ቅዱስ ሲኖዶስ: በምሥራቅ ጎጃም ቆጋ ምስካበ ቅዱሳን ኪዳነ ምሕረት ገዳም የተፈጸመውን ኢቀኖናዊ እና ኢሕጋዊ የጵጵስና እና የፕትርክና ሹመት ሻረ፤ እጃቸውን ያስገቡ ባዕዳን እንዲቆጠቡ አሳሰበ

• የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና በመጣስ እና ሕግን በመተላለፍ፣ ራሳቸውን በራሳቸው የሾሙ መነኰሳት፣ በቀኖና እንዲቀጡ ወሰነ፤ የቅስና ሥልጣናቸው እና ማዕርገ ምንኵስናቸው ተጠብቆላቸዋል፤
–
• “ኮሚቴ ነን” እያሉ የተወገዘውን የቅብዐት እምነት በቤተ ክርስቲያናችን ይዞታ እና ንብረት ለማደራጀት የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች፣ ከሕገ ወጥ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳሰበ፤
–
• ፕሮቴስታንታውያንና የተሐድሶ መናፍቃን፣ በገንዘብም ጭምር እንደሚደግፉት በማስረጃ በመረጋገጡ፣ ከጣልቃ ገብነት እጃቸውን እንዲሰበስቡ አስጠነቀቀ፤
–
• በአንዲት ቤተ ክርስቲያን በአንድ ሃይማኖት እና በአንድ ካህን የምትፈጸመው ጥምቀት አንዲት በመኾኗ፣ “ዳግም ጥምቀት” በሚል የሚደረገው እንቅስቃሴ እንዲቆም አዘዘ፤
–
• ሀገረ ስብከቱ፣ ኦርቶዶክሳዊውን የነገረ ክርስቶስ(ነገረ ሥጋዌ) አስተምህሮ፣ በልዩ እና ተከታታይ የስብከተ ወንጌል ጉባኤያት እንዲሁም የትምህርተ ወንጌል እና የሥልጠና መርሐ ግብሮች እንዲያጠናክር እና እንዲያጸና መመሪያ ሰጠ፤
–
• ሕገ ወጦቹን ተሿሚዎች እና ግብረ አበሮቻቸውን በማጋለጥ እና በመቆጣጠር ትብብር ያደረጉ፣ የሀገረ ስብከቱን አድባራት እና ገዳማት፣ ምእመናንና የመንግሥት አካላት አመሰገነ፡፡
–


