የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

የምርጫ ስርአትን ብሔራዊ ምርጫ በሚደረግበት ተመሳሳይ ወቅት መቀየር ያለው ተጽእኖ

October 21, 2020 

መግቢያ

ይህ የውይይት መነሻ ጽሁፍ በኢትዮጵያ የምርጫ ስርአትን ለመቀየር በሚደረግ ሂደት ወቅት መታየት የሚገባቸውን የቴክኒክ

ጉዳዮችን የሚዳስስ ሲሆን ትኩረት የምርጫ ማስፈጸም ሂደት ላይ ምን አይነት ጉዳዮች ከግምት ውስጥ መግባት አለባቸው
የሚለው ላይ ነው፡፡ ይህ የውይይት ሃሳብ በሚዘጋጅበት ወቅት በምርጫ ስርአቱ ላይ ሊኖሩ የሚችሉ ለውጦች ምን ሊሆኑ
እንደሚችሉ ግልጽ መረጃ የለም፡፡ ነገር ግን የተመጣጣኝ ውክልና ስርአትን በመጨመር የምርጫ ስርአቱን ወደ የቅይጥ ስርአት
የመቀየር ይህም ማለት አሁን ከሚገኘው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስቱ አንቀጽ 54 ከተቀመጠው በአብላጫ ድምጽ የሚገኙ
መቀመጫዎች በተጨማሪ በተመጣጣኝ ውክልና ተጨማሪ መቀመጫዎችን የመጨመር አሰራር ሊሆን ይችላል ተብሎ
ይገመታል፡፡ የምርጫ ስርአት ለውጡ ይህ አይነት ከሆነ የሚመለከተው የተወካዮች ምክር ቤትን ብቻ ይሆናል ማለት ነው፡
፡ የዚህ ፅሁፍ ትኩረት ይህ አይነት ለውጦች የምርጫ ኦፕሬሽን ላይ የሚኖራቸውን ተጽእኖ ላይ ብቻ ይሆናል፡፡ የምርጫ
ስርአት መቀየር ራሱን የቻለ የፓለቲካ ሂደት በመሆኑ ይህ መነሻ ጽሁፍ በእንደዛ ያሉ ጉዳዮች ላይ አቋም ለመያዝ ሳይሆን
በቴክኒካል የምርጫ ሂደት ላይ የሚኖረውን ተጽእኖ ለማሳየት ብቻ የተዘጋጀ ነው፡፡
አጠቃላይ ዋና ዋና ጉዳዮች
የምርጫ ስርአትን ምርጫ በሚካሄድበት አመት/ ወቅት መቀየር ለመራጩ፣ ምርጫ አስፈጻሚው እና ለፓለቲካ ፓርቲዎች
ትልቅ ተግዳሮት ሊሆን ይችላል፡፡ የምርጫ ስርአትን መቀየር የምርጫ ስርአቱ የሚተዳደርባቸውን ህጎች በሰፊው መቀየርን
ይጠይቃል፡፡ በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ የምርጫ ኦፕሬሽን ዲዛይንን መከለስ፣ የፓለቲካ ፓርቲዎችን አደረጃጀት ክለሳን
እንዲሁም ስለምርጫ ስርአቱ ሰፊ ትምህርት የመስጠት ዘመቻንም ጭምር ሊያካትት ይችላል፡፡ አዲስ የምርጫ ስርአት
በሚታሰብበት ወቅት ስርአቱ በተለይ በህዳጣን ማህበረሰብ ክፍሎች፣ እጅግ በጣም ገጠራማ በሆኑ ቦታዎች፣ ዝቅተኛ የማንበብ
እና መጻፍ ችሎታ ባላቸው ማህበረሰብ ክፍሎች እንዲሁም በሴቶች ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ተጽእኖ መገምገም አስፈላጊ
ነው፣ ምክንያቱም ከአዲሱ ስርአት ጋር በቀላሉ ለመዋሃድ አስቸጋሪ በመሆኑ በአዲሱ የምርጫ ስርአት ውስጥ ውክልናቸው
አነስተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ በተጨማሪም የሚደረገው ለውጥ ከታሰበው በተለየ የአገር አቀፍ በጀት አሰራር እና አቅም ላይ
ከፍተኛ ተጽእኖ ሊፈጥር ይችላል፡፡ በስተመጨረሻም የምርጫ ስርአትን መቀየር የምርጫ አፈጻጸምን የተወሳሰበ ሂደት
ስለሚያደርገው ምርጫን ማከናወን በተለመደው ሊወስድ ከሚችለው ጊዜ በላይ እንዲወስድ ሊያደርገው ይችላል፡፡ በመሆኑም
ምርጫ በሚደረግበት አመት የሚኖር የምርጫ ስርአት ለውጥ ከታለመለት አላማ በተለየ የምርጫ ሂደቱ ጥራት እና ተአማኒነት
ላይ ተጽእኖ ሊፈጥር ይችላል፡፡
የምርጫ ስርአት ለውጥ እና የኢትዮጵያ ሁኔታ
ይህ ትንታኔ ኢትዮጵያ ውስጥ የምርጫ ስርአት ለውጥ በአሁኑ 6ተኛው አገራዊ ምርጫ ጋር በተመሳሳይ ጊዜ የሚካሄድ ከሆነ
ምርጫ የማስፈጸም ስራው ከግምት ውስጥ ማስገባት ያለበትን ስድስት ዋና ዋና ጉዳዮች/እንድምታዎች ይዳስሳል፡፡
በህግ እና በተቋማዊ አሰራር ላይ የሚኖረው እንድምታ

  1. ህገመንግስታዊ ማሻሻያ – በ.ኢፌ.ዲ.ሪ ህገመንግስት አንቀጽ 54(2) እና 54(3) የተቀመጠውን የምርጫ ስርአት መቀየር
    በህገመንግስቱ አንቀጽ 104 እና አንቀጽ 105 በተቀመጠው መሰረት መከናወን ይኖርበታል፡፡ ይህ ማለት የምርጫ
    ስርአቱን መቀየር ከፍተኛ ጊዜ፣ ውይይት/ምክክር እና ሃብት የሚወስደውን የህገመንግስት የማሻሻል ስራን ይጠይቃል
    ማለት ነው፡፡ ከነዚህ አጠቃላይ ሂደቶች በተጨማሪ የህገመንግስቱ አንቀጽ 104 ማሻሻያ ለሚመለከታቸው አካላት
    ሊቀርብ እንደሚገባ ይደነግጋል፡፡ የምርጫ ስርአት ማሻሻያ ደግሞ መላ አገሪቷን የሚመለከት በመሆኑ ከተለያዩ
    የማህበረሰብ አካላት ጋር ውይይት መደረግ እንደሚገባ ይኸው የህገ መንግስቱ አንቀጽ ይደነግጋል፡፡
    ስለዚህ አገራዊ ምርጫን በታለመለት በ2013 አመት ለማካሄድ ከታሰበ የምርጫ ስርአት ለውጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ
    መከናወን የሚገባው ሲሆን ለውጡም የምርጫ ኦፕሬሽን ላይ ከፍተኛ ለውጥ የማያስገድድ መሆን ይኖርበታል፡፡
  2. የህግ ማሻሻያ – የህገ መንግስታዊ ማሻሻያው በማስከተል የምርጫ ህጉ እና አሰራሩ ማሻሻያ ሊደረግበት ይገባል፡፡
    ለምሳሌ አሁን ያለው የምርጫ ስርአት እነዳለ ሆነ የተመጣጣኝ ውክልና ስርአት ከተጨመረበት በምርጫ ኦፕሬሽን
    ወቅት ተጨማሪ የድምጽ መስጫ ወረቀት፣ የተለየ የድምጽ ቆጠራ እና ድመራ ስርአት መዘርጋት የሚጠይቅ ይሆናል፡
    ፡ ይህም ለስህተት ለመዳረግ እንዲሁም የምርጫ ውጤት ይፋ ማድረጊያ ጊዜን የማራዘም ተጽእኖ ሊኖረው ይችላል፡
    ፡ የምርጫ፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች እና የምርጫ ስነምግባር አዋጅ 1162 እንዲሁም የብሔራዊ ምርጫ ቦርዱ ማቋቋሚያ
    አዋጅ 1133 በ2011 ዓ.ም ሲወጡ የምርጫ ኦፕሬሽን ላይ ብዙ ለውጦችን ማካተታቸው ይታወሳል፡፡
  3. ተቋማዊ ማሻሻያ – ከህጎች በተጨማሪ የሚቀየረው የምርጫ ስርአት ለውጥ የቦርዱን ውስጣዊ አደረጃጀት የመቀየር
    እድል ሊኖረው ይችላል፡፡ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አዲስ በወጡት እና ከላይ ተጠቀሱት ህጎች መሰረት ተአማኒ እና
    አለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ ምርጫ ለማከናወን ራሱን እያደራጀ ሲሆን የምርጫ ስርአት ለውጥ በቦርዱ የውስጥ
    አሰራር እና መዋቅር ለውጥ ላይ አዲስ ማስተካከያ ለማድረግ ሊያስገድደው ይችላል፡፡
  4. የምርጫ ክልሎች አከላል- የምርጫ ስርአትን መቀየር ከምርጫ ክልሎች አከላል ጋር ሊኖረው የሚችለው ግንኙነት
    እና ተጽእኖ ግልጽ አይደለም፡፡ የምርጫ ክልሎችን የሚነካ የምርጫ ስርአት ለውጥ ከተከናወነ የመጪውን ምርጫ
    የጊዜ ሰሌዳ ላይ ተጽእኖ ሊኖረው ይችላል፡፡
    በምርጫ ጊዜ ሰሌዳው ላይ ያለው እንድምታ
    በምርጫ ስርዓቱ ለውጥ በምርጫ ጊዜ ሰሌዳው ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ በጣም አሳሳቢ ቢሆንም፣ ሊኖሩ የሚችሉትን
    ትክክለኛ ለውጦች መሰረት በማድረግ ተጽእኖውን መቀነስ ሊቻል ይችላል፣ ነገር ግን መዘግየት እንዲፈጠር ሊያደርግም
    ይችላል፡፡
    ከላይ እንደተጠቀሰው፣ በኢትዮጵያ የምርጫ ስርአቱ መቀየር በ1987/ 1995 እ.ኤ.አ/ ዓ.ም. የወጣውን የኢትዮጵያ ህገመንግስት ላይ ለውጥ የሚጠይቅ እና፣ በዚህም የተነሳ ሰፊ ውይይቶች እና ምክክሮችን (አንቀጽ 104) የሚፈልግ እንዲሁም
    ይህን ተከትሎ የምርጫ ህጎችን ለውጥም የሚፈልግ ነው፡፡
    ለጥሩ አላማ ታልሞም ቢሆን ህገ መንግስቱን ለማሻሻል የሚደረጉ ሂደቶች ሊገመቱ የማይችሉ ሲሆኑ ምርጫን ለማድረግ
    የሚያስችል አስተማማኝ የህግ ማእቀፍ ያለመኖር ደግሞ ከፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመነጋገር የምርጫውን ትክክለኛ የጊዜ
    ሰሌዳ ለመወሰን የሚስቸግር እና የምርጫ ዝግጅት ስራዎችንም መስራት ለመጀመር አስቸጋሪ የሚያደርግ ነው፡፡
    በተጨማሪም ሌላው አሳሳቢው ጉዳይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ ቁጥር 16 (2013) በያዝነው አመት 2013 ዓ.ም
    (እስከ ነሀሴ ወር 2013 ዓ.ም ድረስ) ምርጫ እንዲከናወን የወሰነውን ውሳኔ የተመለከተ ነው፡፡ ህገመንግስት የማሻሻል ሂደት
    የሚጀመር ከሆነ፣ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳው በውሳኔው ላይ ከተቀመጠው የጊዜ ገደብ የሚያልፍ ሲሆን፣ የምርጫ ቅድመ
    ዝግጅቶችን በአፋጣኝ መቀጠል ካልተቻለ ቦርዱ ከላይ የተጠቀሰውን የምክር ቤቱን ውሳኔ እንዳያከብር ሊያደርገው ይችላል፡
    ፡ በዚህም መሰረት አዲስ ውሳኔ መወሰን ሊያስፈልግ ይችላል፡፡
    ሲጠቃለል፣ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማንኛውም በህገ- መንግስቱ እና በምርጫ ህጎች እንዲሁም ሌሎች ህጎች ላይ በሚደረጉ
    ውሳኔዎች እና ማሻሻዎች ላይ የተወሰነ ነው፡፡ አስተማማኝ ባልሆነ ጊዜ ሰሌዳ ላይ በመመርኮዝ የምርጫ ዝግጅቶች ማድረግ
    አይመከርም፡፡ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳው ላይ መወያያት እና መወሰን የሚቻለው፣ እንዲሁም ዝግጅቶችን በአግባቡ መጀመር
    የሚቻለው እነዚህ ሂደቶች ከተጠናቀቁ በኋላ ብቻ ይሆናል፡፡
    የምርጫው በጀት ላይ የሚያሳድረው አንድምታ፡
    የህገ መንግስትና የምርጫ አዋጆች ለውጥ ጋር በተያያዘ ህዝብን የማማከር ግዴታዎችን በተገቢው ለመወጣት፣ የታቀደ
    የተወሰነ በጀት ያስፈልጋል። ይሁን እንጂ፣ ይሄ ጉዳይ ከዚህ የውይይት መነሻ ሀሳብ ትኩረት ውጭ ሲሆን የምርጫ ስርአት
    ለውጥ በምርጫ አስተዳደሩ ላይ የሚኖረው የበጀት እንድምታ ለማየት ይሞክራል፡፡
    በምርጫ ወቅት/ አመት ዉስጥ በህገ መንግስቱና የምርጫ አዋጆች ላይ የሚደረግ ለውጥ እንዲሁ ለመጨረሻዉ የምርጫ
    ሂደትና አስተዳደር በተመደበው በጀት ላይ ከፍተኛ አደጋዎች እና ተጽኖዎች ይኖረዋል። ዋና ዋና አደጋዎቹና/ ተጽእኖዎቹም
    የሚከተሉት ናቸው፣
  5. በቋሚ ወይም ወጪ ከተደረጉ በኋላ መመለስ በማይችሉ ወጪዎች ላይ የመክሰር አደጋ፡ ይህ ክስተት የሚያጋጥመው
    ምርጫ ቦርድ፣ ማንኛውም የተሻሻለ የሕግ ማዕቀፍ ግልጽ ከመደረጉ አስቀድሞ አሁን ባለው ህግ መሠረት ዝግጅቶችን
    የመቀጠል ግዴታውን እየተወጣ ሲቀጥል ሲሆን፣ በማንኛውም ለውጥ ተነሳ ኢንቬስት ባደረጋቸው ሃብትና ንብረቶች ላይ
    ከፍተኛ ኪሳራ ሊያጋጥመው ይችላል። የሀብት መባከን ወይንም ኪሳራው ፤ለምሳሌ የምርጫ ቁሳቁሶችን ከመግዛት እና
    ከማከማቸት፣ወይም የምርጫ ሂደትን በአግባቡ ለማስተናገድ ሲባል ተቋማዊ አቅምን ከመገንባት ጋር ሊያያዝ ይችላል፡፡
  6. ለውጦችን ከማስተዋወቅ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ተጨማሪ የበጀት ፍላጎቶች አንድምታ፡ የሕገ-መንግስቱ ድንጋጌዎችና
    የምርጫ አዋጆች ከታወቁ በኋላ፣ ከተሻሻለው የምርጫ ሥርዓት ጋር ተያይዞ ተጨማሪና ከፍተኛ የአሠራር ችግሮች
    ሊያጋጥሙ ይችላሉ። ለውጦቹን ለማስተናገድም ተጨማሪ ሀብቶች የሚያስፈልግበት ሁኔታ ሊከሰት ይችላል።
    በአሠራር ሂደቶች ላይ የሚኖሩት አንድምታዎች፡
    በህገ መንግስትና የምርጫ አዋጆች ላይ የሚደረግ ለውጥ በምርጫ አስተዳደር ስርአቱ ላይ ተጽዕኖ ያስከትላል፡፡
  7. ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚደረግ ምክክር፡ በምርጫ ሥርዓቱ ላይ ለውጥ ከተደረገ በኋላ ማንኛውንም የመመሪያ ወይም
    አሠራር ክለሳን ለማሳወቅ ሲባል ከባለድርሻ አካላት ጋር ተጨማሪ ምክክሮች ሊያስፈልጉ ይችላሉ።
  8. የእጩ ምዝገባ፡ የተመጣጠነ የውክልና ስርአትን ማስተዋወቅ፣ አሁን ካለው ሂደት በተለየ መልኩ የፖለቲካ ፓርቲዎች
    ምዝገባ በተመለከተ ተጨማሪ መስፈርትን መጠቀም ሊጠይቅ ይችላል። ይህም የምርጫ ቦርድ ተጨማሪ ቁሳቁሶችን
    ዲዛይን እንዲያደርግና እንዲገዛ፤ እንዲሁም ለፓርዎችና ለእጩዎች ምዝገባ የታሰበውን የቴክኖሎጂ (አይሲቲ) ትግበራ
    ማስተካከል ሊያስፈልገው ይችላል። በእጩዎች የመለያ ምልክት አመራረጥ ሂደት ላይ የሚከሰቱ ለውጦችንም ሊያካትት
    ይችላል፡፡
  9. የፖለቲካ ዘመቻ፡ ለምርጫ ዘመቻ የሚሆን የፋይናንስ አመዳደብ ዙሪያ ያሉ ሕጎች እና አሰራሮች ግምገማና ማሻሻያ
    ሊጠይቁ ይችላሉ፡፡
  10. የምርጫ ቁሳቁሶች፡ በመላ አገሪቱ ሁለት ውድድሮችን ጎን ለጎን ማካሄድ የሚያስፈልግ ከሆነ፣ እንደ ድምጽ መስጫ ሳጥን
    (በተለይም የክልል መንግስታትም የተመጣጣኝ ውክልና መስፈርቶችን ለማካተት ስርዓታቸውን የሚያስተካክሉ ከሆነ)፣
    የድምጽ መስጫ ወረቀቶች፣ የዉጤት ፎርሞችና ማሸጊያዎች የመሳሰሉ ተጨማሪ ቁሳቁሶች ሊያስፈልጉ ይችላሉ።
  11. የዉጤት አያያዝ ስርአት፡ የተጨማሪ ውድድር አይነት መኖር የውጤት ድምር አሰራሩ ይበልጥ ውስብስብና ጊዜ የሚወስድ
    እንዲሆን ያደርገዋል፤ በተለይም የክልል መንግስታትም በስርዓቶቻቸውን ላይ ማሻሻያ የሚያደርጉ ከሆነ። ውጤቶችን
    በእጅ ሰርቶ በሰንጠረዥ ለማቅረብ የሚዘረጋው ሥርዓትም በጣም የተወሳሰበና ጊዜ የሚወስድ፣ ለስህተት የተጋለጠ
    እንዲሁም ውድ ይሆናል። ይህንን ችግር ለመቀነስ ፣ ቢያንስ በኤሌክትሮኒክስ የታገዘ የውጤት የአሰራር ሂደት መዘርጋት
    ሲኖርበት፤ የውጤት ገለጻ የጊዜ ሰሌዳውም በምርጫ አዋጁ ዉስጥ መስተካከል አለበት።
  12. የቅሬታ/ ግጭት አፈታት፡ ከተመጣጣኝ ውክልና ምርጫ ውድድር (proportional race) አስተዳደር ጋር ተያይዞ የሚነሱ
    ችግሮችንና አለመግባባቶችን በተመጣጣኝ መልኩ ማስተናገድ መቻሉን ለማረጋገጥ፣ አሁን ያለው የምርጫ አለመግባባት
    አፈታት ሥርዓት ማሻሻያ ሊያስፈልገው ይችላል።
  13. ስልጠና፡ አዲስ ውድድርን ወደ ምርጫ ስርዓቱ ማስተዋወቅ የሚያስፈልግ ከሆነ፣ ተጨማሪ የሥልጠና ቁሳቁሶችን
    ማዘጋጀትና፣ የምርጫ አስፈፃሚዎችን እና የምርጫ ጣቢያ ሰራተኞችን ከአዲሱ የምርጫ ሂደት መስፈርቶች ጋር
    ለማስተዋወቅ የተራዘመ ሥልጠና ሊያስፈልግ ይችላል።
  14. የመራጮች ትምህርት፡ የስርዓቱ ለውጦችንና መብቶቻቸውን በተመለከተ ለማህበረሰቡ ሰፊ መረጃ ለማቅረብ፣ በተለይም
    ለችግር ተጋላጭ ለሆኑና ለተገለሉ የማህበረሰብ ክፍሎች የተለየ ትኩረት በመስጠት፣ የመራጮች ትምህርት እና የመረጃ
    አቀራረብ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል፡፡

ማጠቃለያ
በታቀደው የምርጫ ስርዓት ለውጥ ላይ ያለው የመረጃ ውስንነት ለውጡ የሚያመጣውን ቴክኒካዊ አንድምታዎች በተመለከተ
ዝርዝር ትንታኔ ለመስጠት እንዳይቻል ይገድባሉ፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ የመጀመሪያው ትንታኔ እንደሚያመለክተው በምርጫ
ዓመት ውስጥ የሚደረጉ የተወሰኑ ለውጦች በአጠቃላይ የምርጫ ሂደቱ ተዓማኒነት እና ተቀባይነት፣ አካታችነት እና ወቅታዊነት
ላይ ከፍተኛ አደጋን ይጥላሉ፡፡
የምርጫ የጊዜ ሰሌዳን መወሰን የሚቻለው ለውጦቹ ተጠናቀው አዲሱ ህገ-መንግስት ማሻሻያ እና የምርጫ አዋጅ ከፀደቀ በኋላ
ብቻ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዲሱ ህገ መንግስታዊ ማሻሻያ ላይ እና የተሻሻለውን የምርጫ አዋጅ ላይ
በመመርኮዝ መመሪያዎችን እና የአፈፃፀም እቅዶቹን መገምገም የሚችለው ከዚያ በኋላ ብቻ ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ
ምርጫ ቦርድ በሚያወጣው የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ አስፈላጊውን ለውጥ ለማድረግ የሚወስደው ጊዜንም ማካተት ይኖርበታል፡፡
የምርጫ ስርዓቱ መለወጥ ጉልህ የሆኑ ተጨማሪ የአሰራር ችግሮችን የማይፈጥር ቢሆን እንኳን ምርጫው በህዝብ ተወካዮች
ምክር ቤት በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ እንዲካሄድ ለማስቻል እንዲሁም ምርጫ ቦርድ የምርጫ እንቅስቃሴዎችን አተገባበር
ለመቀጠል እንዲችል በጊዜ ውሳኔ ላይ መድረስ አስፈላጊ ነው፡፡ በመጨረሻም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሊኖር
የሚችለው የምርጫ ስርአት ለውጥ የሚጠናቀቅበት ቁርጥ ጊዜን ማወቅ ይኖርበታል፡፡ እንዲሁም በሂደቱ ላይ መሳተፍ እና
የሚመጡት ለውጦች ከምርጫ ኦፕሬሽን እና የጊዜ ሰሌዳ አንጻር ምን ሊመስሉ እንደሚችሉ እና ተጽእኖአቸውን ለመገምገም
ስለሂደቱ በቂ እውቀት ሊኖረው ይገባል፡