November 2, 2020

ጎበዜ ሲሳይ ( ESAT ጋዜጠኛ)

በዚህ ሌሊት መርዶ ነጋሪ ባልሆን ደስ ይለኝ ነበር ። ግን ከስፍራው በስልክ የሚመጣልኝ መልእክት እንቅልፍ የሚነሳ ነው። በየጫካው የልቅሶ ድምጽ ከአውሬ ድምጽ ጋር ተቀላቅሎ ይሰማኛል። ሸሽተው ወደጫካ የገቡት ሰዎች በሹክሹክታ ነው የሚያወሩኝ ። የፈሩት አውሬውን ሳይሆን ኦነግ ሸኔን ነው።

እባካችሁ ለወሬ ነጋሪ አትርፉን ሲሉ መተኛት አልቻልኩም። በአይናቸው ያዩት ሲነግሩኝ የሟቾቹን ቁጥር ከ200 በላይ ያደርሱታል። ይህን ቁጥር ለመጥቀስ እኔ ፈራሁ ግን እንሱ አሉ ።

የመከላከያ ሃይል ቅዳሜ አካባቢውን ለቆ ሲወጣ ህዝቡ ገላችሁን ሂዱ ወይም ይዛችሁን ሂዱ ብለው የመከላከያ ተሽከርካሪ (ኦራል) አግደው እንደነበር ተናግረዋል።

“መከላከያም ታዘን ነው የወጣነው” በሚል አጭር መልስ ሰጥቶ ጥሎ ወጣ ነው የሚሉት። የእለቱ እለት ኦነግ ሸኔ በመከላከያ እግር ገብቶ ዛሬ የቀበሌውን ህዝብ ለስብሰባ እፈልጋችኋለሁ ብሎ የተኩስ እሩምታ በመክፈት ከ200 በላይ ህዝብ እንደገደለ ነው የሚናገሩት።