የአማራን ክልል በሚያዋስነው የምዕራብ ትግራይ ድንበር በኩል ግጭቶች እንዳሉ የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ገለፁ።
ለሁለት ቀናት ያህል በቀጠለው የትግራይና የፌደራል መንግሥት ግጭትን አስመልክቶ በዛሬው ዕለት ለትግራይ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ ነው ይህንን ያሳወቁት።
ደብረፅዮን (ዶ/ር) ውጊያው የአማራ ክልል በሚያዋስነው ድንበር አካባቢ ቀጥሏል ከማለታቸው ውጭ የትኛው ግዛት (ግዛቶች) እንደሆኑ አልጠቀሱም።
የአማራ ልዩ ኃይልና የፌደራል ሰራዊቱ በጥምረት በመሆን የትግራይ ኃይል ጋር በትናንትናው ዕለት ጥቅምት 25/ 2013 ዓ.ም መዋጋታቸውን ተናግረዋል።
የትግራይ ኃይል በክልሉ የሚገኙትን የመከላከያ ሰሜን ዕዝ ጦር መሳሪያም ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር አውሏል ብለዋል።
“ትግራይ በሚገኙ የጦር መሳሪያዎች የትግራይ ህዝብ ጥቃት ሊፈፀምበት አይገባም። አሁን በሙሉ ታጥቀናል። በጦር መሳሪያ ከነሱ ያነስን አይደለንም፤ ምናልባት የተሻልን ነን” ብለዋል በመግለጫቸው
በተጨማሪም ድንበር አካባቢ ሰፍረው የነበሩ የተወሰኑ መከላከያ ሰራዊት አባላት በአዲያቦ በኩል አድርገው ወደ ኤርትራ ድንበር ተሻግረዋል ያሉት ፕሬዚዳንቱ ይህም “ያላቸውን ግንኙነት ያሳየ ነው” በማለት አስረድተዋል።
የሰራዊት አባላቱ ትግራይ ክልል ከሚቆዩ ወደ ኤርትራ እንዲሻገሩም ትዕዛዝ ተሰጥቷቸውም ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በትናንትናው ዕለት ጥቅምት 25/2013 ዓ.ም ማምሻቸውን በሰጡት መግለጫ በሁመራ፣ በዳንሻ እና በቅርቃር አካባቢዎች የአገር መከላከያ ሠራዊት እና የአማራ ክልል ልዩ ኃይልና ሚሊሻ “ሕወሓት ያሻውን ሳያደርግ የሞከራቸው ሙከራዎች ከሽፈዋል” ብለዋል።
የአገር መከላከያ ሠራዊትም “የተቃጣበትን ጥቃት በመመከት እንዲሁም በማክሸፍ የሕዝቦችን ደህንነት እና የአገሪቱን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ ኃላፊነቱን እየተወጣ” እንደሆነ ገልፀዋል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሻከረ የመጣው የፌደራልና የትግራይ ክልል መንግሥት ግንኙነት የማይታረቅ ደረጃ ደርሶ በትናንትናው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ህወሃት በትግራይ የሚገኘው የመከላካያ ካምፕ ላይ ጥቃት ማድረሱን ገልፀው ጦርነት መከፈቱን አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው የመከላከያ ሠራዊት በኮማንድ ፖስት እየተመራ “ሀገሩን የማዳን ተልዕኮውን እንዲወጣ ትእዛዝ ተሰጥቶታል” ብለዋል።
በትግራይና በፌደራል መንግሥት ያለውን ግጭት ተከትሎ በትግራይ ክልል የስልክና ኢንተርኔት አገልግሎት እንደተቋረጠ ነው። የመብራት አገልግሎትም አለመኖሩን መቀሌ የሚገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ ገልጿል።
በከተማዋ ውስጥ ያሉ ባንኮችም ዝግ ሲሆኑ ነዋሪው ከትናንት በተሻለ ሁኔታ ከተማዋ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ታዝቧል።
ከዚህም በተጨማሪ መቀሌ የሚገኙ የንግድ ተቋማትና የገበያ ማዕከላትም አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ ብሏል።
ቢቢሲ