
8 November 2020
ጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም. የተጀመረውን የስምንተኛና የ12ኛ ክፍል የገጽ ለገጽ ትምህርት በመቀጠል፣ ሁሉም ክፍሎች ሰኞ ጥቅምት 30 እንደሚጀምሩ ተወስኖ የነበረ ቢሆንም፣ የተማሪዎቹ የገጽ ለገጽ ትምህርት ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡
ይህ ውሳኔ በመማር ላይ የሚገኙትን የስምንተኛና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የማይመለከት መሆኑን ትምህርት ቢሮው ገልጾ፣ የኮሮና ወረርሽኝ ለመከላከል የሚያስችሉ መሥፈርቶች በሁሉም ትምህርት ቤቶች ተሟልተው እስከሚጠናቀቁ ትምህርት እንደማይጀመር ጠቁሟል፡፡
ከስምንተኛና ከ12ኛ ክፍል ውጪ በተቀሩት ክፍሎች ትምህርት የሚጀመረው፣ በኮቪድ-19 የቀውስ ጊዜ የትምህርት አመራርና አስተዳደር ስትራቴጂ ዕቅድ ላይ የተቀመጡ መሥፈርቶች በሁሉም ትምህርት ቤቶች ተሟልተው ሲጠናቀቁ በመሆኑ፣ ትምህርት ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟልም ተብሏል፡፡
ትምህርትን ለማስጀመር ወሳኝ ከሆኑት አንዱ የሆነው የመምህራን መሟላት ሲሆን፣ በዘርፉ እጥረት መኖሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በአዲስ አበባ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የመምህራን እጥረት ገጥሟል፡፡ በከተማዋ ለሚገኙ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች 1,448 ተጨማሪ መምህራን ለመቅጠር ቢሮው ማስታወቂያ አውጥቷል፡፡
ይህ የመምህራን እጥረት የግል ትምህርት ቤቶች ችግር መሆኑንም ሪፖርተር ያነጋገራቸው ትምህርት ቤቶች ርዕሳነ መምህራን ተናግረዋል፡፡ ለመቀጠር ከሚመጡ አመልካቾች በእጃቸው የሚገባው ደመወዝ 20 ሺሕ ብር እንዲሆን የሚጠይቁ መኖራቸውን፣ ዝቅተኛ የሚጠይቁት ክፍያ ስምንት ሺሕ ብር መሆኑንና ይህም በተለይ ቤት ተከራተው ለሚያስተምሩ የግል ትምህርት ቤቶች ከአቅም በላይ እንደሆነ የግሎሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ቴዎድሮስ ተሾመ አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር በበኩሉ መምህራን ከትምህርት ቤቶች አቅም በላይ ባለመጠየቅ፣ ይህንን የችግር ጊዜ ድርብ ኃላፊነት በመወጣት ከሕዝቡ ጋር አብረው እንዲሆኑ ጥሪ አቅርቧል፡፡