October 25, 2020 

Regional Economic Outlook for Sub-Saharan Africa

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይ ኤም ኤፍ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት 1.9 በመቶ ብቻ እንደሚሆን ተነበየ። 

የአይ ኤም ኤፍ ትንበያ የኢትዮጵያ መንግሥት ከገለጸው የ6.1 በመቶ አጠቃላይ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ምጣኔ ጋር ሲነፃፀር በከፍተኛ ደረጃ ዝቅ ያለ ነው።

ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገሮች የ2020 ዓመታዊ የኢኮኖሚ ሁኔታን የተመለከተ ሪፖርት ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ባለፈው ሐሙስ ጥቅምት 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል። 

የገንዘብ ተቋሙ በሪፖርቱ እንደገለጸው፣ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገሮች ኢኮኖሚ በዋናነት የኮሮና ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ መከሰት ጋር ተያይዞ በተፈጠረው የኢኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ፣ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ማሽቆልቆል እንደሚገጥማቸው ገልጿል።

በዋናነትም በቱሪዝም ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ያላቸው አገሮች ከፍተኛ ጉዳት የሚደርስባቸው ሲሆን፣ ምርቶችን ኤክስፖርት በማድረግ ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ያላቸው አገሮችም በከፍተኛ ደረጃ ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታውቋል።

በዚህም መሠረት ከሰሃራ በታች ያሉ አገሮች አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት ሦስት በመቶ እንደሚሆን ገልጿል። 

በቀጣዩ ዓመትም የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከጉዳት እንደማይወጣ የገለጸው ሪፖርቱ፣ እ.ኤ.አ. በ2021 የአገሪቱ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕደገት 3.1 በመቶ እንደሚሆን ከወዲሁ ገምቷል። ለዚህም በምክንያትነት የገለጸው ወረርሽኙ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ እያደረሰ ባለው ጉዳት ሳቢያ የሚያገኙት የውጭ የገንዘብ አቅርቦትና ብድር በከፍተኛ የሚያሽቆለቁል መሆኑ ነው።

እንደ ተቋሙ ትንበያ በ2021 ከሰሃራ በታች ያሉ አገሮች 290 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የውጭ ፋይናንስ እጥረት ሊገጥማቸው እንደሚችል አስታውቋል።  በተጨማሪም አገሮቹ በከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እንደሚመቱ የገለጸ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ አንዷ ኢትዮጵያ እንደምትሆን አመላክቷል።

አይ ኤም ኤፍ ባወጣው የኢኮኖሚ ሁኔታ ሪፖርት የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት 1.9 በመቶ ብቻ ይሆናል ቢልም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ይህ ሪፖርት ከመውጣቱ ከሁለት ቀናት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ፣ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ መጠነኛ መቀነስ ቢታይም የ6.1 በመቶ ዕድገት እንደሚመዘገብ ተናግረዋል።

The late arrival of the pandemic in Ethiopia has spread the shock into the third quarter of 2020. The rural and subsistence-based agricultural sector has been relatively isolated, but tourism and hospitality services have been hit very hard. The recovery is expected to start gradually in the fourth quarter of 2020, with growth returning to precrisis rates by 2022

በ2012 ዓ.ም. የዘጠኝ በመቶ አጠቃላይ የኢኮኖማ ዕድገት ለማስመዝገብ አቅዳ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ 6.1 በመቶ ዕድገት መመዝገቡን የፕላን ኮሚሽን መረጃዎች ማመላከቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ይህ አፈጻጸም ከዕቅዱ አንፃር የ2.9 በመቶ ቅናሽ ቢታይበትም፣ ዕድገቱ ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከገጠመው የኢኮኖማ ፈተና አንፃር ሲመዘን ትልቅ ዕድገት እንደሆነ ገልጸዋል።

ለኢኮኖሚ ዕደገት መቀዛቀዙ የኮሮና ወረርሽኝ ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ የገለጹት ጠቅላይ ሚንስትሩ፣ በዚህ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ዘርፎች ትራንስፖርት፣ የትምህርት ዘርፍ፣ የሕዝብ አገልግሎቶችና ቱሪዝም መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዚህም መሠረት ትራንስፖርት 1.1 በመቶ፣ ትምህርት 1.8 በመቶ፣ የሕዝብ አገልግሎት 2.3 በመቶ እና ቱሪዝም 9.8 በመቶ የሆነ ዝቅተኛ ዕድገት ማስመዝገባቸውን ጠቁመዋል።

ከኢኮኖሚ ዘርፎች አንፃር ሲታይ ደግሞ፣ ግብርና የ4.3 በመቶ ዕድገት ሲያስመዘግብ፣ ኢንዱስትሪ 9 በመቶ፣ አገልግሎት ዘርፍ 5.3 በመቶ ዕድገት ማስመዝገባቸውን ገልጸዋል። ከሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች አንፃር ሲመዘን ከፍተኛ ዕድገት የተመዘገበው በማዕድን ዘርፍ መሆኑን ገልጸዋል።

 ( አማርኛው ዘገባ የሪፖርተር ነው።)

https://www.imf.org/en/Publications/REO/SSA/Issues/2020/10/22/regional-economic-outlook-sub-saharan-africa