November 1, 2020

(ኢዜአ)

 በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ግጭቶች በአንድ ማኅበረሰብ ላይ ያተኮሩ ቢመስሉም አገር የማተራመስ ዕቅዶች በመሆናቸው በጋራ መመከት ይገባል ተባለ።

በአገራዊ ሠላምና ወቅታዊ የፖለቲካዊ ጉዳዮች ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፖለቲካ ምሁራንና ፖለቲከኞች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቷ የሚታዩ ሕገወጥ ተግባራት አገር ለማተራመስ የታቀዱ ሴራዎች ስለመሆናቸው ይስማማሉ።

የነፀብራቅ አማራ ድርጅት ሊቀ መንበር አቶ ቸርነት አንዳርጌ ግጭቶቹና የሰው ሕይወት የማጥፋት ድርጊቶቹ ብሄር ተኮር ቢመስሉም ዓላማቸው ‘አገር ማተራመስ ነው’ ይላሉ።

እነዚህ ድርጊቶች ሲያጋጥሙ የእኔ ብሄር አልተነካም ብሎ ዝም ማለት የዋህነት ነው ያሉት አቶ ቸርነት ድርጊቶቹን ከወዲሁ ልናስቆማቸው ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ሠላም ማጣት የሚያተርፉ ቡድኖች በማኅበረሰቡ ውስጥ መኖራቸውንና ሕዝቡም እንደሚያውቃቸው የተናገሩት ደግሞ ፖለቲከኛው ዶክተር አንጋሳ አህመድ ናቸው።

በመሆኑን ሕዝቡ ሕገወጥ ግለሰቦችም ይሁን ቡድኖችን በጋራ መከላከል አለበት ነው ያሉት።

ግጭቶችን ለማስቆም በችግሮቻችን ዙሪያ የመወያየት ልምድ ማዳበርና በሠላማዊ መንገድ የመፍታት ባህልን ማሳደግ ይገባናል ያሉት ደግሞ ዶክተር አንዳርጌ ታዬ ናቸው።

ችግሮችና ቅሬታዎችን በንግግር ለመፍታት እየተጀመሩ ያሉ ብሄራዊ ምክክሮች ሊጠናከሩ እንደሚገባም አመልክተዋል።

የፖለቲካ ምሁሩ ዶክተር ዲማ ነገዎ በበኩላቸው በርካታ ችግሮችን አልፈው ወደ ዴሞክራሲ ስርዓት ለሚገቡ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገራት የሚያስፈልገው ሁሉን አቀፍ ምክክርና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ነው ይላሉ።

በኢትዮጵያ ሠላም ለማስፈንና ለማንም የማይወግን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባትም ዜጎች በ’ያገባኛል’ ስሜት መሳተፍ እንዳለባቸው ተናግረዋል።