለው መሆኑን ፕሮፌሰር በየነ ይናገራሉ።
የፓርቲዎች አደረጃጀት ምን ይመስላል? ወደፊት የፖለቲካ ፓርቲዎች አደረጃጀት ምን መምሰል አለበት? በሚለው ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል።
በአንድ ክልል ውስጥ ተወስነው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመሳሳይ ግብ ካላቸው በአንድ ቢደራጁ የሚል ሐሳብ መሰንዘሩን ፕሮፌሰር በየነ ይናገራሉ።
ፖለቲካዊ ዓላማ ሳይኖራቸው በአንድ ብሔር ላይ የሚደርስን ጭቆና ለማስቆም ወይም የብሔሩ ማንነት እንዲታወቅ ለማድረግ የተደራጁ ፖለቲካ ፓርቲዎች ስለመኖራቸውም በትናንቱ ስበሰባ ላይ ተነስቷል።
መሰል ፓርቲዎችም የፖለቲካ ዓላማ ይዘው መደራጀት ይኖርባቸዋል በሚል ሐሳብ ተሰንዝሯል።
ግጭት
ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ጠቅላይ ሚንስትሩ በተሳተፉበት ውይይት ሌላው የተነሳው ጉዳይ በኢትዮጵያ በተለያዩ ስፍራዎች እየተስተዋለ ስላለው ግጭት ነው።
የግጭቶቹ ምንክያቶች ምንድናቸው? በሚለው ላይ ውይይት መካሄዱን ፕሮፌሰር በየነ ይናገራሉ። በአመዛኙ ለግጭቶቹ ዋነኛው ምክንያት የመልካም አስተዳደር እጦት እና የሕግ የበላይነት አለመከበር ናቸው የሚሉ ምክንያቶች መነሳታቸውን ያክላሉ።
በአገር ደረጃ ያለው አለመግባባት ምንድነው? መፍትሄ ሊሰጣቸው የሚችለው አለመግባባቶች የትኞቹ ናቸው? መፈታት የማይችሉትስ የትኞቹ ናቸው? የሚሉት ጉዳዮች መለየት አለባቸው የሚል ሐሳብም መነሳቱን ፕሮፌሰሩ ይናገራሉ።
ምርጫ
ምርጫ የውይይቱ አንዱ ርዕስ ነበር። ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ በኢትዮጵያ የተደረጉ ምርጫዎች ዲሞክራሲያዊ አለመሆናቸው ተነስቷል።
ወደፊት የሚካሄደው ምርጫ መቼ መካሄድ አለበት? እንዴት ነው የሚካሄደው? የሚለው ላይ ውይይት መካሄዱንም ፕሮፌሰር በየነ ጠቁመዋል።
በአገሪቱ ሰላም ሳይረጋገጥ እና ብሔራዊ መግባባት ላይ ሳይደርስ ምርጫ ማካሄድ አስቸጋሪ ነው የሚል ሐሳብም መነሳቱን ፕሮፌሰር ይናገራሉ።
. ምርጫው መካሄድ ይችላል ስለመባሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ምን ይላሉ?
አንዳንድ አካላት በሥልጣን ላይ ያለው የአገሪቱ አስተዳደር ሕጋዊ አይደለም እያሉ ስለሆነ ይህ ደግሞ የጸጥታ ችግር ሊፈጥር ስለሚችል ምርጫ መካሄዱ የግድ ነው ያሉ ተሳታፊዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል።
በውይይቱ ከተሳተፉት አብዛኛዎቹ ምርጫው መካሄድ አለበት የሚል አቋም ማንጸባረቃቸውን ፕሮፌሰር በየነ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ በበኩላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት ቀጥሎ በመካሄዱ ደስተኛ መሆናቸውን በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ገልፈዋል።
“እነዚህ ውይይቶች የፖለቲካ ፓርቲዎች በቅርበት አብረው እንዲሠሩ፣ ለወቅታዊ ጉዳዮች የጋራ መፍትሔ እንዲያበጁ፣ እንዲሁም ለሀገራችን እና ለሕዝባችን የሚጠቅም የዕድገት እና የብልጽግና የጋራ ራእይን እንዲያዘጋጁ ለማስቻል ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው” ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ።

በትናንቱ ውይይት ከተሳተፉት መካከል ሌላኛው ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በበኩላቸው በትናንቱ ውይይት የተለያዩ ሐሳቦች ተነሱ እንጂ መቋጫ አላገኙም ይላሉ።
“መንግሥት ይህን አድርግ። ተቃዋሚዎች ደግሞ ይህን አድርጉ የሚል ነገር የለውም። ዝም ብሎ ሐሳብ ማቅረብ ብቻ ነበር” ብለዋል።
መንግሥት በእነዚህ ውይይቶች የሚነሱ ሐሳቦች አገራዊ ጠቀሜታ አላቸው ብሎ የሚያምን ከሆነ እና በቁርጠኝነት የሚሄደበት ከሆነ መልካም ውጤት ይኖረዋል። ይህ ካልሆነ ግን ጊዜ ማቃጠል እንጂ ሌላ ትርጉም የላቸውም” ብለዋል።
“ከምርጫ በፊት አገራዊ መግባባት ያስፈልጋል”
ፕሮፌሰር መረራ ምርጫ 3 ነገሮች ያሳካል ይላሉ። እነዚህም ሰላም፣ መልካም አስተዳደር እና የአገር እድገት ናቸው።
ምርጫ ታዲያ እንዲህ አይነት ውጤቶችን ይዞ እንዲመጣ በቅድሚያ ከምርጫው በፊት አገራዊ መግባባት መድረስ አንዱ ቅድመ ሁኔታ ነው ይላሉ።
በመንግሥት እና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ትክክለኛ ምርጫ ለማካሄድ መተማመን አለ? ምርጫውን የሚያስፈጽመው ቦርድ ገለልተኛ ነው? የሚሉት ጥያቄዎች ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው ይናገራሉ።
“እኛ ምርጫ ቦርድ ላይ ጥርጣሬ አለን እንላለን። መንግሥት ደግሞ ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ነው ይላል። በዚህ ላይ አልተግባባንም” ይላሉ።
በአሁኑ ሰዓት የሁሉንም ፍላጎት የሚያሟላ ትክክለኛ ምርጫ ማካሄድ ይቻላል? በሚለው ላይ መግባባት አለብን የሚሉት ፕሮፌሰር መረራ፤ “ይህ ሐሳብ በትናንቱ የውይይት መድረክ ላይ ቢነሳም መንግሥት ግን ‘ይህን መርጫ በዚም በዚያም አድርጌ አልፈዋለሁ’ የሚል አቋም የያዘ ይመስላል” ይላሉ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና።