October 24, 2020

ሲራራ

በአገራችን በየቀኑ ስለ ግጭትና ስለ ዜጎች መፈናቀል መስማት የተለመደ ነገር ሆኗል፡፡ ዛሬ በአንድ አካባቢ ግጭት ይቀሰቀሳል፤ ዜጎች ይገደላሉ፤ ንብረታቸው ይወድማል፤ ይፈናቀላሉ፡፡ በማግስቱ ኅብረተሰብ ተወያየ ይባልና ሰላም እንደወረደ ይገለጻል፡፡ ግጭቱ የአካባቢውን ሕዝብ የማይወክልና የማይገልጽ የፀረ ሰላም ኀይሎች ሴራ ነው ይባላል፡፡ የተወሰኑ አመራሮች ተጠያቂ ስለመሆናቸውም ይዘገባል፡፡ ይሁን እንጅ ሕዝብ ተወያየ፣ ሰላም ወረደ በተባለ ማግስት ሌላ ግጭትና የዜጎች ሞት ይከሰታል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የግጭትና የዜጎች መፈናቀል አዙሪት ለብዙ ኢትዮጵያዊያን ግራ የሚያጋባ የራስ ምታት ነው፡

፡–

የኢትዮጵያ ችግሮች እንዲሁ በነጠላ ጉዳዮችና ክስተቶች ላይ የተመሠረቱ አይደሉም፡፡ መፍትሔውም በነጠላ ጉዳዮችና ከስተቶች ላይ በሚደረግ ጥረት የሚመጣ ሊሆን አይችልም፡፡ የአገራችን ችግሮች መዋቅራዊ (structural) ናቸው፡፡ ከታሪክና ከፖለቲካ ትርክት ጋር፣ ከፌዴራላዊ አወቃቀሩና ከሕገ መንግሥቱ ጋር፣ አገሪቱ ከምትገኝተበት ድህነትና ኋላቀርነት ጋር፣ ከፓርቲ ፖለቲካው ጋር፣ በአገሪቱ ከሰፈነው መረን የለቀቀ ሙስናና ዘረፋ ወዘተ… ጋር የተያያዙ መዋቅራዊ ችግሮች ናቸው፡፡ ስለሆነም በአገራችን ግጭቱና የዜጎች ሞትና መፈናቀል ቀጣይ ነው፡፡ ከገባንበት አረንቋ ለመውጣት ከሁሉ በፊት ችግራችን መዋቅራዊ መሆኑን መገንዘብና መቀበል፤ ከዚያ ለጥቆ በጥበብና በዕውቀት ላይ ተመሥርቶ ዘላቂ መፍትሔ መፈለግ ወሳኝ ነው፡፡

የዘውግና ሃይማኖት ብዝሃነት ባለባቸው አገሮች (ማኅበረሰቦች) ግጭት ሊበረክት እንደሚችል ይታመናል፡፡ ሆኖም የዓለም ታሪክ እንደሚያሳየን የዘውግም ይሁን የሃይማኖት ብዝሃነት በራሱ የግጭት ምንጭ ሊሆን አይችልም፡፡ ከፍ ያለ ልዩነትና ክፍፍል ያለባቸው ማኅበረሰቦች ግጭትን ለማስወገድ እና ጠንካራ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመገንባት የሚያስችላቸው የሕግ የበላይነት የነገሠበት እና የዜጎችና የቡድኖች መብት የተከበረበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ብቻ ሳይሆን በተቻለ መጠን ሁሉንም ዜጎችና ቡድኖች በፍትሐዊነት ተጠቃሚ የሚያደርግ የኢኮኖሚ ልማት ነው፡፡

እንዲህ ዓይነት ከፍ ያለ ልዩነትና ክፍፍል ባለባቸው አገሮች ውስጥ ድህነት እና የገቢና የሀብት አለመመጣጠን ሲኖር ችግሮች በቀላሉ ወደ ግጭትና ወደ እርስ በርስ ጦርነት የማምራት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ሥራ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ በዚህች አገር ከፖለቲካው በላይ የግጭትና የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ሊሆን የሚችለው ድህነቱ እና የዜጎች የገቢ አለመመጣጠን ነው፡፡ ክቡር የሆነው የሰው ሕይወት ከምንም ሳይቆጠር በየቦታው የሚቀጠፈው እና ሥርዓት አልባነት የነገሠው ሥር የሰደደ ድህነት አንዱ ለሌላው እንዳይራራ እያደረገው ስለመጣ ነው፡፡ ድህነት ዜጎችን አካላዊ በሆነ መልኩ ብቻ ሳይሆን የማሰብና የማመዛዘን አቅማቸውን ጭምር እንደሚቀጭጨው ግልጽ ነው፡፡ ሰው ኑሮውን ነው የሚመስለው፡፡

ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ልማት ፈጣን የሆነ ግስጋሴ ካላደረገች ከገባችበት አዙሪት መውጣት አይቻላትም፡፡ ጥያቄው በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ሳይኖር እንዴት ኢኮኖሚያዊ ልማት ማምጣት ይቻላል፤ ፍትሐዊ የፖለቲካ ውክልና ሳይኖርና የዜጎች ነጻነት ሳይከበርስ እንዴት ነው ሰላምና መረጋጋት የሚሰፍነው የሚለው ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት የቅደም ተከተል ጥያቄ እያነሱ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ በእርግጥም በዚህች አገር ፍትሐዊ የፖለቲካ ውክልና እንዲኖር ያስፈልጋል፡፡ እውነትም ፍትሐዊ የሆነ የፖለቲካ ውክልና የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሳይገነባ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ማምጣት አይቻልም፡፡ ሰላምና መረጋጋት በሌለበት ሁኔታ ልማት ብሎ ነገር እንደሌለም ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

ግን ዴሞክራሲም፣ ፍትሐዊ ውክልናም በአንድ ጀንበር ሊሳኩ የሚችሉ ነገሮች አይደሉም፡፡ ጊዜው እስኪደርስ ላልተወሰነ ጊዜ በይደር ይቆዩ የሚባሉ አጀንዎችም አይደሉም፡፡ ሒደቱ በጥሩ መሠረት ላይ መጀመር አለበት፡፡ ሒደቱ በጥሩ መሠረት ላይ ከተጀመረ ጎዳናው ቀላል ባይሆንም ወደፊት መሄዳችን አይቀርም፡፡ ሥራ አግኝቶ በልቶ የማደር ጥያቄ ግን ጊዜ አይሰጥም፡፡

ፖለቲከኞቻችን ይህን የእንቁላልና የጫጩት እንቆቅልሽ ለመፍታት ጥረት ማድረግ ይገባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ካለችበት ሁኔታ አንጻር፣ ካላት የዘውግና የሃይማኖት ብዝሃነት አንጻር፣ ከምንገኝበት ጅኦ-ፖለቲካ አንጻር ወዘተ… እየተነተኑ ለዚህች አገርና ለሕዝቧ የሚበጀውን ነገር ማቅረብ ይገባቸዋል፡፡ የአገራችን ፖለቲከኞች ዴሞክራሲ እንደጎለመሰባቸው አገሮች (consolidated democracies) ፖለቲከኞች በግለሰቦችና አንዳንድ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የፖለቲካ ጨዋታ (issue and personality politics) ለመጫዎት መሞከር የለባቸውም፡፡ ስለ ግለሰብ ሳይሆን ስለ ሥርዓታት፣ ስለ ኢኮኖሚያዊና ኅብረተሰባዊ ሽግግር፣ ስለ አገር ህልውና ወዘተ… እንዲጽፉ፣ እንዲመክሩ፣ ምክረ ሐሳብ እንዲያቀርቡና እንዲከራከሩ ነው የሚጠበቅባቸው፡፡

ፖለቲከኞቻችን ርካሽ እና ሕዝብን ወደ እሳት የሚማግድ ሕዝበኛ የሆነ የፖለቲካ ጨዋታን በሩቁ ሊሸሹት ይገባል፡፡ ሕዝብን ተጠቃህ፣ ተዋረድክ፣ መጡብህ እያሉ መቀስቀስ ቀላል ነው፡፡ የተቀሰቀሰው ሕዝብ ወደ እርምጃ ሲገባና ውድመት ሲመጣ ግን ማጣፊያው ያጥራል፡፡ አንዳንድ ጸንፈኛ ፖለቲከኞች እስካሁን እንዳደረጉት ከኀላፊነት መሸሽም አይቻልም፡፡

በሥልጣን ላይ ካሉትም ከተፎካካሪ ፖለቲከኞቻችንም የሚጠበቀው ብዙ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ያለችበት ድህነት፣ መረን የለቀቀው ሥራ አጥነት፣ ላለፉት አርባና ሐመሳ ዓመታት ሲኮተኮት የከረመው፣ በተለይም ባለፉት 28 ዓመታት በከፍተኛ ደረጃ ሥር የሰደደው ጽንፈኛ ዘውጌ ብሔርተኝነት ተቀጣጣይ ቦምብ ነው፡፡ ይህን ተቀጣጣይ ቦምብ ኀላፊነት ባለው መልኩ ለማምከን ወይም እንደ ኒውክሌር ሚናውን ለይቶ ለመጠቀም ከፍ ያለ አርቆ አሳቢነትና ጥበብ ይጠይቃል፡፡ አንዱ ችግር ለሌላው አቀጣጣይና አባበሽ መሆኑን መገንዘብ ትልቅነት ነው፡፡

በሥልጣን ላይ ያሉት አካላት በዚህች አገር ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውጪ ያለው ጎዳና የሞት ጎዳና መሆኑን ከምር መቀበል ይገባቸዋል፡፡ ፍትሐዊ የፖለቲካ ውክልናና ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሰፈነበት ሥርዓት የግድ መሆኑን ከምር መቀበል ያስፈልጋል፡፡ በአገር ህልውና ወይም በድህነት ስም ወይም “ዴሞክራሲ ሒደት ነው” በሚል ካርድ ከዴሞክራሲ ወደኋላ ማፈግፈግ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ በዚህች አገር ኢኮኖሚያዊ ልማትን ማረጋገጥ የሞት ሽረት ጉዳይ መሆኑንም ከቃል በዘለለ ከምር ማመንና በተግባር ሠርቶ በማሠራት ማሳየት ያስፈልጋል፡፡

በተፎካካሪው ጎራም (ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው) ስለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እየሰበኩ በድርጅት ደረጃ ኢዴሞክራሲያዊ መሆንን፣ ስለ ፍትሐዊነት እየሰበኩ ኢፍትሐዊና አግላይ አጀንዳን ማራመድን መሻገር ያስፈልጋል፡፡ ስለ ሰላምና መረጋጋት አስፈላጊነት እየሰበኩ ሰላም የሚያደፈርሱ እርምጃዎችን ከመውሰድና አስተያየቶችን ከመስጠት መቆጠብ ይገባል፡፡

ሲራራ