–
የትግራይ ህዝብ በዚህ ግለሰባዊ አምባገነናዊ ሃይልና ሸሪኮቹ የሚደርሱብህን ቁጥር ስፍር የሌላቸው በደሎች “ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ” በሚል አስተዋይ አካሄድ አገርን ለማዳን ስትል እላፊ ዋጋና መስዋእትነት እየከፈልክ እንደምትገኝ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ትእግስትህን ሊረዱ የማይችሉ አዳዲስ ግልሰባዊ አምባገነኖች ማባሪያ የሌለው ግፍ፣ አድልዎና ግፊት እየፈፀሙብህ ይገኛሉ፡፡ ስለሆነም በደህንነትህና ህልውናህ ላይ ያንዣበበው ተጨባጭ አደጋ በዚህ ሁኔታ ሊቀጥል እንደማይችልና እንደማይገባ ተገንዝበህ እንደወትሮህ ሁሉ ጠላቶችህን ዳግም ለመመከትና ደማቅ ታሪክ ለመስራት ከፍተኛ ዝግጅት እንድታደርግ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
–

የትግራይ ህዝብ በህጉ መሰረት የሚገባው በጀትም ሆነ ሌሎች ድጋፎች ከግለሰባዊ አምባገነን ሃይል ኪስ የሚሰጠው ሳይሆን ከራሱ ከትግራይ ህዝብ በግብርና በቀረጥ የተሰበሰበና በበጀት መልክ ተሸንሽኖ የሚሰጠው ህጋዊ ድርሻው መሆኑ ታውቆ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የትግራይ በጀት ሊለቀቅ ይገባል፡፡ ይህ ህገወጥ ሃይል የትግራይን ህዝብ ህገመንግስታዊ መብት በመጣስ በጀት የሚቆርጥም ሆን የሚያቀርጥ ከሆነ በቀጥታ ጦርነት ማወጅ በመሆኑ፤ በውጤቱ ለሚፈጠር ማንኛውም ዓይነት ሁኔታ ብቸኛው ተጠያቂ በስልጣን ላይ ያለው ህገወጥ፣ አሃዳዊ ግለሰባዊ አምባገነን ሃይል ነው፡፡
–
ይህ በስልጣን ላይ የሚገኝ ህገወጥ ሃይል ዓለማቀፋዊ ቃልኪዳኖችንና ግዴታዎችን በመጣስ ከዓለማቀፍ ምግባረ ሰናይ ተቋማት የተገኘ የምግብ ዋስትና እርዳታን ሳይቀር ለፖለቲካዊ ዓላማው ማራመጃ እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡ ስለዚህ የተባበሩት የዓለም መንግስታት ድርጅትና ኤጀንሲዎቹ እንዲሁም ዓለማቀፍ ምግባረ ሰናይ ተቋማት ለምግብ ዋስትናና ለሰብዓዊ እርዳታ የለገሳችሁት እርዳታ ለህገወጥ አሃዳዊና ግለሰባዊ አምባገነን ሃይል ፖለቲካ መሳርያና ለትግራይ ህዝብን መጨቆኛ እየዋለ መሆኑን አውቃችሁ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል እንድትቆጣጠሩ፤ ህገወጡ ሃይልም ዓለማቀፍ የሰብዓዊነት መርሆዎችን በመጣሱ ተጠያቂ ልታደርጉ ይገባል፡፡ የዓለም ማህበረሰብ፣ አህጉራዊና ዓለማቀፍ ተቋማት፣ በኢትዮጵያ የምትገኙ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ይህች ሃገር ወደ እርስ በርስ ጦርነትና መበታተን ካመራች ቀጠናዊ፣ አህጉራዊና ዓለማቀፋዊ መዘዙ እጅግ ከባድ መሆኑን ተረድታችሁ ሃገርን በማዳን እንቅስቃሴው ላይ ህጋዊና ሞራላዊ ግዴታችሁን ልትወጡ ይገባል፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ በዚች ሃገር ለሚያጋጥመው ቀውስና መበታተን ከታሪካዊና ሞራላዊ ተጠያቂነት ማምለጥ አትችሉም፡፡
