21 ጥቅምት 2020, 07:38 EAT

አንበጣ

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በኢትዮጵያ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ ጥቃት ያደረሰው በ240 ወረዳዎች መሆኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት ሰኞ እለት በተካሄደው 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ ልዩ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ የተከሰተባቸው አካባቢዎች አፋር፣ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይ እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር መሆናቸውን ገልፀዋል።

በእነዚህ የአንበጣ መንጋ ጥቃት የደረሰባቸው አካባቢዎች በጥቅሉ 240 ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ በእነዚህ ወረዳዎች ስር ከሚገኙ ቀበሌዎች መካከል ደግሞ በ705 ቀበሌዎች ላይ ብቻ አንበጣው ጥቃት ማድረሱን ገልፀዋል።

በእነዚህ አካባቢዎች በድምሩ 4 ሚሊየን ሄክታር ታርሷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከዚህም መካከል ጥቃት የደረሰበት 420ሺህ ሔክታር ገደማ መሆኑን ተናግረዋል።

ከውጪ ኬሚካል የሚረጩ አውሮፕላኖችን እና ድሮኖችን [ሰው አልባ አውሮፕላን] ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሂደቱ ግን አልጋ ባልጋ አለመሆኑን አመልክተዋል።

የበረሃ አንበጣ መቼ ተከሰተ?

ከ25 ዓመታት ወዲህ የከፋ ነው የተባለለት የበረሃ አንበጣ ለወራት ኢትዮጵያን ጨምሮ በምሥራቅ አፍሪካ ያሉ አገራት ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው።

ከባለፈው ዓመት ጀምሮ አስካሁን በተከታታይ ለተከሰተው የአንበጣ መንጋ ምክንያቱ እንደ አውሮፓዊያኑ በ2018 እና 2019 ያጋጠመው ከባድ ነፋስና ዝናብ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ እንዳመለከተው ከሁለት ዓመት በፊት በደቡባዊ የአረብ ልሳነ ምድር ላይ የነበረው እርጥብና አመቺ የአየር ሁኔታ የአንበጣው ሦስት ትውልድ ሳይታወቅ እንዲራባ እድል ፈጥሮ በአካባቢው አገራት ላይ የሚታየውን የአንበጣ መንጋ ወረራ አስከትሏል።

የግብርና ሚኒስቴር የበረሃ አንበጣ በኢትዮጵያ ከተከሰተበት ከሰኔ 2011 ዓ.ም ጀምሮ የመቆጣጠር ስራ ሲሰራ እንደነበር ገልጾ በመስከረም ወር 2013 ዓ.ም ከየመንና ከሱማሌ ላንድ መነሻውን በማድረግ ወደ ኢትዮጵያ እንደገባ ይፋ ያደረገው መረጃ ያሳያል።

የአንበጣ ወረርሽኙ መከላከል ሥራ በህብረተሰቡ ተሳትፎ እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር እና የክልል ባለሙያዎችም ሰፊ-ርብርብ እያደረጉ እንደሚገኙ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የግብርና ቢሮ ኃላፊዎች ይናገራሉ።

የግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመሆን የአሰሳ ሄሊኮፕተሮችን፣ የኬሚካል መርጫ አውሮፕላኖችን፣ ተሸከርካሪ ላይ የሚገጠምና በሰዉ የሚያዝ ሞተራይዝድ መርጫዎችን በማቅረብ እንዲሁም ኬሚካል፣ የኬሚካል መከላከያ አልባሳትንና የመስክ ተሸከርካሪዎችን ማቅረቡን ገልጿል።

ሆኖም ግን የአዉሮፕላን እጥረት መኖሩ ክስተቱን በሚመጥን ሁኔታ ለመከላከል ዋና ተግዳሮት መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚንስቴሩ ይህን ችግር ለመፍታትና የርጭት ስራውን በውጤታማ ሁኔታ ለማከናወን እንደአገር በተደረገ ጥረት በተወሰኑ ቀናት ውስጥ ተጨማሪ ኬሚካል የሚረጩ አውሮፕላኖች ከውጭ በማስመጣት የመቆጣጠር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡

አሁን ባለው ትንበያ መሰረት የተባዩ ክስተት ለተወሰነ ጊዜ ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚችልና የአንበጣን መንጋውን ለመከላከል እስከ 10 አውሮፕላኖችና 150 የመስክ ተሽከርካሪ እንደሚያስፈልግ እና ይህንም ለማሟላት ከተለያዩ ተቋማትና ሀገሮች ጋር መንግስት እየተነጋገረ እንደሚገኝ የገለፀው ደግሞ ግብርና ሚኒስትር ነው።

ኦሮሚያ

በኦሮሚያ ክልል የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ በሁለቱ የሐረርጌ ዞኖችና በሰሜንሸዋ ዞን መከሰቱን የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

የከልሉ የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ወረርሽኙ በሰሜን ሸዋ የተከሰተው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው።

ከባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ጀምሮ የአፋር ክልልን በሚያዋስነው የሰሜን ሸዋ ፈንታሌ ወረዳ ውስጥ መታየት ጀምሯል ብለዋል።

እንደ ግብርና ቢሮ ኃላፊው ባለፉት ሶስት ወራት በ850ሺህ ሄክታር ላይ በተደረገ ዳሰሳ 288 ሺህ በሚሆን ሄክታር በአንበጣ መጠቃቱን ታውቋል።

ይህንኑ ጉዳት ለመቆጣጠር የኬሚካል ርጭት እየተደረገ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዳይሬክቶር ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ኢሳያስ ለማ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በተመሳሳዩም አቶ ዳባ በሁለቱ የሐረርጌ ዞኖች በአንበጣው ወረርሽኙ ከተጎዱ ሰብሎች መካከል ማሽላ አንደኛው መሆኑን ተናግረዋል።

ወረርሽኙን ለመከላከል ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት አቶ ዳባ ከእነዚህም መካከል በማህበረሰብ ተሳትፎ የሚከናወነው መከላከል አንዱ መሆኑን ገልፀዋል።

ከመከላከል እርምጃዎቹም መካከል ማህበረሰቡን ከማሳሰብ በተጨማሪ ጭስ ማጨስና ድምጽ ማሰማት አንዱ መሆን አቶ ዳባ ተናግረዋል።

ከዚያ በተጨማሪ የኬሚካል ርጭት እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።

የኬሚካል ርጭቱን ደግሞ በእጅ ማሽን፣ በመኪና እና ላይ በመጫንና በአውሮፕላን በድሮን በመታገዝ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።

የመሳሪያ እንዲሁም የአውሮፕላን አቅርቦት ችግር መኖሩን የሚገልፁት እኚህ ኃላፊ ነገር ግን በመንግሥት ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።\

የአውሮፕላን ችግሩ እየተፈታ ነው ያሉት ኃላፊው “ሂሊኮፕተር አለን፣ መድሃኒት ለመርጨት የሚውሉ ትንንሽ አውሮፕላኖችም አሉን እንዲሁም ሰው አልባ አውሮፕላን ለመጠቀም እየሞከርን ነው” ብለዋል።

የጸረ አንበጣ መድኃኒት ለመርጨት ያሉ አማራጮች

ከግብርና ሚኒስትር፣ ከኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ተውጣጥተው ችግሩ ወደ በሚታይባቸው ስፍራዎች በመውረድ የመከላከል ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ኃላፊው አስታውቀዋል።

አማራ

በአማራ ክልል ከሰሜን ሸዋ እስከ ሰሜን ወሎ ድረስ የአንበጣ መንጋው ከፍተኛ ጉዳት ካስተናገደባቸው ወረዳዎች አንዱ የሃብሩ ወረዳ ነው። በወረዳው ሰባት ቀበሌዎች ሙሉ በሙሉ በአንበጣ መንጋው ወድመዋል።

አርሶ አደር አሊ ሰዒድ ከእነዚህ ቀበሌዎች አንዷ በሆነችው ጥልፌ ቀበሌ ይኖራሉ። ከአራት እርሻዎቻቸው መካከል የ13 ጥማድ [3 ሄክታር በላይ] መሬት ወድሞባቸዋል። አንድ እርሻ ማትረፋቸውን የሚናገሩት አቶ አሊ፣ “የተረፈው እርሻ የአንድ ወር ቀለብ እንኳን የሚሆን አይደለም፣ ዓመት ሙሉ የደከምንበት እንኳን ለእኛ ለከብቶቻችንም የሚሆን እንዳይተርፍ አድርጎ አውድሞብናል” በማለት አንበጣው ያደረሰባቸውን ጉዳት ይገልጻሉ።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋሁን መንግሥቴ የአንበጣ መንጋው በክልሉ 4 ዞኖች፣ 18 ወረዳዎች በ136 ቀበሌዎች መከሰቱን ለቢቢሲ ተናግረዋል። በእነዚህ አካባቢዎች በአጠቃላይ 328 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ መውረሩን የተናገሩት አቶ ተስፋሁን ግማሽ የሚሆነውን መሬት የአውሮፕላን ርጭትን ጨምሮ በተለያዩ የመከላከያ ዘዴዎች የመከላከል ሥራ ተሠርቶበታል ሲሉ ይናገራሉ።

የአንበጣ መንጋው 87 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ በሰብልና በእንስሳት መኖ ላይ ጉዳት አድርሷል የሚሉት አቶ ተስፋሁን፣ ከእነዚህም መካከል 30 ሺህ 500 ሄክታር የሚሆነው የሰብል ምርት መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

የአንበጣ መንጋው ባደረሰው ከፍተኛ ውድመት የተጎዱ አርሶ አደሮችን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ድጋፍ ለማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ምክትል ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል።

ትግራይ

አርሶ አደር ንጉስ ሲሳይ በትግራይ ክልል የራያ ጨርጨር ወረዳ ኗሪ ናቸው። እኚህ የ50 አመት አርሶ አደር ሰባት የቤተሰቦች አባላትን ያስተዳድራሉ። ሁሉም ልጆቻቸው ወንዶች ስለሆኑ፤ በእድሜ ተለቅ ያሉት ሁለት ወንድ ልጆቻቸው ይዘው ባለፈው አመት የመጋቢት ወር ላይ ማሳቸውን ሲንከባከቡና ለምርት ሲያበጃጁ መክረማቸው ይናገራሉ።

ባለቤታቸውም፤ የተዘራው እህል አረም እንዳያጠፋው ከስር ከስር ማገዛቸው የሚገልጹት አርሶ አደር ንጉስ፤ ከመጋቢት እስከ ግንቦት 2012 ባሉት ወራት ውስጥ በ250 ሄክታር መሬት ላይ ጤፍ፣ በቆሎና ሽምብራን ዘርተው እንደነበር ይናገራሉ።

“ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ዝናብ ስለነበረ፣ ከአንድ ሄክታር እስከ 80 ኩንታል በቆሎ፣ 40 ኩንታል የሚደርስ ደግሞ ጤፍ አገኛለሁ የሚል ተስፋ ነበረኝ። አሁን ይሄ ሁሉ በአንበጣ መንጋ ተበልቶ ወድሟል” ይላሉ። በዚህ ወቅት፣ በቴክኖሎጂ ታግዘው በመስራታቸው ትልቅ ተስፋ የጣሉበት የምርት ዘመን ድንገት በአንበጣ መንጋ ሲወረር ቢቻል ከውድመት ለማትረፍ ባህላዊ በሆኑ መንገዶች በወጣቶችና ህብረተሰቡ እገዛ መከላከል ቢሞክሩም ውጤታማ እንዳልሆነ አርሶ አደሩ ገልጸዋል።

“በቅርቡ ለሦስተኛ ጊዜ የመጣው የአንበጣ መንጋ ከአቅማችን በላይ ስለነበረ መከላከል አልቻልንም። እህሉን ጨርሶ በሰው አይን ላይ ያርፍ ነበር። በዚህ ወቅት ሴቶች እጅግ ተጨንቀዋል። ሚስቶቻችን ደህና የነበረው ሰውነታቸው ከስቶ በተስፋ መቁረጥ ጠቁረዋል፤ ምን እንበላለን? ወዴት እንሄዳለን? እያሉ ነው” ብለዋል።