November 5, 2020

ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶክተር)

የአማራን ክልል በሚያዋስነው የምዕራብ ትግራይ ድንበር በኩል ግጭቶች እንዳሉ የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ገለፁ።

ለሁለት ቀናት ያህል በቀጠለው የትግራይና የፌደራል መንግሥት ግጭትን አስመልክቶ በዛሬው ዕለት በትግራይ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ ነው ይህንን ያሳወቁት።

የአማራ ልዩ ኃይልና የፌደራል ሰራዊቱ በጥምረት በመሆን የትግራይ ኃይል ጋር በትናንትናው ዕለት ጥቅምት 25/ 2013 ዓ.ም መዋጋታቸውን ተናግረዋል።

የትግራይ ኃይል በክልሉ የሚገኙትን የመከላከያ ሰሜን ዕዝ ጦር መሳሪያም ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር አውሏል ብለዋል።

“ትግራይ በሚገኙ የጦር መሳሪያዎች የትግራይ ህዝብ ጥቃት ሊፈፀምበት አይገባም። አሁን በሙሉ ታጥቀናል። በጦር መሳሪያ ከነሱ ያነስን አይደለንም፤ ምናልባት የተሻልን ነን” ብለዋል በመግለጫቸው

በትናንትናው ዕለት ጥቅምት 25/2013 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ማምሻቸውን በሰጡት መግለጫ በሁመራ፣ በዳንሻ እና በቅርቃር አካባቢዎች የአገር መከላከያ ሠራዊት እና የአማራ ክልል ልዩ ኃይልና ሚሊሻ “ሕወሓት ያሻውን ሳያደርግ የሞከራቸው ሙከራዎች ከሽፈዋል” ብለዋል።

በትግራይና በፌደራል መንግሥት ያለውን ግጭት ተከትሎ በትግራይ ክልል የስልክና ኢንተርኔት አገልግሎት እንደተቋረጠ ነው። የመብራት አገልግሎትም አለመኖሩን መቀሌ የሚገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ ገልጿል።

በከተማዋ ውስጥ ያሉ ባንኮችም ዝግ ሲሆኑ ነዋሪው ከትናንት በተሻለ ሁኔታ ከተማዋ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ታዝቧል።

ከዚህም በተጨማሪ መቀሌ የሚገኙ የንግድ ተቋማትና የገበያ ማዕከላትም አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ ብሏል።

https://bbc.in/3l3dGbP