የፌድራል መንግሥት “የአገር መከላከያ ኃይሎችን አደረጃጀትና ስምሪት በተመለከተ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ ሕጋዊ ኃላፊነትም ሆነ ስልጣን ስለሌለው የተወሰኑት ውሳኔዎች ተቀባይነትም ሆነ ተፈፃሚነት የላቸውም።” ሲል የትግራይ ክልል ተቃውሟል።

Tigray regional Gouvernement Emblem (Tigray Communication affairs office)

የትግራይ ክልላዊ መንግሥት በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ውስጥ የሚደረገውን የአደረጃጀት ለውጥ ተቃወመ። የክልሉ መንግሥት ከኤርትራ ጋር ዳግም ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ሥጋት እንዳለው አስታውቋል።

በአገሪቱ ጦር ውስጥ ተግባራዊ እየተደረገ ነው የተባለው ማሻሻያ “የትግራይን ሕዝብ ለማንበርከክ” ያለመ ሲል የወነጀለው የክልሉ መንግሥት ባለፈው ጥቅምት 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የፌድራል መንግሥቱ “የስልጣን ዘመኑ ስላበቃ ፖለቲካዊም ሆነ ወታደራዊ ውሳኔዎች የማስተላለፍ ምንም ዓይነት ሕጋዊ ኃላፊነትም ሆነ ስልጣን የለውም” ሲል ውድቅ አድርጓል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አዛዦች ባለፈው ሳምንት በሰጡት ማብራሪያ ተግባራዊ ተደርጓል ያሉት “የመከላከያ ሪፎርም” ከአገራዊ ለውጥ ጋር የተያያዘ እንደሆነ አስረድተው ነበር። ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አደም መሐመድ እንዳሉት ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከነባሩ አየር ኃይል በተጨማሪ የምድር ኃይል፣ የባሕር ኃይል፣ የሳይበር ኃይል፣ የልዩ ዘመቻ እና የኮማንዶ ኃይሎች ተቋቁመዋል። የጦሩ የዕዞች ቁጥርም ከአራት ወደ ስድስት ከፍ ብለዋል።

የጦሩ ዕዞች “የውስጥም የውጪም ጥቃቶችን ለመከላከል በሚያስችል አቀማመጥ ላይ እንዲቀመጡ” በማሰብ ቁጥቸው ከፍ ማለቱን ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ገልጸዋል። አዲስ የተቋቋሙት መቀመጫውን በአዲስ አበባ ያደረገው ማዕከላዊ ዕዝ እና በባሕር ዳር የሚገኘው የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ናቸው። ከዚህ ቀደም የነበሩት ሰሜን ዕዝ በመቐለ፤ ምሥራቅ ዕዝ በሐረር፤ ምዕራብ ዕዝ በነቀምት እንዲሁም ደቡብ ዕዝ በሐዋሳ ነበሩ።

በስድስት የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኘው የዕዞቹ አቀማመጥ “ወደ ፊት ሊያጋጥሙ የሚችሉ የጸጥታ ችግሮች እና ድንበሮቻችንን በተሻለ መንገድ ለመቆጣጠር እና የአገራችንንም ሉዓላዊነት በሚገባ ለመከላከል” እንደሚያስችሉ ጄኔራል አደም መሐመድ ተናግረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሀኑ ጁላ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ነበረበት ላሉት “የገለል ተኝነት ጥያቄ” መፍትሔ ለማበጀት ማሻሻያዎች መደረጋቸውን አስረድተዋል። 

“ኢሕአዴግ ከሌለ አገር ስለሚበተን፤ ኢሕአዴግን ሠራዊቱ መንከባከብ አለበት የሚል መልዕክት” ነበር ያሉት ጄኔራል ብርሀኑ “የሠራዊት ግንባታ አቅጣጫው በቀጥታ ኢሕአዴግን ብቸኛ የአገር ደሕንነት ኃይል አድርጎ የሚመለከት” ነበር ብለዋል። 

በኢትዮጵያ ጦር ውስጥ የተደረገው የአደረጃጀት ለውጥም ይሁን “የሠራዊት ግንባታ አቅጣጫ” ቅያሬ በቀጥታ የሚያስከትለው ለውጥ በግልጽ አልታወቀም።

ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል የሚመሩት የትግራይ ክልል ግን የፌድራል መንግሥቱ “የአገር መከላከያ ኃይሎችን አደረጃጀትና ስምሪት በተመለከተ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ ሕጋዊ ኃላፊነትም ሆነ ስልጣን ስለሌለው የተወሰኑት ውሳኔዎች ተቀባይነትም ሆነ ተፈፃሚነት የላቸውም።” ሲል ተቃውሟል።

“ከትግራይ ጋር የተያያዙ የስምሪትም ሆነ የአመራርና የአደረጃጀትና ለውጦች፣ የሰራዊትም ሆነ የጦር መሳሪያ እንቅስቃሴ ፍፁም ተቀባይነትና ተፈፃሚነት እንደሌለው ሊታወቅ ይገባል” ያለው የክልሉ መንግሥት የአገሪቱ ጦር አባላት “ይህንን ሕገ-ወጥና ከሕገ-መንግስታዊ ተልዕኳቸው ውጪ የሚደረግ አደረጃጀትና ስምሪት” እንዳይቀበሉ ጥሪ አቅርቧል።  

የትግራይ ክልል ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመሩትን የፌድራል መንግሥት “የኢሳያስ ስርዓት ቂም መወጫ ለማድረግ የአገርን ሉዓላዊነት አሳልፎ እስከመስጠት የደረሰ ክህደት እና በደል በመፈፀም ላይ ይገኛል” በማለት ወንጅሏል። መግለጫው “የኢሳያስ ስርዓት ከትግራይ ህዝብ ጠላቶች ጋር ተሻርኮ ዳግም ወደ ደም መቃባት ሊያስገባን ላይ ታች በማለት ላይ ይገኛል” የሚል ክስም አቅርቧል።