8 November 2020

EthiopianReporter.com

ተመስገን ተጋፋው

በኢትዮጵያ ለበርካታ አገልግሎት የሚውለውን የእንሰት ተክል የዘረመል ምሕንድስና እንዳይደረግበት፣ ማኅበረሰቡ ከፍተኛ ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ፡፡

ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን እየሰጠ የሚገኘውን እንሰት የዘረመል ምሕንድስና ቴክኖሎጂን በመጠቀም፣ የዘር ዓይነቱን አንድ ዓይነት ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ ተቋማትን ማስቆም እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የዕፀዋት የሥነ ሕይወት ክፍል የብዝኃ ሕይወት ትምህርት መምህርና ተመራማሪ ሰብስቤ ደምሴ (ፕሮፌሰር) እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ 230 የሚሆኑ የእንሰት ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡ እንሰቶቹን በመንከባከብና እንዳይጠፉ በማድረግ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ ሲቻል፣ አንድ ዓይነት ዘር እንዲኖራቸው ማድረግ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የባህላዊ ምግቦች ትሩፋት የሆነው የእንሰት ተክል የዘረመል ምሕንድስና እንዲደረግበት መፈቀዱ ተገቢ አለመሆኑን፣ መንግሥትም እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎች ላይ ከመድረሱ በፊት አርሶ አደሮችንና ተጠቃሚ የሆኑ ማኅበረሰቦች ማነጋገር እንደነበረበት ሰብስቤ (ፕሮፌሰር) አስረድተዋል፡፡

የተለያዩ ጥቅሞችን እየሰጠ የሚገኘው እንሰት የእያንዳንዱ የዘር ዓይነት የሚለያይ በመሆኑ፣ አርሶ አደሮች የሚያገኙት ጥቅም ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸው በተለይም ለምግብነት፣ ለቃጫ፣ ለቤት ምንጣፍ፣ ለገመድና ለሌሎች አገልግሎቶች እንደሚውል አስረድተዋል፡፡

ያለውንም ችግር ለመቅረፍ ማኅበረሰቡም ሆነ አርሶ አደሮች አንድ ላይ በመሆን ትኩረት ሰጥተው መሥራት አለባቸው ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በእንሰት ተክል ላይ የዘረመል ምሕንድስና እንዲደረግበት የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ኮሚሽን ፈቃድ መስጠቱ በማኅበረሰቡም ሆነ በአርሶ አደሩ ዘንድም ቁጣ ማስነሳቱን፣ እንዲሁም ደግሞ ውሳኔው ሲተላለፍ የሚኖረውን ጠቀሜታ ግምት ውስጥ አለመግባቱን፣ የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ጥበቃ ማኅበር መሪ ገብረ መድህን ቢረጋ (ሻምበል) ገልጸዋል፡፡

ከሥራ ሥር ተክሎች ጎራ የሚመደበው እንሰት አንድ ዓይነት ዘር ኖሮት ለአርሶ አደሩ ከመከፋፈሉ በፊት ያለውን ጠቀሜታ ማጤን እንደሚያስፈልግ፣ ይህ ካልሆነ ግን የመጥፋት ዕድል እንደሚኖረውም ገብረ መድኅን (ሻምበል) ጠቁመዋል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ ፔለም ኢትዮጵያ ኮንሰርቲየም፣ የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ጥበቃ ማኅበርና ሌሎች ሲቪል ማኅበራት አንድ ላይ በመሆን ለሚመለከተው አካል ደብዳቤ በመጻፍ ለባለድርሻ አካላት ማስተላለፋቸውን አስታውሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ እስካሁን ድረስ የሚመለከተው አካል ምንም ዓይነት ምላሽ እንዳልሰጣቸው፣ ባለፈው ሳምንትም በመገናኛ ብዙኃን ላይ ቀርበው አንድ ላይ ውይይት ቢያደርጉበትም መፍትሔ ሳይገኝለት መለያየታቸውን አክለዋል፡፡  

በደቡብ ክልል ከንባታ ጠንባሮ ዞን አቃቂ ቢራ ወረዳ ደባሬ ቀበሌ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አቶ ወልዶሮ አቤቦ እንደተናገሩት፣ የእንሰት ተክል በመጠቀም የተለያዩ አገልግሎቶችን እያገኙ መሆኑንና መንግሥትም የዘረመል ምሕንድስና እንዲደረግበት መፍቀዱ አግባብ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

በአካባቢያቸው የተለያዩ የእንሰት ተክል ዝርያዎች እንዳሉ የተናገሩት አቶ ወልዶሮ፣ እንሰቱን ለተለያዩ ምርቶች እንደሚጠቁሙት ገልጸዋል፡፡ ከዚያም አልፎ ከኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቦች አንዱና የአካባቢው ነዋሪዎች መተዳደሪያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ብቻ ለምግብነት የሚውለው የእንሰት ተክል በደቡባዊ ምዕራብ የኢትዮጵያ ክፍሎች ለሚኖሩ የጉራጌ፣ የስልጤ፣ የሐዲያ፣ የከምባታና ጠምባሮ፣ የአላባ፣ የሲዳማ፣ የጌዴኦ፣ የወላይታ፣ የዳውሮ፣ የጋሞ፣ የጎፋ፣ የከፋ፣ የሸኮና የሌሎች ብሔረሰቦች ዋነኛ ምግብ ነው፡፡ FacebookTwitterTelegramGmail