“ትንሽ ቆሎ ይዞ ወደአሻሮ ጠጋ”የዶናልድ ትራምፕ ንግግር
==============
የአገዛዙ አዳዲስ ካድሬወች አንድነት እና ትብብር ማሳየት አሁን ነው የሚሉ አስተያየቶችን እየለጠፉ ነው። መልካም ነበር የምንለውም ይህንኑ ነው ግን በአንድ ሕዝብ ላይ የጥፋት ዘመቻ የከፈተ ኃይል እና ለጥፋቱ ዋና ሞተር ከሆነው ኃይል አፎቱን ሳያዞር እና ግድያውን፤ ማሰደዱን እና ማፈናቀሉን ሳይገታ እንዴት አንድ መሆን ይቻላል?ትራምፕ ከኖቨምበር 3 በኋላ ታሪክ እንዲሆን ምኞታችን ነው። ለዚያም የአሜሪካን ሕዝብ በባለት ሳጥኑ በመወሰን ላይ ነው። በሀገራችን በአንድ ዘር ላይ የተከፈተው የፍጅት ዘመቻ ግን መሬት ላይ ያለ እና እንደ ቋያ እሳት እየለበለበ ያለ ያንን ሕዝብ ሰላሙን አሳጥቶ አባቶቹ በደም ያቆሟት ሀገሩ ላይ እንዳይኖር የምድር ሲአኦል ያደረገ ነው። ይህ የዘረኞች እና ባለግዜወች ፍጅት እስካልቆመ እንዴት ሀገር እና ሕዝብ አንድ ሆኖ በአንድ ለአንድ አላማ ሊቆም ይቻለዋል? ገዳይ እና ተገዳይ። አሳዳጅ እና ተሳዳጅ ማለት መሆኑ እንዴት ይጥፋን? ተከታታይ የዘረኛ መንግስቶች ወያኔ እና ብልጽግና ማለት ነው። የሀገር አንድነትን ያጎደሉ፤ ለመለያየት በህግ መብት የደነገጉ-አንድን ሕዝብ ጠላት ብለው የፈረጁ እና ዘመቻቸውን በዚያ ሕዝብ ላይ ያጧጧፉ፤ ከደቡብ እስከ ሰሜን እና እስከ እራሱ ባድማ ድረስ ዘልቀው የገደሉት ሳያንስ ከማሕል ከተማው ለማስለቀቅ በሁለተኛ የቋንቋ ስልት ጠራርገው ከመንግስት እና የግል ባለሀብት መስሪያ ቤቶች ሊያባርሩት እየተዘጋጁ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ሆኖ ሳለ የትራምፕ ሰፊ አፍ ተናገረ በሚል አንድ እንሁን ይላሉ። ይህ ነው “የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳ” ይባል ነበር። አይን አውጣወች አንድ ሀገር የገነባ ሕዝብ ላይ All-out war አውጀው ከላይ እንደጠቀስሁት የተመረጠ መንግስት ያልተስማማበትን እና አንድን የስራ ቋንቋ ለመቀየር ዘመን ወስዶ በጥንቃቄ በትውልድ ሊሰራ የሚችለውን ስራ በጀንበር እና በራሳቸው ጉልበት ያውም ያነጣጠሩበትን ሕዝብ ለማስወገድ ብሎም ሲርበው እና ሲቸገር ውጣ ሳንለው ጓዙን ጠቅሎ ይወጣል – አዲስ አበባ የኦሮሚያ የማድረጉን እቅድ ለማሟላትም አዲስ ስልት ዘይደው አንድነት ሊሉን ይዳዳሉ። የሀገር አንድነትን ለማምጣት በጮሌነት በግማሽ እምነት እና ልቦና እንዳልሆነ መታወቅ አለበት። ትራንፕ የሚወገዝ ንግግር አድርጓል ሁላችንም እናወግዛለን።ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ቅኝ አገዛዝ ተመርጣ ሳይሆን በሕዝቧ ደም እና አጥንት ነጻነቷን ጠብቃ ነው የኖረችው። ያ የተቻለው ግን መሪወቿ በአንድ አይን የሁሉም መሪ ሆነው በመገኘታቸው ነበር። ለዚያ ደግሞ የነጻነት ተጋድሎ ኩራት አሁን ጦርነት አውጀው እየጨረሱት ያለው ሕዝብ እንደነበር ታሪክ አይስተውም። ዛሬ ያነን ነጻነት አስጠባቂ ሕዝብ እያረዱ በሀገሩ እንዳይኖር መብት መንፈግ ብቻ ሳይሆን እየገደሉ እና እያሳደዱ ድንገት ሲደነግጡ አንድነትን መስበክ የጅሎች ስራ ከመሆን የማያልፍ ተግባር ነው። በጉራፈርዳ፣ በመተከል የሚፈሰው የንጹሐን ደም አልቆመም። አንድነት የሚኖረን በእኩል የሚዳኝ ፍርድቤት-በአንድ አይን የሚያይ መንግስት – የጋራ የሚያስማማ ህግ እና ስርአት ሲኖረን ብቻ ነው።