16 ጥቅምት 2020, 16:55 EAT

ጭምብል ያጠለቀች ሴትዮ

የዓለም ጤና ድርጅት ሁለተኛው ዙር የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለአፍሪካ በእጅጉ አስጊና ከባድ ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቋል። ድርጅቱ አክሎም ወረርሽኙ በተለይ ለአፍሪካ ኢኮኖሚ አስጊ እንደሆነ አስታውቋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ይህንን ያለው በርካታ አገራት የእንቅስቀሴ ገደቦችንና ሌሎች የጥንቃቄ እርምጃዎችን ማላላት መጀመራቸውን ተከትሎ የቫይረሱ ስርጭት እንደገና ማንሰራራት በመጀመሩ እንደሆነ ተጠቁሟል።

የአፍሪካ አገራት ኢኮኖሚያቸውን ለማነቃቃት በማሰብ ወደቀደመው እንቅስቃሴያቸው መመለስ መጀመራቸው ቫይረሱ ከቁጥጥር ውጪ እንዲሆን እድል እንደሚፈጥር ድርጅቱ አስጠንቅቋል።

በርካታ አገራትም በቂ ዝግጅት ሳያደርጉ እንቅስቃሴዎችን እንደገና እያስጀመሩ መሆኑ እንዳሳሰብው ጠቁሟል።

ድርጅቱ አክሎም ነገሮች በዚሁ የሚቀጥሉ ከሆነ የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ እንደአዲስ ተንሰራፍቶ አገራት ተመልሰው ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴ ማገድ ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ አስታውቋል።

አፍሪካ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ካጋጣት የኢኮኖሚ ውድቀት ለማገገም እንዲሁም የጤና ወጪ 1.2 ትሪሊየን ዶላር እንደሚያስፈልጋት ዓለም አቀፉ ገንዘብ ተቋም [አይኤምኤፍ] ማስታወቁ የሚታወስ ነው።

ገንዘቡ ያስፈልጋታል የተባለው ደግሞ በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ነው።

በአፍሪካ በኮሮናቫይረስ የተያዙ እንዲሁም የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከሌሎች አህጉራት ያነሰ ነው፤ ነገር ግን የዓለም ባንክ በወረርሽኙ ሳቢያ ተጨማሪ 43 ሚሊዮን የሚሆኑ አፍሪካዊያን ለከፋ ድህነት የመጋለጥ አደጋ ተጋርጦባቸዋል ብሏል።

በወረርሽኙ ሳቢያ የሥራ እድሎች በመታጠፋቸው እና የቤተሰብ ገቢ በ12 በመቶ በመቀነሱ የደረሰው የኢኮኖሚ ተፅእኖ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአፍሪካ እየታየ የነበረውን ጠንካራ እድገት እየቀለበሰው መሆኑም ተጠቁሟል።

አይኤም ኤፍ የአፍሪካ አገራት ከደረሰባቸው ተፅዕኖ እንዲያገግሙ 26 ቢሊዮን ዶላር የለገሰ ቢሆንም፤ የግል አበዳሪዎች እና በሌሎች አገራት ድጋፍ ቢኖርም፤ አሁንም ግን ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ እጥረት አለ።

የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር የሆኑት ማሺዲሶ ሞዌቲ እንዳሉት አህጉሪቱ የሚገባትን የክትባት ድርሻ እንድታገኝም ከአሁኑ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው።

በአፍሪካ እስካሁን 1.6 ሚሊየን ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ወረርሽኙ አህጉሪቱ ውስጥ መግባቱ ከተሰማባት ዕለት አንስቶ ደግሞ ከ39 ሺ በላይ ሰዎች በዚሁ ቫይረስ ሳቢያ ሕይወታቸው አልፏል።