FanaBC

On Nov 5, 2020

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያና  እስራኤል  በመረጃና ደህንነት  ዘርፍ  ተባብረው  ለመሥራት  ስምምነት ላይ መድረሳቸውን  የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት  አስታውቋል ።

የእስራኤል ደህንነት ምክትል ሚኒስትር  ጋዲ ይቫርካን  ከብሄራዊ  መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር  ጄነራል ኮሚሽነር  ደምላሽ ገብረ ሚካኤል ጋር  ተገናኝተው  ውይይት አድርገዋል ።

በውይይታቸውም ሁለቱ አገራት  በአፍሪካ  ቀንድ ሽብርተኝነትን በጋራ ለመዋጋት፣ የመረጃ  ልውውጥ ለማድረግ ፣ በቴክኖሎጂ  ሽግግር እንዲሁም  በአቅም ግንባታ  ዘርፍ  ይበልጥ   ተባብረው ለመሥራት   መስማማታቸውን  ገልጸዋል ።

የብሄራዊ  መረጃና ደህንነት  አገልግሎት  ዳይሬክተር ጀኔራል ኮሚሽነር  ደምላሽ  ገብረሚካኤል በውይይቱ  ወቅት ÷  ኢትዮጵያና  እስራኤል  በመረጃና  ደህንነት ዘርፉ ተባብረው  ቢሰሩ  በአፍሪካ  ቀንድና አካባቢው  ሰላምና መራጋጋት በማጠናከር በኩል  ትልቅ አስተዋጽኦ  ሊያበረክቱ  ይችላሉ ብለዋል ።

የእስራኤል  ደህንነት  ምክትል ሚኒስትር ጋዲ  ይቫርካን በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ  በአፍሪካ  ቀንድ ቀጣና  ሰላምና መረጋጋት  በማስፈን  ረገድ  ትልቅ ሚና  ያላትና ተሰሚ  በመሆኗ  ምክንያት   እስራኤል  ከኢትዮጵያ  ጋር በመረጃና ደህንነት  ዘርፉ  ያላትን ትብብር  ይበልጥ ማጠናከር  እንደምትፈልግ  ገልጸዋል ።

ኢትዮጵያ  በመረጃ  ዘርፍ  የጀመረችውን  ለውጥ  እስራኤል   እንደምትደግፍም  ምክትል ሚኒስትር ጋዲ  ይቫርካን  ተናግረዋል ።

ኢትዮጵያና እስራኤልም በመረጃና ደህንነት ዘርፍ በጋራ  ለመሥራት  የደረሱትን  ስምምነት  በቅርቡ   ወደ ተግባር  ይሸጋገራል ተብሎ እንደሚጠበቅም  ብሄራዊ  መረጃና ደህንነት  አገልግሎት  የላከው  መረጃ አመልክቷል ።