ክልልም ራስገዝም ሆነን ብዙ አመታት አይተነዋል ፡፡ ለህዝብ ጥቅም ፍትህ ና ዕኩልነት ያመጣ አደረጃጀት አላየንም ፡፡ ከተወሰኑ ሰወች ጥቅም በስተቀር ፡፡ እኛ /ኢዜማ / ህዝብ የሚበጀውን ያውቃል እንላለን !! እያንዳንድ ዜጋ በድምፅ ይወስን ፡ እኛ እናውቅልሃለን አንበል ፡፡ – ናትናኤል ፈለቀ የኢዜማ ህዝብ ግንኙነት
ክልል/ራስ ገዝ መሆን ከምን ያድናል?
–
አንድ አካባቢ ክልል በመሆኑ ሌሎች በሕገ ወጥ መንገድ ሊጭኑበት ያሰቡትን የበላይነት መከላከል ይችላል?በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶቻቸው እና ጥቅሞቻቸው ይጠበቁላቸዋል?
–
ኢትዮጵያ ውስጥ የፌደራል ሥርዓት ሕገ መንግሥታዊ እውቅና ማግኘቱን ተከትሎ የተፈጠሩት ክልሎች በተግባር ክልል መሆናቸው ያረጋገጠላቸው መብት እና ተተቃሚነት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ክልል ሆነው ተደራጅተው የፌደራል መንግሥቱን በበላይነት ይዞ የነበረው ሕወሃት የፈለገውን ነገር ከማድረግ መከላከል የሚችሉበት አቅም አልፈጠረላቸውም። በክልሎች ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን ጥቅም እና መብት ማስከበር የሚችሉበት ተቋም እና አሠራር አልሰጣቸውም። ክልሎቹ ፍላጎታቸውን ለማስከበር እና ከሌላ ቦታ የሚመጣን ስጋት ለመከላከል ያደራጁት ልዩ ኃይል በክልሎቹ ውስጥ አምባገነናዊ ሥርዓቱን መጠበቂያ፣ «መጤ» ተደርገው የሚቆጠሩ ዜጎች ላይ ሰቆቃ ፈጻሚ እንዲሁም ለሀገራዊ አንድነት እና መግባባት አደጋ ደቃኝ ነው የሆኑት።
–
1. በዜጎች እና በመንግሥት እንዲሁም በዜጎች መካከል የሚደረግ መስተጋብር ከሁሉ በፊት አስቀድሞ የሚያስፈልገው ሥርዓት ነው። የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ በጋራ የምንወስንባቸውን ጉዳዮች ምን ዓይነት ሂደት ተከትለን፣ ምን ዓይነት ጉዳዮችን ከግምት አስገብተን እንወስን የሚለው ላይ መስማማት እና በዛ መሰረት ተግባር ላይ ማዋል ያስፈልጋል። የሕግ የበላይነት ካልተረጋገጠ ሌላ የሚተገበሩ ጉዳዮች በሙሉ ለሁሉም እኩል እንደሚሠሩ ማረጋገጥ አይቻልም። ጉልበተኞች ደካሞች ላይ የሚፈልጉትን እንደማይጭኑ ማረጋገጫ የለም።
ኃላፊነት የሚሰማን እና ከምር መወሰድ የምንፈልግ ከሆነ አዲስ አበባ ክልል/ራስ ገዝ ትሁን የሚለው ክርክር ላይ ከመድረሳችን በፊት የሕግ የበላይነት ተረጋግጧል ወይ? ክልል/ራስ ገዝ እንድትሆን ለመወሰን የምንሄድበት በሀገር ደረጃ ሊተገበር የሚችል የሚያስማማን የአሠራር ሥርዓት አለ ወይ? የሚለውን መጠየቅ እና አጥጋቢ መልስ ማግኘት ግዴታ ነው! አዲስ አበባ ክልል/ራስ ገዝ ሆና ተዋቅራ በቅርብ ጊዜ ታሪካችን እንደምናውቀው በሕግ ከተገደበ ሥልጣን በላይ እየተጠቀሙ የከተማዋ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ሚገቡ ጉልበተኞችን ማስቆም የሚያስችሉ የከተማዋ እና የፌደራል መንግሥት ተቋማት እና ሥርዓት ከሌለ ክልል መሆኗ ዋጋ የለውም።
–
2. የአንድ ማኅበረሰብ የምኖርበት አካባቢ ክልል/ራስ ገዝ ይሁን-አይሁን ወይንም በምን መልክ ይደራጅ የሚል የረጅም ጊዜ ውጤት ያለው ጉዳይ ላይ ይቅርና ከተማውን በሚመለከት በማናቸውም ጉዳዮች የመወሰን የራስን በራስ የማስተዳደር መብቱ ሊረጋገጥ ይገባል። የከተማው ነዋሪ ወክለውት የሚወስኑትን ሰዎች ነፃ እና ፍትሃዊ በሆነ ምርጫ መርጦ ሥልጣን መስጠት አለበት።
ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን ማረጋገጥ ያልቻለ ማኅበረሰብ ክልል/ራስ ገዝ ልሁን ብሎ ቢጮህ ምንም ትርፍ የለውም። ጥቅሜን ያስጠብቁልኛል፣ መብቴን ያስከብሩልኛል የሚላቸውን ሰዎች መርጦ ሥልጣን መስጠት እና ሳይፈልግ ሲቀር ሥልጣን መንሳት የማይችል ማኅበረሰብ በክልልነት/በራስ ገዝነት መደራጀት ቢፈልግ እንኳን ያንን ፍላጎቱን ማሟላት የሚችልበት ሥልጣን የለውም ማለት ነው። ፍላጎታችን የማኅበረሰቡን ፍላጎት ማሟላት ከሆነ ያንን ማሟላት የሚችልበት ሥርዓት መኖሩን ማረጋገጥ ቅድሚያ ልንሰጠው ይገባል። ይህ ሥርዓት ሳይረጋገጥ በፊት እንደዚህ ዓይነት ትልልቅ ጉዳዮችን ማጯጯህ ድጋፍ ለማሰባሰብ ይጠቅም ይሆናል፤ ነገር ግን ከተግባራዊነቱ አንጻር አሁን አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን መቼም የማይቻልበተን ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል።
–
3. የኢዜማ ፕሮግራም ውስጥ በግልፅ እንደተቀመጠው አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት መሻሻል አለበት። መሻሻል ካለባቸው ነገሮች ዋነኛው ደግሞ የፌደራል ሥርዓቱ የተዋቀረበትን መንገድ ነው። የፌደራል ሥርዓቱ የተዋቀረበትን መንገድ የሕዝብ ሥነ-ልቦና፣ ቋንቋ፣ ባሕል እና አሰፋፈርን፤ የመልከዓምድራዊ አቀማመጥ፤ የአስተዳደር እና ልማት ፍትሃዊነትን እንዲሁም ለአጠቃላይ ሀገራዊ መግባባት በሚያግዝ መልኩ እንደገና መሻሻል እንዳለበት በግልፅ አስቀምጠናል።
–
የሕገ መንግሥት ማሻሻያ በሕዝብ በእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የተመረጡ ተወካዮች ካገኘን በኋላ በየአካባቢው ማኅበረሰቡ በሰፊው ተወያይቶበት እና በተቻለ አቅም የሁሉም ኢትዮጵያዊያን አመለካከት የሚንፀባረቅበት አሳታፊ ሂደት አልፎ መከናወን አለበት። የዛኔ በመላው ሀገራችን ሁሉም ዜጎች እኩል መብት እና ዕድል የሚያገኙበት በመተባበር መንፈስ የተገነቡ ፌደራላዊ የአስተዳደር አካባቢዎች ይኖሩናል። ይህን እውን ማድረግ ረጅም ጊዜ፣ ስክነት እና አስተዋይነትን ይጠይቃል። ላለብን ሀገራዊ ችግር በሰፊው አስበን የማንመለስበትን ሀገራዊ መፍትሄ መስጠት እንጂ በተናጥል መፍትሄ ለመስጠት መግፋት ውጤት አይኖረውም ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ አደጋም ይዞብን ይመጣል።
*****
ኢዜማ የሚሠራውን እና የሚሳተፍበትን ነገር በሙሉ ከምር የሚወስድ፤ ለሕዝብ የሚጠቅሙ ጉዳዮችን መቼ እና በምን ሁኔታ ቢተገበሩ ይሻላል የሚለውን አስቦ የሚሠራ፣ ነገሮችን ከረጅም ጊዜ ጉዳት እና ጥቅማቸው አመዛዝኖ የሚጓዝ ድርጅት ነው።
–
ትላንት በነበረው ውይይት ተገኝተን ከላይ ያሉትን ሀሳቦች ለማንፀባረቅ ሞክረናል። አዘጋጆቹ መድረኩ የአዲስ አበባን ክልልነት/ራስ ገዝ መሆንን ደግፈው አሁን ተግባራዊ እንዲሆን የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች መድረክ እንደሆነ አስረግጠው ሲነግሩን ሁሉም የተሰበሰቡት ፓርቲዎች ሕገ መንግሥቱ መሻሻል አለበት ብለው ስለሚያምኑ እና ምርጫው ነፃ እና ፍትሃዊ እነዲሆን በሚሉ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ፍላጎት እንዳለን ነገር ግን አሁን የተዘጋጀው መድረክ ላይ መቀጠል እንደማንችል በአክብሮት አቋማችንን አሳውቀናል።
–
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ መድረክ ከፍቶ ፓርቲዎችን ለውይይት መጋበዙ የሚያስመሰግን ነው። ነገር ግን ባለፈው የነበረው ውይይትን ተከትሎ የተዘገበበት መንገድ ልክ አይደልም የሚል አስተያየት ሰጥተን የነበረ ቢሆንም አሁንም ተመሳሳይ የውይይት መንፈሱን የሚጎዱ እና በቀናነት የሚሳተፉ ፓርቲዎችን እምነት ሊሸረሽሩ የሚችል ተግባር ተደግሟል። አሁንም ቢሆን እነዚህ ችግሮች ታርመው በምንስማማባቸው ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ ውይይት እንደሚኖረን ተስፋ አደርጋለሁ። በዚህ አጋጣሚ በመድረኩ የነበሩ የፓርቲ ተወካዮች ሀሳባችንን አክብረው ለማስረዳት እና ለማቀራረብ ያደረጉትን ጥረት ለማድነቅ እፈልጋለሁ።
–
ናትናኤል ፈለቀ የኢዜማ ህዝብ ግንኙነት
