ባለቤትነታቸውን ማረጋገጥ ያልተቻለ የታጠሩ ቦታዎች፣ ጅምር ግንባታዎች፣ ቤቶችና ህንፃዎች ሕጋዊ ባለቤት ነኝ የሚል አካል ወይም ግለሰብ ካለ ለዚሁ ጉዳይ በየክፍለ ከተማው በተዋቀረ ግብርኃይል ዘንድ በመቅረብ ሪፖርት እንዲያደርግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አሳሰበ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህገ-ወጥ የመሬት ወረራና ህገ-ወጥ ግንባታ ጋር ተያይዞ በየደረጃው በተዋቀረ ግብረሃይል ከአንድ ወር በላይ አደረኩት ባለው የማጣራት ሥራ ብዙ ግኝቶችን ማግኘቱን አስታውቋል።
ግኝቶቹም፦
1ኛ – በህገ-ወጥ መንገድ የታጠሩ እና ባለቤትነታቸውን ማረጋገጥ ያልተቻለ ቦታዎች መኖራቸው
2ኛ – በህገ-ወጥ መንገድ መገንባት የተጀመሩ ግንባታዎች መኖራቸው፤
3ኛ – ባለቤቶቻቸው ያልታወቁ ቤቶች እና ህንፃዎች መገኘታቸውን የአጣሪ ኮሚቴው ደርሶባቸዋል ብሏል፡፡
ግኝቶቹ በየክፍለ ከተማው እና በየወረዳው ከነገ ጀምሮ ስለሚለጠፍ ህጋዊ ማስረጃ አለኝ፤ የሚል አካልም ሆነ ግለሰብ ካለ ከነገ ጥቅምት 23/02/2013 ጀምሮ ለ3 ተከታታይ ቀናት የሚቀርብ መረጃም ሆነ ማስረጃ በመያዝ ለዚሁ ጉዳይ በየክፍለ ከተማው በተዋቀረ ግብረሃይል ጋር በመቅረብ እንዲያስረዳ የከተማ አስተዳድሩ በጥብቅ አሳስቧል፡፡
ሆኖም ግን ይህ ሳይሆን ቀርቶ በተጠቀሱት ቀናቶች ውስጥ ማስረጃውንም ሆነ መረጃውን ሳይቀርብ የሚገኝ እንደሆነ ከተማ አስተዳደሩ አስተዳደራዊም ሆነ ህጋዊ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን በአፅንኦት ሰጥቶ ገልጿል ፡፡
ይህን ጉዳይ አስመልክቶ ዝርዘር መረጃው ከነገ ጥቅምት 23/02/2013 ጀምሮ በየክፍለ ከተማው እና በየወረዳው የሚለጠፍ መሆኑን በድጋሚ እየገለፅን ተጨማሪ የመሬት ወረራና ህገ ወጥ ግንባታን አስመልክቶ ተጨባጭ ጥቆማ ያለው ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ተቋም አበረታታለሁም ብሏል፡፡
አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕሬስ ሴክሬታሪያተ ጽ/ቤት
