November 6, 2020

ዋዜማ – የትግራይ ተወላጆች የሆኑ የብሄራዊ ጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ሠራተኞች በግዳጅ ዕረፍት እንዲወስዱ እንደተደረጉ ዋዜማ ሰምታለች፡፡ በተያያዘ፣ በአውሮፕላን ወደ ውጪ ሀገራት ጉዞ የነበራቸው የትግራይ ተወላጅ መንገደኞች መታወቂያቸው እየታየ እና ብሄራቸውን እየተጠየቁ ከጉዟቸው እንዲቀሩ እና ወደቤታቸው እንዲመለሱ መደረጋቸውን ዋዜማ ድርጊቱ ተፈጽሞብናል ካሉ ምንጮች ሰምታለች፡፡ ዋዜማ በጉዳዩ ላይ የመንግሥትን አስተያየት ለማግኘት እየሞከረች ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በሱማሊያ ከአፍሪካ ኅብረት ማዕቀፍ ውጭ በተናጥል የሠፈሩ ወታደሮቹን ማስወጣት እንደጀመረ ዋዜማ ከአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ሃይል ምንጮቿ ሰምታለች፡፡ ወታደሮቹ የተጠሩት የሀገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ከትግራይ ክልል ጸጥታ ሃይል ጋር የገባበትን ግጭት እንዲያግዙ ነው፡፡ ከባድ ጦር መሳሪያ የታጠቁ ወታደሮች የኢትዮጵያ አዋሳኝ ወደሆነችው የሱማሊያዋ ጌዶ ግዛት ተመልሰዋል፡፡ በተያያዘ፣ የሱማሌ ክልል ልዩ ሃይል ወደ ኢትዮጵያ-ሱማሊያ ድንበር ተጠግቶ ድንበር እየጠበቀ እንደሆነ ታውቋል፡፡

በመከላከያ ሠራዊት እና በትግራይ ክልል ታጣቂዎች ሃይሎች መካከል የተቀሰቀሰውን ግጭት ለማስቆም አፍሪካ ኅብረት ከመጋረጃ ጀርባ የጀመረውን የዲፕሎማሲ ጥረት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ እንዳልተቀበሉ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ በተያያዘ፣ ከዛሬ ጧት ጀምሮ በትግራይ-አማራ ድንበር የመድፍ እና ጥይት ተኩስ ይሰማ እንደነበር እና በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ በአብደራፊ ከተማ 24 ያህል ቁስለኛ ወታደሮች ሕክምና ሲሰጣቸው ምንጮች መመልከታቸውን ሮይተርስ ጨምሮ ጠቅሷል፡፡ ቁስለኞቹ ከየትኛው ወገን እንደሆኑ ግን ምንጮች ማረጋገጥ አልቻሉም ብሏል፡፡ ዋዜማ