
የተጀመረውን ጦርነት አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ !
******//******
ጦርነት በወንድማማች እና እህትማማች ሕዝቦች መሀል የተከሰተ ልዩነትን ለመፍታት ተመራጭ መንገድ ባይሆንም ሁኔታዎች ወደተካረረ ደረጃ ላይ ሲደርሱ አይቀሬ ይሆናል፡፡ ከውጭ ከሚመጣ ወራሪ ጦር ጋር የሚደረግ ጦርነት የቱንም ያህል የሰውና የንብረት ኪሳራ ቢያስከትልም ውጤቱ ነፃነት ሲሆን ተጋድሎው ለትውልድ የሚተላለፍ ኩራት ይሆናል፡፡ የእርስ-በእርስ ጦርነት በምንም መመዘኛ ቢታይ የኩራት ምንጭ አይሆንም፡፡
እንዲያውም አንገት የሚያስደፋ እና ጸጸትን የሚወልድ ተግባር ነው፡፡ እንግዲህ ኢትዮጵያ ወደዚህ መራር እውነታ ጫፍ ተገፍታለች፤ የጦርነት መጀመርን ዜናም ሰምተናል፡፡ ጦርነቱ በትዕቢተኛው ሕወሃት ታጣቂ ሃይሎች ትንኮሳ የተጀመረ መሆኑም ታውቋል፤ በዚህ ጦርነት የሚወድቁት ሁሉ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ እንደሚታወቀው በጦርነት የሚጎዱት ጦርነት ናፋቂዎችና ለኳሾች አይደሉም፤- ሕዝቡ እንጂ! የመከላከያ ሠራዊት አባላትም ይሁኑ ሕወሓት ያሰለፋቸው ሃይላት የኢትዮጵያ ሕዝብ ልጆች ናቸው፤ የሚጎዱትም እነርሱና በጦርነቱ ቀጠናዎች አካባቢ ያለው ንፁህ ሕዝብ ነው፡፡
እንግዲህ የመጀመሪያዋ የጦርነት ማስጀመሪያ ጥይት ስትተኮስ ሁኔታው ፈሩን ስቶ ሰላም ደፍርሷል፤ የደፈረሰ ነገር ደግሞ ካልጠራ ሰላም የለም፡፡ ሰላማችን ሕገ-ወጡ ቡድን ባሰማራቸው ታጣቂዎች በየአካባቢው በሚተኮሱ ጥይቶችና በሚወረወሩ ቦንቦች ምክንያት በተፈጠሩ ትናንሽ ጥቃቶች ከደፈረሰ ረጅም ጊዜ አስቆጥሯል፤ የበርካታ ዜጎቻችንን ሕይወት ቀጥፏል፤ የሕዝቡም ሕይወት ተበጥብጧል፤ ዛሬ ግን ለይቶለት ወደ መደበኛ ጦርነት አድጓል፡፡
በወንጀለኛው ቡድን የተጀመረው ጦርነት ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ኪሳራ ሳያበዛ መጠናቀቅ ይኖርበታል፡፡ እስከአሁን የተደረገው ጦርነት የቀጠፋቸውን ኢትዮጵያውያንን ማሰብ ያማል፤ በጦርነቱ ድምጸት የደነገጡ ልጆችን ማሰብ ያሳዝናል፣ የእናትና የአባቶቻቸውን ጭንቀት አረጋውያኑንና ህሙማኑን ማሰቡም ይከብዳል፡፡ በአጠቃላይ ጎስቃላው ሕዝብ የሚካፈለው ኢትዮጵያ አስመዘገበች ከሚባለው ዕድገት ሳይሆን ከችግሯ በመሆኑ እንደሀገር እንድናፍር ያደርገናል፡፡ ያም ሆነ ይህ፣ ወደድንም ጠላን፣ ፈለግንም አልፈለግን ጦርነቱ ተጀምሯል፡፡ ጦርነቱ ብዙ ጉዳት ሳያስከትል ማለቅ አለበት፡፡ የውስጥ ችግራችንን ውጠን እና ሁልጊዜም የምናሰማቸውን ብሶቶች ያዝ አድርገን ከመንግሥትና ከሕዝብ ጎን መቆም ግድ ይለናል፡፡
ከዚህ ክፉ አጋጣሚ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚደረግን ሩጫ በፍጹም ማየት አንፈልግም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! ጦርነት የሚካሄደው በጦር ግንባር ብቻ ያለመሆኑን በማሰብ ከማንኛውም ከይሲ እንቅስቃሴ ራስህን ልትጠብቅ ይገባል፡፡ አሁን ጦርነቱ በተጀመረበት ቀጠና አካባቢ የምትገኙ የትግራይና የአማራ ሕዝብ ሆይ፤ መተሳሰብና አብሮነታችሁን ለሚፈትን እኩይ ቅስቀሳ ሳትበገሩ መንፈሳዊ አንድነታችሁን ጠብቁ፡፡
የዘርና የሃይማኖት ጥቃት በሚዘወተርባቸው አካባቢዎች የምትገኙ ኢትዮጵያውያን በአካባቢያችሁ ከሚገኙ የመንግሥት ሃይላት ጋር በመሆን አካባቢያችሁን የመጠበቅ ሃላፊነት አለባችሁ፡፡ ኢሕአፓ ይህ አስከፊ ጦርነት በአጭሩ እንዲገታ ይመኛል፡፡ ኢሕአፓ ሕዝብን እና ሀገርን ለመታደግ ለመከላከያ ሠራዊትና ለመንግሥት የሚያስፈልገውን ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን እየገለጸ በየአካባቢው ያላችሁ አባላቱ ሁሉ ከሕዝብ ጋር እንድትቆሙና የበኩላችሁን ሃላፊነት ሁሉ እንድትወጡ አደራ ይላል፡፡
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥቃት መካችነት ከአስከፊ ጦርነት ትወጣለች !
ኢትዮጵያ አንድነቷ ተከብሮ ለዘላለም ትኑር!
ኢሕአፓ ለተሻለ ነገ!
ጥቅምት26/2013 ዓ.ም