
እጆቻቸውን ጉንጮቻቸው ላይ አድርገው በሐሳብ ጭልጥ ብለዋል። በመሃል ንቅት ብለው ማሳቸውን እያዩ ‹‹አላህ›› ያውቃል እያሉ ራሳቸውን ያፅናናሉ።
18 October 2020
ያለ ዕድሜያቸው ያስረጃቸው በኑሮ መጎሳቆልና ድህነት መሆኑን ከገጻቸው ለማንበብ አያዳግትም፡፡ የለበሱት ቀሚስ ከአቡጀዲ የተበጀ ሲሆን፣ ከውስጥ ያለውን ክሳታቸውን አልሸሸገላቸውም፡፡ ካሉት እናቶች አንፃር ሲታዩ በኑሮ ድክም እንዳሉ ያስታውቃሉ፡፡ እንደ አካባቢው ወግ፣ ልማድና ባህል አናታቸው ላይ ጣል ያደረጉት ሸክምም ቢሆን እምብዛም ለዓይን የሚገባ አይደለም፡፡ ዓይናቸው በእንባና ድካም ብዛት ስልምልም ብሏል፡፡ እግራቸውና እጃቸው እንደ ጎረቤት እንስት በእንሶስላ የተዋበ ሳይሆን ቀንና ማታ ማሳቸው ውስጥ የበረሃ አንበጣ በማባረር ብዛት ጥቀርሻ መስሏል፡፡ እጆቻቸውን ጉንጮቻቸው ላይ አድርገው በሐሳብ ጭልጥ ብለዋል፡፡ በመሃል ንቅት ብለው ማሳቸውን እያዩ ‹‹አላህ›› ያውቃል እያሉ ራሳቸውን ያፅናናሉ፡፡ ባለቤታቸውን በሞት የተነጠቁት እኚሁ ባልቴት የሰባት ልጆች እናት በመሆናቸው፣ በበረሃ አንበጣ ሰብላቸው በመጠቃቱ አልቅሰው ያመጣላቸው ነገር አለመኖሩን፣ እንዲያውም ከራስ ጋር ንግግር ብቻ ከጀመሩ ቀናት ማስቆጠራቸውን የነገሩን ወ/ሮ መዲና ሞሰማ ይባላሉ፡፡
ወ/ሮ መዲና ሞሰማ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በጅሌ ጡሙጋ ወረዳ፣ ሙጤ ፈጫቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ ባለቤታቸውን በሞት ከተነጠቁ በኋላ አንድ ሔክታር ማሳ ማረስ በእሳቸው ጫንቃ ላይ ከወደቀ ሰነባብቷል፡፡ እንደ ወትሮው ወደ ማሳቸው ዘልቀው ከዘሩት ሰብል፣ እሸት መብላት አልቻሉም፡፡ ዘንድሮ ያለወትሮው አዝመራው እጅግ የሰጠና ያማረ ቢሆንም፣ አላህ አልፈቀደም ይላሉ፡፡
አላህ ቆንጆ ልጅ ሰጥቶ እንደመንሳት ያህል እንደተሰማቸው ለሪፖርተር ያስረዱት ወ/ሮ መዲና፣ በአካባቢው በዓመት አንዴ ዝናብ ጠብቀው ከሚያርሱ አርሶ አደሮች መሆናቸው ደግሞ ይበልጥ ችግሩ ከፍ እንዳደረገውና ልጆቻቸው ዓይናቸው እያየ እንዳያጧቸው መሥጋታቸውን፣ ገና ከመጀመሩ ለሳምንት እንኳን የሚቆይ የምግብ አቅርቦት የሌለው ቤተሰብ እንዳለም ገልጸዋል፡፡
ሌላኛው የሙጤ ፈጫ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ አሊ ሙሳ በማሳው ውስጥ ያለውን የበረሃ አንበጣ ለመከላከል ቢሞክሩም፣ እጅግ አድካሚ በመሆኑ ከቤታቸው ውጪ ተቀምጠው ነው ያገኘናቸው፡፡ ዘንድሮ በዚህ ቀበሌ እጅግ በሚገርምና በሚደንቅ ሁኔታ ፍሬያማ ምርት የታየ ቢሆንም፣ አንበጣው እንዳልነበረ አድርጎታል ይላሉ፡፡
አቶ አሊ፣ ቀን ከሌት መንጋውን ለመከላከል ቢጥሩም ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ ዓይናቸው እያየ የለፉበትን ሰብል እምሽክ አድርጎታል፡፡ ማሽላ ዘርተው ጥሩ ምርት የሚገኝበት ነው ተብሎ የተገመተ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ማሳቸው ሙሉ በሙሉ በአንበጣ መንጋ ወድሟል፡፡
የአራት ልጆች አባት የሆኑት አቶ አሊን ጨምሮ በቀበሌው የነበሩ አርሶ አደሮች በጠቅላላ የዓመት ቀለባችን ጥሩ አፍርቶ የምናገኝበት የነበረ ቢሆንም አላህ እንዳልፈቀደው ተናግረዋል፡፡
ባለፈው ሰኔ የአንበጣ መንጋ በአካባቢው የተከሰተ በመሆኑ ቀኑን ሙሉ ለማባረር ጥረው ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ ማሳውን ጥለው እንደወጡና ምንም ዓይነት የግብርና ሥራ አለመከናወኑን ያስረዱት አቶ አሊ፣ በሕይወት ዘመናቸው እንዲህ ዓይነት መዓት አይተው እንደማያውቁ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ቦሎቄ ሁለት ሔክታር፣ ጤፍ አንድ ሔክታር ተኩል ጨምሮ ሌሎች የእህል ዓይነቶችን የዘሩት በሞዴል አርሶ አደርነት የሚታወቁት አቶ ሃምዛ ገብረ መስቀል አሁን ላይ አይደለም ሊሸለሙበት የዕለት ጉርሳቸውን ሳይቀር የአንበጣ መንጋው እንደነጠቃቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ለፈጣሪ ከዚህ መዓት እንዲታደገን መለመን እንጂ፣ ምንም ተስፋ የለም፤›› ይላሉ፡፡
አምና ከተከሰተው ከፍተኛ ዝናብ እንዲሁ እህል እንደተበላሸባቸው ያስረዱት ሞዴል አርሶ አደሩ፣ ዘንድሮ በተለየ ሁኔታ ምርት እንደሚሰጥ ተስፋ ቢጣልበትም አብዛኛው የገበሬ ማሳ መና መቅረቱን አስረድተዋል፡፡
በአካባቢው ትልቁ ችግር የሆነው የእርሻ ማሳዎች ከመበላታቸው በበለጠ ከፊል አርብቶ አደሮች ከብቶቻቸውን የሚመግቡት የግጦሽ መሬትና ቁጥቋጦ ሳይቀር በመንጋው መውደሙ ከፍተኛ ረሃብ በአካባቢው ሊከሰት ይችላል ብለው መሥጋታቸውን አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል፡፡
አቶ ሃምዛ፣ በ2012 ዓ.ም. በኮንትራት ሦስት ሔክታር ማሾ (ምስር) የዘሩ ቢሆንም በዝናብ ተበላሽቶባቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ በአካባቢው በዓመት አንዴ ብቻ ለሚያርሱ ገበሬዎች ትልቅ ችግር ውስጥ በመሆናቸው በባለሀብቶችና በመንግሥት ሊታገዙ እንደሚገባ አቶ ሃምዛ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አቶ ሃምዛ፣ አምና በከፍተኛ ዝናብ ምክንያት ኪሳራ የገጠማቸው ሲሆን፣ 2013 ዓ.ም. ላይ ደግሞ 87 ሺሕ ብር በላይ ፈሰስ ያደረጉበት የእርሻ ሰብል በአንበጣ መውደሙን ይገልጻሉ፡፡
አቶ አብዱ መሐመድ የሰይድ ጊልዶ ጥሙጋ ወረዳ የግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እንደገለጹት፣ በአጠቃላይ በ2012 እና 2013 ዓ.ም. ምርት ዘመን በሰብል ልማት ሥር ይለማል ተብሎ በተያዘው 12 ሺሕ ሔክታር መሬት ነው፡፡ 22 የገጠርና ሁለት የከተማ ቀበሌዎችን ለማልማት የታለመ ቢሆንም እስካሁን የአንበጣ መንጋው 14 ቀበሌዎችን እንዲሁም የአፋር ክልል አጎራባችን ጨምሮ ሰብሉ በአንበጣ መንጋ መውደሙን ተናግረዋል፡፡
በወረዳው የተሰበሰቡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ 60,500 ሔክታር ውስጥ 26,000 ሔክታር የሚሆነው ሙሉ በሙሉ በአንበጣ መንጋው ተበልቷል፡፡ ቁጥቋጦ፣ ግጦሽና የሰብል መሬት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ የሰብል መሬት 4,600 ሔክታር የወደመ ሲሆን፣ ወደ 2,600 አባወራዎች ተጎጂ ሆነዋል፡፡ በየሰዓቱ አዳዲስ መንጋ በየቀበሌዎቹ አረንጓዴ የተባለ ቅጠል ሳይቀር ድምጥማጡን እያጠፋ ነው፡፡ ወረዳው ወደ ሌሎች አካባቢ እንዳይዛመት ለማስቀረት ቢጥርም ከአቅም በላይ መሆኑን አቶ አብዱ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
ሙጤ ፈጫ ባጪና ወሰን ቁርቁር የተባሉ ቀበሌዎች ላይ እስከ ጥቁሬ ጉርዳ ቀበሌ ጨምሮ በአውሮፕላን፣ በሰው ኃይልና በመኪና የመድኃኒት ርጭት እየተደረገ ቢሆንም ከአቅም በላይ መሆኑም ተገልጿል፡፡
በከፍተኛ ሁኔታ ተጎዳ የተባለው ቀበሌ ከ1,600 ሔክታር በላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን፣ ዝቅተኛው 800 ሔክታር ቢሆንም አብዛኛው ግን በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዳው እንደሚያመዝን የግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
ለአሥራ አምስት ቀናት ያህል የተለያየ ቡድን በመሆን የመከላከል ሥራ መሠራቱን የገለጹት አቶ አብዱ፣ 1,304 ሔክታር ለማዳን መቻሉን ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን መንጋው የዕድገት ደረጃዎች ስላሉት ከሥር ከሥር የሚጨምርበት ሁኔታ እንዳለም ይናገራሉ፡፡ በወረዳው አቅም መከላከል የሚቻለው የአንበጣ ደረጃዎች ደግሞ ‹‹ሆፐር›› ደረጃ ላይ የሚገኘውን ሲሆን፣ ሌሎቹ ግን መቆጣጠር እጅግ አዳጋች መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
ዕድገቱን በጨረሰ አንበጣ ላይ በኬሚካል ርጭት ማድረግ ከባድ በመሆኑ ሌሊት ሲያርፉ ብቻ ካልሆነ የኬሚካል ርጭት ማድረግ አዳጋች መሆኑን የጠቆሙት፡፡
ዘመቻው ጥሩ ቢሆንም በአፋር አንዳንድ ወረዳ የሚገኙ ቀበሌዎች ብዛት ከስምንት በላይ በመሆኑ መድረስ እንዳልተቻለ ያስረዳሉ፡፡
እንደ አካባቢው ነዋሪዎች ገለጻ ከሆነ፣ አፋር ላይ ያለው አንበጣ ሳይበዛ ማኅበረሰቡና መንግሥት ቀደም ተብሎ ሥራ ቢሠራ ላይከሰት ይችል እንደነበርና ቢከሰትም እንኳን መጠኑ አነስተኛ ሊሆን እንደሚችል ይገምታሉ፡፡
ለወደፊቱ የአንበጣ መንጋው ዘሩን አባዝቶ ወደ ሌሎች አካባቢዎችና ሌሎች የእርሻ መሬቶችን መና እንዳያስቀር የሚል ትልቅ ሥጋት ተፈጥሮባቸዋል፡፡
በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን የጅሌ ጡሙጋ ወረዳ አስተዳዳሪ ጀማል ሀሰን መሐሙድ፣ የአንበጣው መንጋ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ከወረዳው 63 ኪሎ ሜትር ተጉዘው፣ አፋር ክልል ውስጥ የመከላከል ሥራ እየተሠራ መቆየቱ ጠቅሰው፣ ነገር ግን መንጋው የሚፈለፈልባቸው ቦታዎች በርካታ በመሆናቸው እየገፋ መምጣቱን፡፡ ከ24 ወረዳዎች በአሥራ ስድስት ቀበሌዎች ማዳረሱንና ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ እየወደሙ ያሉት ከስምንት በላይ መሆናቸውንም አክለው ገልጸዋል፡፡
በሰው ኃይል፣ በባህላዊ መንገድ፣ በመኪና፣ በአውሮፕላን ርጭት ሦስት ጊዜ የተደረገ ቢሆንም፣ እርሻዎችንና የግጦሽ መሬትን ከአንበጣ መንጋ መታደግ አልተቻለም፡፡ በአውሮፕላን የሚደረገው የኬሚካል ርጭት አንበጣው ላይ ጉዳት የሚያደርስ ቢሆንም፣ በወረዳው የኬሚካል ርጭት አድርጎ ወደ ሌላ ቦታ ሲኬድ ሌላ የአንበጣ መንጋ ይመጣል፡፡ አርሶ አደሩ ሌትና ቀን እርሻ ውስጥ አንበጣውን ለማባረር ይጥራል፡፡ የአንበጣ መንጋ እንደ አዲስ የሚተካ በመሆኑ ገበሬውም ሆነ ወረዳው የአቅሙን ቢጥርም እጅግ አስቸጋሪ እንዲሆነባቸው ይናገራሉ፡፡
አቶ ጀማል ለሪፖርተር እንደገለጹት መንጋው ቢጠፋም እንኳን የሰሜን ሸዋ አካባቢ እንዳይጎዳ ተፈርቷል፡፡ ኤፍራታ፣ ቀወት ወረዳና ሸዋ ሮቢት ከጃሌ ጡሙጋ ወረዳ ጋር እየሠሩ የሚገኙ ሲሆን፣ ሸዋ ሮቢት አካባቢ የአውሮፕላን ማረፊያ ተሠርቶ የኬሚካል ርጭት ካልተከናወነ በሁለቱ ዞኖች የቀረውን ሰብል ማትረፍ ከባድ መሆኑን አቶ ጀማል ገልጸዋል፡፡
በአቶ ጀማል አገላለጽ፣ አርሶ አደር ሆኖ ምንም ዓይነት የእንስሳት መኖ የሌለው ሰው በይበልጥ የሚጎዳ በመሆኑ ሊታገዝ ይገባል፡፡ አርሶ አደሮች ሰብል ከተሰበሰበ በኋላ ሳይሆን፣ እሸቷን እየተመገበ እስከሚደርስ የሚጠብቅ በመሆኑ ችግሩ ከአሁን እንደሚጀምር መታወቅ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር በትኩረት ሊሠራ ይገባው የነበረው በ2012 ዓ.ም. የተከሰተው አንበጣ እንደገና ተፈልፍሎ ዳግመኛ ችግር እንዳይፈጠር ማድረግ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡
የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አስተባባሪው አቶ መሐመድ ያሲን ከአንድ ወር በፊት የአንበጣ መከላከል ሥራ መሠራቱን ያወሳሉ፡፡ በሁሉም ወረዳዎች የተቀናጀ ሥራ ለመሥራት ከ60 እና ከዚያ በላይ ኪሎ ሜትሮችን በማቋረጥ አፋር ክልል ድረስ ተሄዶ የመከላከል ሥራ ተሠርቷል፡፡ ነገር ግን ግጭቶች ባሉባቸው ቦታዎች ላይ ባለመሠራቱ፣ ችግር መከሰቱን ይገልጻሉ፡፡
አቶ መሐመድ እንደገለጹት፣ በአምስት ወረዳዎችና ከ56 በላይ ቀበሌዎች ላይ ከፍተኛ ውድመት ደርሷል፡፡ ከ17 ሺሕ በላይ ሔክታር በዞኑ የሰብል ዘር በመንጋው ተበልቷል፡፡ 21,000 በላይ ቤተሰብ በዚህ ችግር ውስጥ ይገኛል፡፡ አካባቢው በሰብል ብቻ የሚተዳደር ባለመሆኑ፣ የግጦሽ መሬት ላይም በተመሳሳይ መልኩ የደረሰው ጉዳት እጅግ አሳሳቢ አድርጎታል፡፡
የአንበጣ መንጋ ያደረሰው የጉዳት መጠንና እየተወሰደ ያለው ዕርምጃ
የአንበጣ መንጋ የተከሰተባቸው በባቲ፣ ደጭጨፍ፣ አርጡጣ ፋርሲ፣ ቾሌ ጥሙጋ፣ ዳዌ ሃረዋ ወረዳዎች በሚገኙ ከ110 በላይ ወረዳዎች ላይ 56ቱ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በ19,772 ሔክታር ላይ ያረፈ ሰብል ጉዳት የደረሰበት ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 14,400 ሔክታር ሙሉ ለሙሉ መውደሙን የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ እብሬ ከበደ ዓሊ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ለከብት ግጦሽ የሚውል 11,977 ሔክታር መሬት አንበጣ ስለበላው በቀጥታ የእንስሳት ሀብት ላይ ትልቅ ችግር እንዳለው ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
በአጠቃላይ 1,700 ቁጥቋጦ፣ 74,000 አትክልትና ፍራፍሬ በአጠቃላይ ሰባት ሔክታር ሰብል ጉዳት ደርሶበታል፡፡ በዞኑ ከሚገኙ ወረዳዎች ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ደግሞ የባቲ ወረዳ ሲሆን ከ26 ቀበሌዎች ውስጥ 20ዎቹ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አጋጥሟቸዋል፡፡
26,000 አባወራና እማወራዎች በአጠቃላይ 151,291 የጉዳቱ ሰለባ መሆናቸውንና እነዚህን ቤተሰቦች አስቸኳይ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የጠቆሙት ኃላፊው፣ ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የጤና ሴክተሩን እንደፈተሸው ሁሉ የአንበጣም መንጋ መከሰትም የግብርና ሴክተሩን እየፈተነው በመሆኑ ዞር ተብሎ መቃኘት ግዴታ መሆኑን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
አክለውም ለእነዚህ አርሶ አደሮች ከሁለት እስከ ሦስት ወር ጊዜ የሚደርሱ ሰብሎችን እንዲያመርቱ በማገዝ ችግሩን ለመቅረፍ እየተሠራ መሆኑን አክለዋል፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተደረገ ያለውን እንቅስቅሴ አስመልክተው በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ለማ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ዓለም አቀፍ ተዛማች ችግር የሆነውን የበረሃ አንበጣ ለመከላከል ከዓለም አቀፍና ከምሥራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ መከላከያ ድርጅት የሚሰጡ ትንበያዎችንና መረጃዎችን መሠረት በማድረግ ከበፊትም ጀምሮ ሲሠራበት የቆየ ነው፡፡
በተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት የሚሰጡ መረጃዎችንና ትንበያዎችን መሠረት በማድረግ ዕርምጃዎች ሲወሰዱ የቆዩና አሁንም እየተወሰዱ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ኢሳያስ፣ መንግሥት ምንም እንዳልሠራ ተደርጎ በአንዳንድ ማኅበራዊ ትስስር ገጾች የሚነገረው ከእውነታው የራቀ መሆኑንም አክለዋል፡፡
ክረምት ላይ በታችኛው የኢትዮጵያ ክፍል በተለይ በደቡብ ኮንሶ፣ ቦረና ታችኛው ሱማሌ አካባቢዎች ላይ ትንበያውና መረጃው ስለነበር በኢትዮጵያ በኩል በተሠራውና በኬንያ በኩል ጥሩ ቁጥጥር ስለተደረገ የበረሃ አንበጣውን ለመቆጣጠር መቻሉንም ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ ኢሳያስ፣ አሁን ላይ ደግሞ በሶማሌ፣ በድሬዳዋ፣ በምሥራቅና ምዕራብ ሐረርጌ፣ ምሥራቅ አማራ፣ አፋርና ደቡባዊ ትግራይን ይዞ ለተከሰተው የበረሃ አንበጣ ትንበያው ከተነገረበት ጊዜ አንስቶ፣ ተከሰተ በተባለበት ቦታ ሁሉ የመከላከልና ወደሌላ እንዳይዛመት የማድረግ ሥራው መከናወኑን ሆኖም ከውጭ የሚገባው እስካልቆመ ድረስ አንበጣ መኖሩ እንደማይቀር፣ ሚኒስቴሩ የክልል ግብርና ቢሮዎች እስከታችኛው መዋቅር ባሉ አሠራሮች ላይ አሁን ሰብል በደረሰበት ወቅት የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ መንጋ እየተከላከሉና እየተቆጣጠሩ ነው፡፡
ሚኒስቴሩ በሰመራና በኮምቦልቻ አየር ማረፊያ አውሮፕላን መድቦ እየሠራ እንደነበርና አንዱ አማራ አንዱ ሶማሌ ውስጥ መከስከሳቸው ጫና እንደፈጠረ፣ ሆኖም በኢትዮጵያ የበረሃ አንበጣው የተከሰተው መንግሥት ሳያውቅና ምንም ሳይሠራ እንደሆነ ተደርጎ የሚነገረው ስህተት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በኮሮና ወረርሽኝ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጊዜ የሚኒስቴሩ ባለሙያዎችም አፋርና አማራ ውስጥ እንደነበሩ አሁንም ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ የሙያቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡
‹‹አንበጣ በየትኛውም ቦታ ሊከሰት የሚችል የፖለቲካ ፓርቲና ብሔር የሌለው፣ የመንግሥትም ሆነ ሌሎች ተቋማት የሚያሰማሩት እንስሳ አይደለም፤›› ያሉት አቶ ኢሳያስ፣ ኅብረተሰቡን ከማደናገር ይልቅ የግብርና ባለሙያዎች ስለበረሃ አንበጣ ባህሪያትም ሆነ የመከላከል ዘዴዎች የሚመክሩትን በመስማት ችግሩን በጋራ ለመቅረፍ መሥራት ይመረጣል ብለዋል፡፡
አንበጣ የጊዜ ዑደትን ተከትሎ ረዥም ጊዜ የሚጓዝ፣ በመንጋ የሚሄድና በመንጋ ሲመጣ ከፍተኛ ውድመት የሚያደርስ፣ በኢትዮጵያ የተከሰተበት ጊዜ ደግሞ ሰብል የደረሰበትና ያለበት በመሆኑ ኅብረተሰቡንም መንግሥትንም ይጎዳል ያሉት አቶ ኢሳያስ፣ ነገር ግን ግብርና ሚኒስቴር ሦስት አውሮፕላኖች ተከራይቶ እየሠራ መሆኑን ሆኖም በየክልሉ የሚደረገውን ቁጥጥር ኅብረተሰቡ ማገዝ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
የአንበጣን መንጋ መግደል እንጂ በዘመቻ በማባረር ለውጥ እንደማይመጣ፣ ከአንዱ ሲባረር ወደአንዱ እንደሚሄድ የገለጹት አቶ ኢሳያስ፣ ይህ በመሆኑም በአውሮፕላን የማይመችበት ቦታ በመኪና ርጭት እንደሚደረግ ለዚህም ከተጠሪ ተቋማት ተጨማሪ መኪኖች እየተሰማሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል ያለውን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ፣ አፋር የእንስሳት ሚኒስትር ዴኤታ እየመሩትም ይገኛሉ፡፡ ከተጠሪ ተቋማት ተጨማሪ መኪኖች እየሰማሩ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፡፡ ከውጭ አገር ተጨማሪ ሒሊኮብተርና አውሮፕላን ለማስገባት እየተሞከረና አንድ የገባች አውሮፕላንም መርጫ እየተገጠመላት መሆኑን፣ ተጠግኖ በቅርቡ ወደ ሥራ የሚገባም እንዳለ አስረድተዋል፡፡
የበረሃ አንበጣው በተከሰተባቸው ቦታዎች የደረሰው ጉዳት ከሰብል ሰብል፣ ከቦታ ቦታ ስለሚለያይ ይህ ተጠንቶ በአጠቃላይ ይፋ ይደረጋል ያሉት አቶ ኢሳያስ፣ ሰብሉ የሚያገለግለው ለሚቀጥለው ዓመት መሆኑን በማስታወስም፣ የተጎዱ አካባቢዎች ላይ ጥናት ተደርጎ አስፈላጊው ምላሽ እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
አንበጣን ለመቆጣጠር የራሱ ሒደትና ደረጃ ያለው በመሆኑ ይህንን ተከትለን እየሠራን ነው በማለትም የበረሃ አንበጣን የፖለቲካ መጠቀሚያ ማድረግ ለማንም አይጠቅምም ብለዋል፡፡
ዓምና 143 ሺሕ ሔክታር በበረሃ አንበጣ የተጎዳ መሆኑንና ከአሁኑ ጋር ሲነፃፀር የመቆጣጠር አቅም አነስተኛ እንደሆነ፣ ዘንድሮም መንግሥት ለችግሩ ቀዳሚ ትኩረት ሰጥቶና በጀት ይዞ የበረሃ አንበጣውን ለመከላከል እየተሠራ መሆኑን ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡

