25 October 2020
በነሲቡ ስብሐት (ሰሜን አሜሪካ፣ ቨርጂኒያ)
ክፍል ሁለት
የመጽሐፉ ርዕስ፡ ‹‹ዳኛው ማነው?›› የብርሃነ መስቀልና የታደለች ሕይወት
በኢሕአፓ የትግል ታሪክ
ደራሲ፡ ታደለች ኃይለ ሚካኤል
የኅትመት ዘመን፡ 2012 ዓ.ም.
ገጽ ብዛት፡ 442
-
የብርሃነ መስቀል የእስር ቤት ቃል ምርመራ
የመንግሥቱ ኃይለ ማርያም መወገድና የኢሕአፓ የመከላከል ዕርምጃ
‹‹ዳኛው ማነው›› ስለከተማው ራስን የመከላከል ሒደትና ስለመኢሶን እየተደጋገመ ኢሕአፓ የሚወነጀልበትን በገጽ 254 እና 255 የተዘረዘረው የብርሃነ መስቀልን የቃል ምርመራ በማጠናከር ነው፡፡
ብርሃነ መስቀል ስለመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ግድያ ተቃውሞውን ያሰማበትን እዚህ አልዘረዝረውም፡፡ በምርመራ ቃል ዘገባው ገጽ 21 እስከ 23 ያለውን አንብቡ፡፡ ብርሃነ መስቀል በዚህ ዘገባ ስለመንግሥቱ ኃይለ ማርያም አለመገደል አጥብቆ ይከራከራል፡፡ በእውነት በዚያ ዘመን የደረሰባቸውን እጅግ ዘግናኝ ግርፊያና ትልተላ ተቋቁመው እንኳን መዘላበድ አይደለም የሚያውቁትን ምስጢር እንደያዙ የተሰጠው ወጣት ወንድምና እህቶቻችን ለኢሕአፓና ለአገር ብለው ነው፡፡ ያውም በሕይወት ኖሮ የቀይ ሽብርን ፍጅት የተመለከተ፣ ደርግና ፋሺስቱ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም እንዴት እያደረገ ተቃዋሚ ኃይሎችን ብቻ ሳይሆን ጎኑ ያሉትንም እንደረሸነ የሚያውቀው ብርሃነ መስቀል እንደ ፍቅሬ ዘርጋው ‹‹በኢሕአፓ ውስጥ ልዩነት ቢኖርም ከእኔ ግን ምንም አታገኙም›› ብሎ ተተልትሎ እንደተሰዋው ቆራጥነቱን ቢያሳይ ዕውን ዛሬ አስተያየትሌላ በተጻፈ፡፡ ግና ስለብርሃነ መስቀል ባለቤቱ ወ/ሮ ታደለች ሊመሰክሩ ከሚችሉት በላይ ራሱ ተናግሯልና ለዚህ ነው ‹‹ዳኛው ማነው?›› መጽሐፍና የብርሃነ መስቀል የምርመራ ቃል ዘገባ ግንኙነትና ተዛማጅነት ያላቸው የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጾች በመሆናቸው ትኩረት የሰጠሁት፡፡
መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ደርግ አስተባባሪ ኮሚቴ ብሎ ራሱን ማሰባሰብ ከጀመረበት ዘመን ጀምሮ ፈርጥጦ ከሄደበት እስከ ግንቦት 1983 ዓ.ም. በአገራችንና ሕዝባችን ላይ የሠራውንና የፈጸመውን ግፍ ለመዘርዘር አንድ መጽሐፍ አይበቃውም፡፡ በትንሹ መንግሥቱ ላይ ኢሕአፓ የመግደል ሙከራ ማካሄዱ ልክ ነበር ወይስ አይደለም የሚለውን ዕይታዬን ብቻ አቀርባለሁ፡፡
ከየካቲቱ 1966 ዓ.ም. የአብዮት ፍንዳታ በኋላ በተሰባሰበው የወታደሩ ክፍል ውስጥ የመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ስም ገኖ የወጣው ያለምክንያት አይደለም፡፡ በማንኛውም አንድ እንቅስቃሴ ውስጥ ሁልጊዜም ቁንጮ ሆነው ስማቸው የሚጠራ ግለሰቦች አሉ፡፡ በተማሪው ንቅናቄ እነጥላሁን ግዛው፣ ዋለልኝ መኰንን፣ በኢሕአፓ እነተስፋዬ ደበሳይ፣ ብርሃነ መስቀል፣ በመኢሶን ኃይሌ ፊዳ የመሳሰሉት የሚጠቀሱት ከእንቅስቃሴው ጎላ ብለው ስለወጡ መሪነቱን ስለወሰዱም ጭምር ነው፡፡ እነዚህን የመሰሉ ግለሰቦችና መሪዎች ታዲያ ሁሉም አንድ ናቸው፣ ሁሉም በበጎ ጎን ብቻ ይነሳሉ ሳይሆን በጥፋታቸውም ጎልተው ይነሳሉ፡፡ የጀርመኑ አዶልፍ ሂትለር በጨካኝነቱ ክብረ ወሰን በመስበሩ እስከ ዛሬ ይተረክለታል፡፡ የእኛም መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በጎልማሳ ዕድሜው ስሙ ብቅ ብቅ ማለት ጀምሮ ይበልጥ ኃይለ ሥላሴን በማውረድ ሒደቱ ላይ ኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት በመገኘት ቀጥተኛ ተሳታፊ ከመሆን ጀምሮ በተለይ በኅዳር ወር 1967 ዓ.ም. የ60ዎቹ ጅምላ ፍጅት እጅጉን ስሙ ጎላ፡፡ በላቸው ነበር የተባለለት፡፡ ከዚያ ወቅት ጀምሮ በደርጉ ውስጥ የሚካሄደውን ሒደት ኢሕአፓ እንደ ፓርቲነቱ ይከታተላል፡፡ ከደርጉ ውስጥ ደጋፊ ብቻ ሳይሆን ንቁ ተሳትፎ ያላቸው አባላት እንዳሉት ይታወቃል፡፡ የደርግ ስብስብ ውስጥ ቀና አሳቢዎችና የመጡበትን ተልዕኮ አጠናቀው ወደ መንግሥትነት ከመቀየር ይልቅ ወደ ጦር ሠፈራቸው መመለስ እንደሚገባቸው የሚጥሩ፣ የሚመክሩ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ በዚህ ሒደት በአንድ ስብስብ ውስጥ ወደ አምባገነንነት የሚያመራ አንድ ግለሰብ ብቅ ሲል ተስተውሏል፡፡ በስተመጨረሻም የመጣው ሁሉንም ተራማጅ ኃይሎች ደምስሶና ረሽኖ ‹‹ከአንድ ፈላጭ ቆራጭ አመራር ጋር ወደፊት!›› ያሰኘ አምባገነን ብቻ ሳይሆን ፋሺስት መሪ ነበር አገሪቱ የገጠማት፡፡ ይህ እንዳይመጣ ነበር አርቆ አሳቢው ኢሕአፓ አስቀድሞ ያስገነዘበው፡፡
ይህ ሳይገጥም በፊት ሒደቱን ለመግታትና ሌሎቹ የደርግ አባላት የኃይል ሚዛን እያዩ ወደ ነፈሰበት የሚያዘነብሉ ምን እንደሚሠሩ እንኳን የማያውቁ፣ ግልጽ አቋም እንዳልነበራቸው ይታወቃል፡፡ ቢሆንም በወቅቱ የመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ተከታዮችም አልነበሩም ማለት አይደለም፡፡ ኢሕአፓም በ1967 ዓ.ም. እና በተለይ ደግሞ በ1968 ዓ.ም. የትግል ጉዞው በአደረገው ሙሉ ሰላማዊ ትግል እጅጉን የሰመረለትና የተዋጣለት ነበር፡፡ ኢሕአፓን ከፍ ካደረጉት ዋና ጉዳዮች አንዱ ራሱን ለሕዝብ ይፋ ከማውጣቱ በፊት የተዘጋጀበት፣ የተገነባበት የትግል መሠረቱ ነው፡፡ ዝም ብሎ ዘሎና ተሰብስቦ ፓርቲ ነኝ ያለ ድርጅት አይደለም፡፡ ይህ ጠንካራ መሠረቱ ነው ራሱን ይፋ ባወጣ በአንድ ዓመት ውስጥ በመላ አገሪቷ መዋቅሩን አስፋፍቶ፣ ትግሉን በበላይነት የመራው፡፡ በዚህ ሒደት ገና ከጅምሩ ‹‹ለደርግ ሒሳዊ ድጋፍ›› ያለው መኢሶን በድርጊቱ እንኳንስ ከወጣቱ፣ በፖለቲካው ጥልቅ ዕውቀት ባይኖራቸውም እንኳ በእናት አባቶች የተጠላው፡፡ መኢሶን በአጭር ጊዜ ባጣው ሕዝባዊ ድጋፍ (Mass Base) ምክንያት ‹‹ለደርግ ሒሳዊ ድጋፍ›› የሚለውን ‹‹ትንታኔውን›› ደርግን ተገን በማድረግ ኢሕአፓን ማዳከም፣ ማጥቃት እየለወጠው መጣ፡፡ ለዚህ ሒደቱም ዋና መሣሪያ ሆኖ ያገኘው መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ነበርና የጥፋት እርሾውን ጠነሰሰ፡፡ የዚህ ውጤት ደግሞ ደርግ ሥልጣኑን ከያዘበት 1967 ዓ.ም. ጀምሮ የነበረውን የገዳይነት ስሜት ይበልጥ በመረዳት በመኢሶን ገፋፊነት በ1968 ዓ.ም. ይበልጥ የሚያደርጋቸው እስር፣ ማሰቃየት፣ ግድያ ከሕዝቡ የዕለት ተዕለት ሕይወት ጋር የተያያዘ በመሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነበር፡፡ ተያዙ፣ ተደመሰሱ፣ ይወድማሉ፣ ዕርምጃ ተወሰደባቸው በእነዚህ ዓመታት የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የየዕለት ዕትም ላይ ያልወጣበት ወቅት አልነበረም፡፡ የዚህ የደርግ ወደ ጨካኝነት አካሄድና የመኢሶን ደባ ለኢሕአፓ አመራር የቅርብ ዕውቅናና ክትትል የነበረው ለመሆኑ የወቅቱን ዲሞክራሲያዊ ዕትሞች ማንበብ በቂ ነው፡፡
ከዚህ በላይ ምን ልትጽፍ ፈለግህ አትበሉኝና ከላይ እጅግ በአጭሩ ያስቀመጥኩላችሁን ትንታኔ ከደርጉ ውስጥ አደገኛ አካሄድን እየገፋፋና እየመራ የተጓዘው መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ነበር፡፡ በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ የበላይነቱን እየተቆጣጠረ የገሠገሰው ኢሕአፓ ላይ ደርግ ሐሙስ መስከረም 6 ቀን 1969 ዓ.ም. ‹‹ፀረ ሕዝብ ሁሉ በጭቁኑ ጫማ ሥር እንደ ድመት ያለቅሳል›› በሚል በሰጠው መግለጫ ኢሕአፓን በጠላትነት በመፈረጅ የማጥፋት ጦርነት አወጀበት፡፡ ኢሕአፓም ለዚህ የማጥቃት እወጃ ለመከላከል ተዘጋጀ፡፡ በመሆኑም በደርግ ውስጥ ብቅ እያለ የመጣው የመንግሥቱ ኃይለ ማርያም አምባገነናዊ ሒደት በአጭር መቀጨት እንዳለበት በፓርቲው ሲወሰን የመንግሥቱ ኃይለ ማርያም መወገድ ያለ ጥርጥር የወቅቱን የፖለቲካ አቅጣጫ ሙሉ በሙሉ ይቀይረው ነበር፡፡ በወቅቱ በመዋለል ላይ ያሉት የደርግ አባላት በአብዛኛው ወደ ቀና አስተሳሰብና ዲሞክራሲያዊ ጎዳና መሳብ አስቸጋሪ አልነበሩም፡፡ የመኢሶንና ወዝ ሊግ መሪዎች በማግሥቱ ሻንጣቸውን ሸክፈው ከአገር ይወጡ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ አቅጣጫ ሙሉ በሙሉ ሊቀየር ይችል ነበር፡፡ ሆኖም ግን አልተሳካም፣ አልሆነም፡፡ ከዚህ በኋላ ነው የኢሕአፓ ስህተት ሊጠቆም የሚችለው፡፡ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ከአደጋው ስለተረፈ ‹‹ብለን ነበር›› ማለት የፖለቲካ ትርፍ/የበላይነት አያስገኝም፡፡ ኢሕአፓ ሲጀመር ይህንን ዕርምጃ ሲወሰድ ሁልጊዜ ሊገጥሙ የሚችሉ ጉዳዮች አሉና በቂ ዝግጅት ተደርጎበታል ወይ? ባይሳካስ ቀጣይ ፕላን ምንድነው? የሚለውን ማየት ተስኖት ነበር፡፡
ከመስከረም 13ቱ የመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ግድያ ሙከራ መክሸፍ በኋላ ኢሕአፓ ለሌላ ዕርምጃ ከመጓዙ በፊት የዚህ ዕርምጃ መክሸፍ በራሱ የሚያመጣውንና በመንግሥት በኩል ሊወሰድ የሚችለውን ዕርምጃ የትግል ሥራውን እየሠራ መከታተል ነበረበት፡፡ በወቅቱ መስከረም 21 ቀን 1969 ዓ.ም. የተደረገው የመኢሶን አመራር አባል ፍቅሬ መርዕድ ግድያ ለምን አስፈለገ? የሚለው ዛሬም ያቃጭልብኛል፡፡ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ላይ የተሞከረው ግድያ ሳቢያ የደርግና የግል ዕርምጃቸው ምን ሊሆን እየተገመተ ወዲያውኑ ከመኢሶን አመራር መግደል የመንግሥቱ ኃይለ ማርያምንና የመኢሶንን ግንኙነት እጅጉን ከማጠናከሩም በላይ መኢሶን ኢሕአፓ ላይ ይበልጥ በትሩን ለማሳረፍ አጋዥ ኃይል ያገኝ ዘንድ አመቻችቶለታል፡፡
በእኔ አመለካከት ዛሬ ኢሕአፓ ለድል ስላልበቃና ስለተመታ የምቃወመው ሳይሆን ኢሕአፓ ከትግል ጉዞው አንፃር በመርህ ደረጃ የተጀመረው የከተማው ራስን ከጥቃት መከላከል ዕርምጃ አግባብ ነበር እላለሁ፡፡ ስህተቱ ፓርቲው ለዚህ ሲዘጋጅና ተግባራዊ ከማድረጉ በፊት መመለስ የነበረባቸው ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች ዛሬ ላይ ሆኜ ሳያቸው የከተማው ፓርቲውን የመከላከል ሒደት በቂ ዝግጅት ሳይደረግበት መጀመሩ አግባብ እንዳልነበር መናገር ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በቂ የመሣሪያ፣ የትጥቅ አቅርቦት ነበር ወይ? መጠነኛም ቢሆን በወታደራዊ መስክ የሠለጠኑና ልምምድ ያደረጉ እስኳዶች ነበሩ ወይ? በ1967 እና 1968 የትግል ወቅት በተለያየ አጋጣሚ ለመንግሥት የተጋለጡ አባላቱን ወደ ገጠር የማሸሽ ዕቅድ ነበር ወይ? በከተማው እጅግ ባስቸገሩ ግለሰቦች ላይ በሚወሰደው ዕርምጃ መንግሥት ለሚወስደው አፀፋ የሚጋለጡና አካባቢ መልቀቅ ላለባቸው አባላቱ አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ ግብረ ኃይል ነበር ወይ? ዕርምጃ የሚወሰድባቸው በሚገባ ጥናት ተደርጎ በኮሚቴና በሚመለከተው አካል የሚወሰን ነበር ወይ? እና መሰል ጥያቄዎችን ስንቃኝ ያለምንም ምስክር ደካማ ጎኖቹ ያመዝናሉ፡፡ ለዚህ ነው እየከፋ ለመጣው የደርግ አፀፋዊ ምላሽ መሸሽ እንኳ ሳይቻል እምሽክ ያልነው፡፡ ስህተቱ በየከተማው ራስን ከጥቃት መከላከል መጀመሩ ሳይሆን፣ ለመጀመር የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች ተሟልተው ነበር ወይ? የሚለው ነው ሊታይና ሊተችበት የሚገባው ባይ ነኝ፡፡
ብርሃነ መስቀል መረዳት የነበረበት በኢሕአፓ የታቀፉ አባላት፣ ደጋፊዎች በጥቅሉ ፀረ ደርግ ትግሉ የጥቂት አመራሮች ወይም እሱ እንደሚለው ‹‹የክሊኩ›› አልነበረም፡፡ በዚህ የግል ዝና ዕጦት ወይም ብርሃነ እንኳ ራሱ ትክክል መሆኑን ቢገምትም ከኢሕአፓ የሚያገኘውን መረጃ ለማክሸፍና ተግባራዊ እንዳይሆን በሚያደርገው ሒደት እየጎዳና አሳልፎ እየሰጠ የነበረው በዚያ ጊዜ በአሥራዎቹና በሃያዎቹ ውስጥ ያለነውን በርካታ ወጣቶችን እንኳ አላሰበንም፡፡ በብርሃነ መስቀል የተሰባሰበው ቡድን ለደርግ የኢሕአፓን መዋቅርና ምስጢር አሳልፎ በመስጠት ምን ያህል የሕዝብ ልጆችና ድርጅቱንም እንደጎዱ መሰመር ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ በዚህም ድርጊቱ ኢሕአፓን በማዳከሙ የሱም አሻራ ቀላል እንዳልነበር ከምርመራ ቃሉ ገጽ 34 ላስነብባችሁ፣
‹‹. . . ጥር 17 ቀን 1969 ዓ.ም. ከፓርቲው ኮሚቴዎች ከተገለልን በኋላ (በማዕከላዊ ኮሚቴው ውሳኔ መሠረት) በእኔ በኩል ክሊኩ ከአስቀመጠኝ ቦታ ማለትም ከሰባ ደረጃ አካባቢ በመሠወር ግንኙነት አቋረጥሁ፡፡ ከዚህ በኋላ ዋናው ተግባሬ የዕርማት ንቅናቄውን ማስፋፋት ሲሆን፣ ከጥር 18 ቀን 1969 ዓ.ም. ጀምሮ ክሊኩ ሊወስዳቸው ያቀዳቸውን ፋሺስታዊ የግድያና የኃይል ዕርምጃዎች መቃወምና በተግባርም ማክሸፍ ነበር፡፡. . .›› (ስርዝ የተጨመረበት) እያለን የድርጅቱን ምስጢርና ሥራዎችም የሚያገኘውን ሲገልጽ፣
‹‹. . . መመርያውም የደረሰኝ ከእርማት ንቅናቄው መሥራቾች አንዱ ከነበረው በክሪ የአዲስ አበባ ዞን አንድ (መርካቶ አካባቢ) ጸሐፊ ስለነበር በእሱ አማካይነት ነበር፡፡. . .›› ይህ አሳዛኝ መረጃ ብርሃነ መስቀል በእልህ ስንቱን አባላት እንደ ጎዳና ድርጅቱን በተቻለው አቅም ለደርግ አሳልፎ እንደሰጠ ጠቋሚ አይሆንምን? እዚህ ላይ ነው ብርሃነ መስቀልና ጌታቸው ማሩ ቅድሚያ ተግባራቸው ፓርቲውን በሚያውቁት የመዋቅር ሰንሰለት እየበጠሱ፣ የሚተላለፉ መረጃዎችን እያፈኑ፣ ከመዋቅር ውጭ የሚያውቋቸውን እየተገናኙ የሚችሉትን ያህል ማዳከሙን እንደገፉበት ኢሕአፓም ያውቀዋል የቃል ምርመራውም ይነግረናል፡፡ ታዲያ ይህ የአንጃነት ተግባር አይደለምን?
ስለእርማት ንቅናቄው
አምባሳደር ስለእርማት ንቅናቄው በሰፊው ዘግበዋል፡፡ ይህንን ክፍል ብርሃነ መስቀል በቃል ምርመራው ላይ በደንብ አልዘረዘረውም፡፡ ምናልባት እንደገና ኢሕአፓን ልታደራጅ ነው በሚል ክሱ እንዳይጠነክርበት ወይም ከስም ያልዘለለ እንቅስቃሴ በመሆኑ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህን ክፍል ሳነበው ራሴን 1969 ዓ.ም. አጋማሽ ነፃ ዕርምጃ፣ ከዚያም 1970 ዓ.ም. ቀይ ሽብር፣ ቀጥሎም ከሞት የተረፉት የእስር ቤት ኑሮ የተፈታነው ደግሞ ሕይወት እንደ ገና የቁም እስር ስቃይ ላይ ራሴን አስቀምጬ ነው፡፡
ስለቀይ ሽብር አምባሳደርም ሆኑ ሌሎች አንባቢያን እጅግ በርካታ የተጻፉ እውነተኛ መጻሐፍትን ማንበቡ በመጠኑም ቢሆን ግንዛቤ እንደሚሰጥ እየጠቆምኩ በካዛንችስ አካባቢ የነበረውን የቀይ ሽብር ሁኔታ የራሴን እውነተኛ ታሪክ መጽሐፍ ‹‹ፍፁም ነው እምነቴ የከፍተኛ 15 ቀይ ሽብር እውነተኛ ታሪክ›› መስከረም 2007 ዓ.ም. ትመለከቱት ዘንድ እጠቁማለሁ፡፡ ቃላት ካልተገኘለት የደርግ አስከፊ ግርፍና ግድያ የተነሳ መላ የኢትዮጵያን ሕዝብ ያስደነገጠና እግዚኦ ያሰኘ ዘመን ነበር፡፡ ሁሉም ወጣት ራሱን የሚያድንበት መንገድ ፈላጊ ሲሆን፣ ወላጆች የተሰቃዩበት፣ ሕፃናት የፈዘዙበት፣ ቤተሰብ በጥቅሉ የሐዘን ማቅ የለበሰበት ዘመን ነበር፡፡ ይህ ወቅት ኢሕአፓ፣ አንጃ እየተነጠለ ሳይሆን ወጣቶች በጅምላ እየታደኑ የሚገደሉበት፣ የሚሰቃዩበት ዘመን ነበር፡፡ ከደርግ እስር ለጊዜው አምልጠው ወደ ዘመዱና ወደ ክፍለ አገር የሄዱት እንኳን በሄዱበት ሁሉ ተመሳሳይ ሒደት በመኖሩ ተመልሰው እየመጡ ‹‹ለሞት›› እጃቸውን የሰጡበት ወቅት ነበር፣ እንኳን ሌላ ሊታሰብ፡፡ በዚህ አስከፊ ሁኔታ የኢሕአፓ መዋቅር እየተበጣጠሰ ድርጅታዊ መረጃ በጠፋበትና መተማመን በተሸረሸረበት ወቅት ‹‹ዕርማት ንቅናቄ›› ብሎ ሰፋ ያለ እንቅስቃሴ እንደነበር ለማመን ያዳግተኛል፡፡ ከአዲስ አበባ መውጣት መግባትም ሆነ በየትኛውም ክፍለ አገር መዘዋወር እጅጉን አዳጋች ነበር፡፡ በፀጉረ ልውጥነታቸው ብቻ እየተጠረጠሩ የተያዙ የተገደሉ ቀላል አልነበሩም:: ሽሽቱና ከአገር መውጣቱ ተሳክቶላቸው የነበሩ ዕድለኞች ናቸው ከማለት ሌላ የሚኖር አይመስለኝም፡፡
‹‹ታጥቆ አደራጅና አንቂ ቡድን (ታአአቡ)›› ራሱ ስሙን ሳየው መኢሶን ነው ትዝ ያለኝ፡፡ ‹‹ለነቃ፣ ለተደራጀና ለታጠቀ የሕዝብ ትግል›› በሚል ገና ከጅምሩ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ታጥቆ መታገል ሲገባው በረሃና ውጣ ውረዱ፣ አቀበትና ቁልቁለት እንዴት ይደፈራልና በሒሳዊ ድጋፍ ቤተ መንግሥት ተቀምጦ በሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽሕፈት ቤት ስም ሲፒኤ የማያውቀው የመንግሥት በጀት ተመድቦለት በዚያ ጊዜ በትንሹ በወር 900 ብር ደመወዝ እየተከፈላቸው ትግል ካሉት መዶለትን መረጡ፡፡
እናም ታአአቡ በአጭር ጊዜ የተደራጀውን፣ የታጠቀውን ኢሕአፓና በእሱም ሥር የተሰባሰቡትን ንቁ አባላቱንና ሕዝባዊ ድጋፉን አራግፎ እንደ ገና ለነቃ፣ ለተደራጀ፣ ለታጠቀ የዕርምት ንቅናቄ ሲባል ዕውን አዋቂነት ነው ወይስ የመረበሽና የንዴት ውጤት? ያሰኛል፡፡
ታጋይ ታደለች በዚህ ጉዳይ የሰጡን ትንታኔ ብርሃነ መስቀል በወቅቱ የዕርማት ንቅናቄ በሚል በድርጅት ላይ ድርጅት ምሥረታ እንደተያያዘ ነው፡፡ እዚህ ላይ ነው አንጃ የሚያሰኘው፣ ከባዱም ጥፋት፡፡ የዕርማት ንቅናቄውን ለማጠናከር እነብርሃነ መስቀል ከፓርቲው ሰው ለማሰባሰብ ውስጥ ውስጡን ቅስቀሳ ሲያካሂዱ፣ ዕቅድ ሲያወጡ፣ ፓርቲውን ሲሸረሽሩ ነበር ማለት ነው፡፡ ይህንን ነበር ኢሕአፓም በወቅቱ ለአባላቱ ያሳወቀው፡፡ ለዚህም መጽሐፉ በገጽ 302 ይህንን መረጃ ያስነብበናል፡፡
‹‹. . . የዕርማት ንቅናቄው ቅድሚያ ዝግጅት በማድረግ፣ ከከተማም ሰዎች በማሰባሰብና መሣሪያም በማምጣት አንድ ድርጅታዊ መዋቅር መሥርቶ ሰዎችንም ማወያየት ተጀመረ፡፡›› ስርዝ የተጨመረበት ገጽ 302፡፡
‹‹. . . የእርማት ንቅናቄውን ለመመሥረት የሥራ ክፍፍል በማድረግ ለመንቀሳቀስ የተሰየሙት ብርሃነ መስቀል፣ ጌታቸው ማሩ፣ አብዩ ኤርሳሞና በክሪ ነበሩ፡፡›› ገጽ 299፡፡
‹‹ . . . የ‹ዕርማት ንቅናቄው ጥያቄ ሌላ ሳይሆን ፓርቲው የሚያካሂደው ሕገወጥ የተሳሳተ የትግል መስመር በመያዝ ጠቅላላ ጉባዔ የሚጠራበትን ለማመቻቸት ነበር፡፡ . . .›› (ገጽ 298)፡፡
‹‹የእርማት ንቅናቄው ቁጥራቸው 20 የሚደርሱ አባሎችን (በተለያየ ጊዜ የተቀላቀሉ) ይዞ፣ ሰፊ ውይይት በማድረግ ከዓላማው ጋር የሚሄድ፣ ታጥቆ አንቂና አደራጅ ቡድን (ታአአቡ) እንዲቋቋም ተደረገ›› ገጽ 303፡፡
ብርሃነ መስቀል በሰኔ 1967 ዓ.ም. ከኢሕአፓ ፖሊት ቢሮ ዝቅ በማለቱና በማዕከላዊ ኮሚቴ መካተቱ የበላይነቴን ተነጠቅሁ የሚል ስሜት ቢያድርበት አይፈረድም፡፡ ግና ደርግ ተራማጅ ነው፣ ደርግ ፋሺስት አይደለም፣ ከደርግ ጋር ያለ ቅድመ ሁኔታ ግንባር መፍጠር አለብን፣ በከተማው የተጀመረው ራስን የመከላከል ዕርምጃ መቆም አለበት የሚሉ አመለካከቶች፣ የመስመር ልዩነቶች ከኢሕአፓ እየነጠለውና ጥያቄ ውስጥ እየከተተው መምጣቱን በራሱ የምርመራ ቃል የተቀመጠ ነው፡፡ ኢሕአፓ እሱ በሚፈልገው መንገድ እንዲሄድ ስላልቻለ በዕርማት ንቅናቄ ስም ሌላ ድርጅት ለማዋቀር በሚያደርገው ሒደት ፓርቲውን ለማፈራረስና ለማዳከም ድርጅታዊ ምስጢር ወጥቷል፣ ተሰጥቷል፣ አባላት እንዲጋለጡ ተደርጓል፣ መሣሪያና ገንዘብ ተወስዷል ሌላም ሌላ፡፡ ይህ ነው አሳዛኙና ዋናው መሠረታዊ ስህተት፡፡ ኢሕአፓ በ1968 ዓ.ም. ለገነባው ሕዝባዊነት እንኳንስ ወዳጅ ጠላት የመሰከረውና ግራ የገባው ወቅት ነበር፡፡ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ አባላቱም ድርጅቱ ፍፁም አይደለምና ከመለስተኛ ድክመቶቹ ጋር ቅድሚያ ጉዟቸው፣ ትግላቸው፣ ጥንካሬያቸው ደርግን ከሕዝብ ጫንቃ ላይ ማውረድ ነበር፡፡ ‹‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል›› ወይም ‹‹ባልበላም ጭሬ አፈሰዋለሁ›› አባባልና አካሄድ አገር ልታገኛቸው የማትችል ብርቅዬዎችን አሳጣ፣ ኢሕአፓንም አስመታ፡፡ ዕውን ከኢሕአፓ ደርግ ይመረጥ ነበርን? ዕውን ከኢሕአፓ መኢሶን ተወዶ ነበርን? ዛሬ ላይ ሆነን እንኳ ‹‹ምነው እነኛ ኢሕአፓዎች በተንቀሳቀሱ›› የሚባልበት ምክንያት ሁሉም ጥንካሬውንና ለአገርና ለሕዝብ ያለውን ቁርጠኛነት ስለሚረዳው ነው፡፡ ይህንን ጠንካራ ኃይል ውስጥ ሆኖ ዕቅድ በመንደፍ ሌላ መዋቅር ለመዘርጋት መነሳሳት ‹‹ዳኛው ማነው›› በሰፊው የገለጸልን ምስክርነት ፓርቲው የሚለንን ይበልጥ በማጠናከሩ በኢሕአፓ ውስጥ ስለተፈጠረው አንጃ አካሄድ ግልጽ የሆነ መልስ አግኝቼበታለሁ፡፡
መኢሶን የቀይ ሽብርን ዕቅድ አውጥቶና ጠንስሶ ካበቃ በኋላ ከደሙ ንፁህ ነኝ ለማለት ‹‹በሁለት በኩል ተጠቃን›› ይለናል፡፡ ‹‹ዳኛው ማነው›› መጽሐፍም በድርጅት ላይ ድርጅት ሊመሠርት የተነሳውን የ‹እርማት ንቅናቄ ቡድን ‹‹. . . በሁለት ኃይሎች መካከል ዒላማ ተደርገዋል፡፡ . . .›› (ገጽ 299) ይለናል፡፡ እንግዲህ ደርግ ፋሺስት አይደለም፣ ደርግ ገዳይ አይደለም የተባለለት አቋም ለምንሳ ከኢሕአፓ የተገነጠለውን ለማሳደድ ፈለገ?
እዚህ ላይ ግልጽ ለማድረግ እንደውም ኢሕአፓ ነው ከውስጥ በነብርሃነ መስቀል፣ ከፊት ለፊት በደርግና ከባቢዎቹ በተለይ መኢሶንና ወዝ ሊግ፣ ከጀርባ በሕወሓት/ወያነ፣ በመሰሪ ሴራ በሻዕቢያና በባዕዳን ኃይላት ተከቦ ኢትዮጵያን የት ሊያደርስ የሚችል ትውልድ እምሽክ የተደረገው፡፡ በዓድዋና ማይጨው ወረራ ያላገኟትን ኢትዮጵያ በተቀነባበረ ታላቁ ሴራ ትውልዷን ቀብረው፣ አንድነቷን ሸርሽረው ዛሬ ኢትዮጵያ ትኑር አትኑር ህልውናዋ አጠያያቂ የሆነበት ደረጃ ትገኝ ዘንድ ጠላቶቿ ለጊዜውም ቢሆን ተሳክቶላቸዋል፡፡
በጥቅሉ ‹‹የብርሃነ መስቀልና የታደለች ሕይወት በኢሕአፓ የትግል ታሪክ›› የሚያወሳው ‹‹ዳኛው ማነው›› የሚለው መጽሐፍ፣ የኢሕአፓን አንድ የታሪክ ገጽታ ስለሚዳስስ በርካታ ጉዳዮች ሊጻፉበት ይችላል፡፡ ስለኤርትራ ጉዳይ፣ ብርሃነ መስቀል የመጀመርያው የኢሕአፓ አስኳል በኤርትራ በረሃ በታገተበት ወቅት ወደ አውሮፓ ጉዞና በቀጣይነትም ከሻዕቢያ ጋር በምን ጉዳይ ቢስማሙ ነው ወደ አሲምባ ሊገቡ የቻሉት? በሌላ በኩል በመጽሐፉ ገጽ 170 እንደተቀመጠው፣
‹‹ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይና ዘርዑ ክህሸን ኤርትራ ሜዳ ሄደው፣ ከፓርቲው ፕሮግራም ውጪ ገና አቋም አልወሰድንም በሚል በፓርቲው ስም ያንን አወዛጋቢ ኮሚኔክ ፈርመዋል፡፡ ጉዳዩን ለምን እንዳደረጉ ግን በዚያን ወቅት በውል ማወቅ አልተቻለም፡፡››
እንደቀልድ የሚታለፍ አባባል አይደለም፡፡ እንደ መጽሐፉ አባባል ‹ዕውን ዘርዑ የተስፋዬን ደካማ ጎን ተገን አድርጎ ተጠቅሞበታል? አባባሎች ጠንከር ያለ ውይይት ቀስቃሾች፣ ብዕርና ወረቀት ፈላጊዎች ናቸው፡፡
አንዳንድ ነጥቦች
-
ከገጽ 246 እስከ 249 የተዘገበው የፍቅርተ ገብረ ማርያም፣ አበበች በቀለና አዳነች ፍሥሐዬ ከፓርቲው መዋቅር ውጭ ስለፓርቲው ጉዳይ ታደለችን ሊያናግሯት መምጣታቸውንና የተፈጠረውን ትርዕይት ሁሉም የተጠቀሱት ሴቶች በሕይወት አሉና የራሳቸውንና የሚያውቁትን ቢያስነብቡን መልካም ነው እላለሁ፡፡
-
ዳኛው ማነው መጽሐፍ እውነተኛ ታሪክ እንደመሆኑና በአጠቃላይ ትረካው ስም እየተጠቀሰ ሲሆን በገጽ 242 ‹‹የሴቶች እንቅስቃሴ›› በሚለው ምዕራፍ 14 ‹‹የህቡዕ እንቅስቃሴና ንትርክ›› ከገጽ 242 ላይ የተካተተው ፍሬ ሐሳብ ላይ ለምን ስም መጥቀሱ እንደተዘነጋ ግልጽ አይደለም፡፡
-
ገጽ 271 ፍቅሬ መርዕድ መስከረም 16 ቀን 1969 ዓ.ም. እንደተገደለ የተዘገበው መስከረም 21 ቀን 1969 ዓ.ም. መሆኑን መስከረም 23 ቀን 1969 ዓ.ም. የወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዘግቦታልና ይስተካከል፡፡
-
ገጽ 243 በቢቢሲ ዜና፣ በአውሮፓ የኢሕአፓ ተወካይ በሚል የተዘገበው ስሙ ቢጠቀስ መልካም ነበር
መደምደሚያ
አምባሳደር ታደለች ከስዊዘርላንድ አዲስ አበባ መርሐ ቤቴ ከርቸሌ የሕይወት ጉዞና ውጣ ውረድ ለታዋቂው ባለቤታቸው ብርሃነ መስቀል ረዳ ያላቸውን ፍቅርና ስሜት አስነብበውናል፡፡ ሁላችንም ስህተትን መቀበል የከበደን ዘመን ላይ ብንሆንም እሳቸውም በብርሃነ መስቀል በኩል የተሠሩ ስህተቶች እንዳሉ ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ በጥቅሉ ደግሞ ኢሕአፓ ከጠንካራ ጎኖቹ አኳያ ከድክመትም እንዳልፀዳ መቀበል ይኖርብናል፡፡ በተለይ በአመራር በኩል፡፡ ኢሕአፓ ታጋይ እንጂ አመራር የለውም፡፡ ይህ ችግር ለውድቀቱ የራሱ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ሁላችንም ፍፁም ልክ ነን ካልን ታዲያ የተሳሳተው ማነው?
ከሁሉም በላይ ይሉናል ወ/ሮ ታደለች፣ ‹‹ከሁሉም በላይ ፓርቲው ቢሳሳት፣ እነተስፋዬ ሊያርሙት ምንም አይቸግራቸውም ብዬ ነው የማስበው፡፡ እነብርሃነ ችግሩን አይተው ‹‹ስህተት እየተፈጸመ ነው›› ሲሉ፣ እነተስፋዬ በተቃራኒው ይቆማሉ የሚል እምነት አልነበረኝም፡፡ በተለይ ተስፋዬ ለብርሃነ የነበረው መልካም አስተሳሰብና ብርሃነ ለተስፋዬ የነበረውን አክብሮት ሳስበው፣ በምን ምክንያት ስለጉዳዩና ስለችግሮቹ መነጋገርና መፍትሔ መሻት እንዳቃታቸው ግራ ይሆንብኛል፡፡ ለምን እያልኩም አዘውትሬ ጠይቄዋለሁ›› (ገጽ 269፣ 270)፡፡ አባባል ሳነበው ዛሬ ላይ ሆነን ይህ ቢሆን ኖሮ የምንል በርካቶች ልንሆን እንደምችል ገመትኩ፡፡
የሆነው ሆኗል፣ ቀላል ያልተባለ ትውልድ ኢትዮጵያችን አጥታለች፡፡ የዚያ ዘመን ውጤት ዛሬም ያስከተለው መዘዝ ቀላል አይደለም፡፡ ሁላችንም ከስህተት ራሳችንን አፅድተን ወደፊት ለመጓዝ አልቻልንም፡፡ የተሠሩ ስህተቶችን በታሪክነታቸው ተቀብለን ለአገርና ለሕዝብ ሲባል በተለይ ደግሞ ለአሁኑና ለተተኪ ትውልድ ስንል መግባባትንና ብሔራዊ ዕርቅን ተግባራዊ አድርገን ብናሸልብ ይመረጣል፡፡ እንደተባላ ጀምሮ እንደተባላ ያለፈ ትውልድ አይሁን ታሪካችን፡፡ የዚያ ትውልድ አካላት ስለአገር፣ ስለሕዝብ ያለን አመለካከታችን፣ አካሄዳችን ተለያይቶ ለውድቀት አበቃን እንጂ ሁላችንም ኢትዮጵያችንና ሕዝባችንን እንወዳለንና ትውልድ ዕርቅን፣ ይቅር መባባልን ይቀጥልበት ዘንድ አርአያ እንሁን፡፡
የሸንበለል፣ ውበት (ማሚኩ) እና ሐቂ እናት፣ የስድስት ታዳጊዎች አያት፣ የኢሕአፓው መሥራች ብርሃነ መስቀል ረዳ ባለቤት የትናንቷ ጓዲት የዛሬዋ አምባሳደር ታደለች ኃይለ ሚካኤል ይህን መጽሐፍ በማስነበብዎ እንኳን ደስ አልዎት፡፡ ይህ አስተያየቴ ፖለቲከኛ ስለሆኑ እንደ ኢሕአፓ ትውልድ ታሪክ ተከላካይነት እንደሚመለከቱት ተስፋ ባደርግም ለልጆችዎ ግና ይከብዳል፡፡ የእርሶ ልጆች አባታቸውን አያውቁም፣ የተስፋዬ ደበሳይ ልጅ ሐምራዊት አባቷን አታውቅም፡፡ ለአንድ ዓላማ ተነስተው ታሪካቸው የተለያየው ወንድማማቾች ለልጆቻቸው አባት ናቸውና እኩል ስሜታቸው ይጎዳል፡፡ ይህ ሆኗል ከዚህ ታሪካችን ትውልድ ይማርበት ዘንድ ‹‹በእኛ ይብቃ›› ብለን ዳግም እንዳይደገም ጥሩውም ደካማውም ጎን አስተማሪነቱን እንቀበለው፡፡ ‹‹ዳኛው ማነው?›› ብለው ርዕስ ለሰጡት መጽሐፍዎ ለ17 ዓመታት በአገራችን ኢትዮጵያ ራሱ አሳሪ፣ ራሱ ከሳሽ፣ ራሱ ሕግ አውጪ፣ ራሱ ፈራጅ፣ ራሱ ገዳይ፣ ራሱ ቀባሪ ሆኖ አገሪቱን ያመሰቃቀለው ፋሺስትና አምባገነን መሪ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ይመራ የነበረው የደርግ ስብስብ ነበርና ‹‹ዳኛውማ ደርግ ነው›› ብያለሁ፡፡
ባለኝ ግንዛቤ የተሰማኝን ከራሴ አመለካከት አንፃር ሐሳቤን ስዘነዝር ከመጽሐፎ ያገኘኋቸው ቁምነገሮችና አሁንም በጥያቄ ያሉ ያልተመለሱ ምስጢሮች ውስጤ ተመላልሰዋል፡፡ እንደቆጨኝ ይዤ ያለሁት በጥቅሉ ‹‹ያ ትውልድ›› ላይ የተጠነሰሰው ቀደምት ሴራ ኢትዮጵያ ዛሬ ላለችበት አስከፊ አደጋ የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው ይሰማኛል፡፡ ኢሕአፓን አምነው፣ ዓላማው ዓላማቸው ሆኖ በንፁህ ፍቅርና እምነት ለምስኪኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመሬት ለአራሹ መፈክር ጀምሮ ለደሃ መማር፣ ነፃ የሕክምና አገልግሎት ማግኘት፣ ለዲሞክራሲያዊ መብትና ለሕዝብ መንግሥት ምሥረታ ሕይወታቸውን የሰጡ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆች ሁሌም ልናከብራቸው፣ ልናስባቸው ይገባል እላለሁ፡፡ ተምሮ ሥራ መያዝን አጥተውት ሳይሆን ቅድሚያ አገራችን፣ ሕዝባችን ብለው ነውና ድፍት ያሉት፣ አጥንታቸው ሊወጋን ይገባል፡፡
በተጨማሪ በኢሕአፓ አመራር እርከን ላይ የነበሩ አባላትና የሴቶች እህቶቻችን የነበሩበት የኑሮ ሁኔታ ሳስበው በአብዛኛው ለራሳቸው ከበቂ በላይ የተመቻቸላቸው ነበሩ፡፡ ማንነታቸውን ለአገርና ሕዝብ ሰጥተው እግራቸውን ለጠጠርና እሾህ፣ እምቡጥ ገላቸውን ለአረር ፀሐይና ለነጎድጓዳማ ዝናብ አሳልፈው ጨቋኝና በዝባዥ ሥርዓትን፣ አምባገነን አገዛዝን የተጋፈጡ እንስቶች እጅጉን ሊከበሩ ይገባል::
ይብቃኝ! ስለኢሕአፓ ሲወራ ያመኛል፣ ይነዝረኛል፣ በሚሰማኝ ኩራት ላይ ቁጭት ይወረኛል፡፡ አስከፋሁም አስደሰትኩም የምለውን ብያለሁ፡፡ ቸር ይግጠመን፡፡
ከአዘጋጁ፡– ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው nhsibhat@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡
ከሪፖርተር የተወሰደ

