October 21, 2020 – Konjit Sitotaw 


በደቡብ ክልል ቤንች ሸኮ ዞን ጉራ ፈርዳ ወረዳ “ማንነታቸው ያልታወቀ” የተባሉ ታጣቂዎች 12 ሰዎች ገደሉ–የወረዳው ባለስልጣናት እንዳስታወቁት ታጣቂዎቹ ግድያውን ባለፈው ሰኞ ምሽት የፈጸሙት በወረዳው ሹቢ በተባለ የገጠር ቀበሌ ውስጥ ነው።–

ታጣቂዎቹ በቀበሌው በሚገኙ መንደሮች በድንገት በከፈቱት የተኩስ እሩምታ አንድ ህጻንን ጨምሮ 12 ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች 5 ሰዎች መቁሰላቸውን ነው የጉራ ፈርዳ ወረዳ ፖሊስ ዋና አዛዥ ኢንስፔክተር በቀለ በየነ ዛሬ ለዶይቸ ቬለ (DW) በስልክ ያረጋገጡት ።–“ጥቃቱ የደረሰባቸው በሙሉ አርሶ አደሮች ናቸው ። ባልታሰበ ሰዓት ምሽት በየቤታቸው ተቀምጠው ባሉበት ወቅት ነው የተገደሉት ። አሁን የወረዳ ፣ የክልል እና የፌዴራል የፀጥታ ሃላፊዎችና የሰራዊቱ አባላት በስፍራው ደርሰን አካባቢውን እያረጋጋን እንገኛለን። በትናንትናው እለትም የሟቾቹ አስክሬን እንዲቀበር ፣ የቆሰሉትም ወደ ህክምና እንዲወሰዱ አድርገናል ” ብለዋል።–አካባቢው እስከአሁን ሰላማዊ ፣ የተረጋጋና የልማት ቀጠና ነበር የሚሉት የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፍቅሬ አማን በበኩላቸው በአሁኑወቅት ጥቃት አድራሾቹን ለመያዝ በዞኑ የኮማንድ ፖስት አማካኝነት የተቀናጀ የጸጥታ ሀይል ክትትል በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል።በተጨማሪም በሁኔታው ተደናግጠው ወደ አጎራባች ቀበሌያት የሸሹ ነዋሪዎችን የማረጋጋት ፣ወደ ቦታቸው የመመልስና ሰብእዊ ድጋፎችን የማቅረብ ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውንም ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።–ጥቃቱ ተፈጽሟል በተባለበት በዚሁ የቤንች ሸኮ ዞን በስራ ጉብኝት ላይ የነበሩት የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳ “በደረሰው ጉዳት ጥልቅ ሀዘን ተሰምቶኛል ፣ የድርጊቱን ፈጻሚዎችን ይዘን ለህግ ለማቅረብ እንሰራለን” ሲሉ የክልሉ መንግስት ንብረት ለሆነው የደቡብ ቴሌቪዥን መናገራቸውን ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ ከሐዋሳ ዘግቧል።–በቤንች ሸኮ ዞን መስተዳድር ስር የሚገኘው የጉራ ፈርዳ ወረዳው ተሰባጥረው ከሚገኙት የቤንች ፣ የሸኮ እና የሜኒት ጎሳዎች በተጨማሪ ከአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በመንደር ማሰባሰብ የመጡ ማህበረሰቦችም ይኖሩበታል።–የቀድሞው የቤንች ማጂ ዞን መስተዳድር ምዕራብ ኦሞ እና ቤንች ሸኮ ዞን በሚል ለሁለት ሲከፈል የጉራ ፈርዳ ወረዳ በየትኛው የዞን መስተዳድር ይጠቃለል የሚለው ጥያቄ የአካባቢው ፖለቲከኞችን ሲያነታርክ መክረሙ ይታወሳል ።–የአሁኑ ጥቃት ከወረዳው የአከላለል ጥያቄ ጋር የተያያዘ መሆን አለመሆኑ እስከአሁን የታወቀ ነገር ባይኖርም የዞን ባለስልጣናት ግን ጥቃት አድራሾቹ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚሰሩ ቡድኖች ናቸው እያሉ ይገኛሉ።