November 6, 2020

ህወሓት ሀገራዊ መግባባት የሚፈጥሩ እድሎችን በሙሉ ዘግቶ ጦርነትን እንደተሻለ አማራጭ መጠቀሙ ትልቅ ጥፋት መሆኑን” የኦሮሞ ነጻነት ግንባር(ኦነግ) ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ቀጄላ መርዳሳ አስታወቁ ።

አቶ ቀጄላ መርዳሳ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በተለይ እንደገለጹት ፣ ህወሓት ሀገራዊ መግባባትን የሚፈጥሩ እድሎችን በሙሉ ዘግቶ ጦርነትን እንደተሻለ አማራጭ አድርጎ መጠቀሙ ትልቅ ጥፋት ነው። በድፍረት የጀመረው ጦርነት ለየትኛውም ወገን አይጠቅምም ።የትግራይ ክልል ቀደም ሲልም የጦርነት ቀጣና በመሆን የአካባቢው ማህበረሰብ ህይወት ሲታወክ ነበር ያሉት ኃላፊው ፣አሁንም ህዝቦችን በጸጥታ ችግር ማወክና ለስደት መዳረግ አስፈላጊ አልነበረም ብለዋል።

አካባቢውን የጦርነት ቀጠና ማድረግ በነዋሪዎች ቤት ላይ እሳት እንደመለኮስ ይቆጠራል ያሉት ኃላፊው፣ በተለይም ለህዝቤ ቆሜያለው ያለው ህወሓት ህዝቡን ሰላምና ጸጥታ ከሚያደፈርስ ተግባር ሊቆጠብ ይገባው ነበር ብለዋል።

“ህወሓት የሀገር መከላከያ ሰራዊትን እንደራሱ ወገን ከመመልከት ይልቅ እንደጠላት ተመልክቶ ጥቃት መሰንዘሩ ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ነው። በጦርነቱ የትኛውም አካል ቢያጠቃ ሀገሪቱ የምታተርፈው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስን ብቻ ነው”ብለዋል ።

ህወሓት ጦርነት የጀመረው ትኩረት ለመሳብና ድርድር ለማድረግ እንዲያመቸው በማሰብ ሊሆን ይችላል ያሉት አቶ ቀጄላ ፣አሁንም የከፋ ጉዳት ሳይደርስ በሁለቱም በኩል ሰላማዊ ንግግር የሚደረግባቸውን መንገዶች ቢያስቡ ይመረጣል ብለዋል።

ህወሓት ሁለት ዓመት ሙሉ የጦርነት ዝግጅት ሲያደርግ እንደነበር በመጥቀስ የፌዴራል መንግሥት በድንገት የገባበት ጦርነት መሆኑንም ጠቅሰዋል። በዚህም ጦርነቱ ሊራዘም እንደሚችልና በዘንድሮው ዓመት ይካሄዳል የተባለው አገራዊ ምርጫ ሊደናቀፍ እንደሚችል ፤ መንግሥት ከውጭ የሚሰነዘር ጥቃት ቢገጥመው የመመከት ኃይሉ ሊዳከም እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

“ህወሓት ከሁለት ዓመት በፊት በሀገሪቱ መንግሥት ውስጥ የነበረው ሚና እየቀነሰ ሲመጣ ያጣውን ስልጣን ለማግኘት ሲል የቀየሰው ስትራቴጂ እንደሆነ አመልክተው፣ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩት ግጭቶች የህወሓት ድጋፍ ያላቸው እንደሆኑ የሚመላክቱ ነገሮች አሉ ብለዋል ።

መንግሥት ጦርነቱን በአጭር ጊዜ በበላይነት ማጠናቀቅ ከቻለ የችግሮች ምንጭ ስለሚወገዱ በየጊዜው በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ግጭቶች ይቀንሳሉ፤ የውጭ ጥቃትን ለመመከት የሚያስችል አቋምም ሊጠናከር እንደሚችል ጠቁመዋል። ህዝቡ በጦርነቱ ሳይሸበር በተረጋጋ መንፈስ አካባቢውን እየተቆጣጠረ የተለመደ ሥራውን መስራት እንደሚገባውም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ምንጭ፦ አዲስ ዘመን – EPA/ኢፕድ