ሐራ ዘተዋሕዶ
October 28, 2020
- እነሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኰንን፣ “የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ” በሚል ሲያደርጉት የቆዩትን እንቅስቃሴ አቆመው፣ በአሐቲ ቤተ ክርስቲያን መዋቅር ሥር ኾነው፣ ለኦሮሚያ ክልል አህጉረ ስብከት ችግሮች መፍትሔ ለማስገኘት እንደሚጥሩ መስከረም 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ከሽማግሌዎች ጋራ የተስማሙበት እና መስከረም 22 ቀን 2013 ዓ.ም. ለቋሚ ሲኖዶስ ያረጋገጡበት ቃለ ጉባኤ፣ በንባብ ለምልአተ ጉባኤው በየተራ ቀርቦ ከተሰማ በኋላ፣ የተላለፈባቸው ክህነታዊ እግድ እንዲነሣ፣ ምልአተ ጉባኤው ልዩነት በሌለው ድምፅ ወስኗል፤

- ከሽማግሌዎች ጋራ በተደረሰበት እና ምልአተ ጉባኤው ይኹንታ በሰጠው ስምምነት እና ውሳኔ መሠረት፣ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኰንንን ጨምሮ አራት ካህናት፣ ችሎታቸው በሚመጥነው የቤተ ክርስቲያን መዋቅር እና አገልግሎት ላይ ተመድበው ያገለግላሉ፤
- ወደ አሐቲ ቤተ ክርስቲያን መዋቅር ተመልሰው በሕጓ እና በአሠራሯ መሠረት እንዲያገለግሉ ያደረጋቸው፥ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ባለፈው ዓመት ጥቅምት ምልአተ ጉባኤው፣ አፋን ኦሮሞን ጨምሮ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች፣ በስብከተ ወንጌል፣ በሥልጠና እና በመጻሕፍት ኅትመት የዕቅበተ እምነት ሥራዎች ላይ አተኩሮ የሚሠራ፥ የቋንቋዎች አገልግሎት ማስተባበሪያ ማዕከል በጠቅላይ ጽ/ቤቱ እንዲቋቋም፣ በተገቢው የሰው ኃይል እና በበጀት እንዲጠናከር ውሳኔ በማሳለፉ፣ ይህም ላነሡት ጥያቄ መሠረታዊ ምላሽ ለመስጠት እንደሚያስችል በማመናቸው እንደኾነ፣ እነሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኰንን በስምምነቱ አስረድተዋል፤

- ተፈጥሮ የነበረው ችግር በቤተ ክርስቲያንን አንድነት ላይ የሚያስከትለው ችግር ያሳሰባቸው ኦርቶዶክሳውያን ምሁራን እንዲሁም፣ “ጃን ትምህርት እና ሰላም ሲቪክ ማኅበር” የተሰኘ በጎ አድራጎት ተቋም፣ ካለፈው ዓመት ግንቦት አንሥቶ፣ ከእነሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኰንንና ስምንት የአደራጅ ኮሚቴው አባላት ጋራ አስቀድሞ በመወያየትና ስምምነቱንም ለቋሚ ሲኖዶስ በማቅረብ፣ ከዛሬው የተሳካ ውጤት ላይ ለማድረስ መቻሉ ተገልጿል፤
- የምልአተ ጉባኤውን ይኹንታ ያገኘው ይኸው ስምምነት በቀጣይም፣ አደራጅ ኮሚቴው ይጠቀምበት የነበረውን የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያ እና ስታፎች፣ ለቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት የሚውልበትን ኹኔታ ጨምሮ በሒደት የሚከናወኑ፣ ዝርዝር የማስፈጸሚያ የድርጊት መርሐ ግብርን ማካተቱ ታውቋል፤
- በሌላ በኩል ምልአተ ጉባኤው፣ በዛሬው የቀትር በኋላ ውሎው፣ በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት በምስካበ ቅዱሳን ቆጋ ኪዳነ ምሕረት ገዳም የተፈጸመውን የዶግማ እና የቀኖና ጥሰት አስመልክቶ፣ የሊቃውንት ጉባኤ እና የአካባቢው ተወላጆች እንዲሁም ብፁዓን አባቶች ያሉባቸው ኹለት ኮሚቴዎች፣ ከሰፍራው ድረስ በመሔድ ያቀረቧቸውን ሪፖርቶች እና መረጃዎች መሠረት በማድረግ ጉዳዩን መመርመር መጀመሩ ተጠቁሟል፡፡
