7 ህዳር 2020

ከጊዜ ወደ ጊዜ የሻከረው የትግራይ ክልልና የፌደራል መንግሥት ግንኙነት ወደማይታረቅ ደረጃ ደርሶ ወደ ጦርነት አምርቷል። ለመሆኑ የዚህ ጦርነት መዘዙ ምንድን ነው? የሚሉና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ በዩናይትድ ኪንግደም በኬል ዩኒቨርስቲ መምህርና የምስራቅ አፍሪካ የፖለቲካ የግጭቶች ተንታኝ አወል አሎ ቃሲም (ዶ/ር) ጋር ቢቢሲ ቆይታ አድርጓል።
ቢቢሲ፡ -በትግራይ ክልልና በፌዴራል መንግስት የተከሰተው ጦርነት አራተኛ ቀኑን አስቆጥሯል። ሁኔታው ወደ ጦርነት ያመራል የሚል ግምት ነበረዎት? ሁለቱም ወገኖች ችግራቸውን በሰላምና በእርቅ ሊጨርሱት ያልቻሉበት ምክንያት ምንድን ነው?
አወል አሎ (ዶ/ር)፦ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የሚመራው የፌዴራል መንግሥትና ህወሃት የሚመራው የትግራይ ክልል መንግሥት ልዩነቶች የቆዩ ናቸው። እንደዚህ ዓይነት ልዩነት ደግሞ በሳል በሆነ ሁኔታ በወቅቱ የማይፈታ ከሆነ አደገኛ ወደ ሆነ ሁኔታ ሊያመራ እንደሚችል በጣም ግልጽ ነበር።
በርካቶች ሊመጣ እንደሚችል ሲገምቱት የነበረ ጦርነት ነው። ያልተጠበቀ ነገር አይደለም። ምናልባት በዚህ ወቅት ይመጣል ብሎ የጠበቀ ላይኖር ይችላል። ነገር ግን የፌዴራል መንግሥቱ የስልጣን ወቅት ከሚያልቅበት እስከሚቀጥለው ምርጫ መሃከል ግጭት ሊከሰት እንደሚችል የተለያዩ ተንታኞች ሲያመለክቱ ነበር።
ምክንያቱም ህወሃት እንደሚታወቀው ምርጫው መደረግ አለበት ብሎ የፌዴራል መንግሥቱን በመቃወም ምርጫውን ማካሄድ ግንኙነታቸውን እያካረረው መጣ። ከህወሃት እይታ አንፃር የዐብይ መንግሥት ላይ ትልቅ ጫና መፍጠር የሚቻለው የፌዴራል መንግሥት ስልጣን ማብቂያ ጊዜ ነው የሚል እምነት ያለ ይመስላል።
ሁለቱም በአቋማቸው ለድርድር ፍቃደኛ እንዳልሆኑ የሚያሳዩ ብዙ ምልክቶች አሉ። በመጨረሻም በሁለቱም ጎን ወደ ኋላ የመመለስ ፍላጎት ስላልነበረ ሁለቱም መንግሥታት በጣም አሳፋሪ ወደሆነ ምናልባትም በቀላሉ ሊያባራ ወደማይችል ጦርነት እንደሚያመራ ግልጽ ነበር።
ቢቢሲ፡ -ጦርነቱ እንዲህ በቀላሉ ሊያባራ አይችልም ከተባለ ምን ሊያስከትል ይችላል?
አወል አሎ (ዶ/ር)፦ መመልከት ያለብን ነገር በሁለቱም መሃከል ያለው ፖለቲካዊ ልዩነት ምንድን ነው የሚለውን ነው። በመሰረቱ በዐብይ መንግሥትና በህወሃት መሃከል ያለው ልዩነት የርእዮተ ዓለም ልዩነት ነው።
ከዚህ ርእዮተ ዓለም በሚነሳ ኢትዮጵያ ለወደፊት ምን ዓይነት አገር መሆን አለባት? የምትከተለው መርህ ምን መምሰል መቻል አለበት? ሃገረ መንግሥቱ ምን ዓይነት ቅርጽ ሊኖረው ይገባል? በሚሉ ሁኔታዎች ላይ መሰረታዊ የሆኑ ልዩነቶች አሉ።
ከዚህም በተጨማሪ ህወሃት ከስልጣን መውረዱን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የራሳቸው ስልጣን ከማጠናከር አኳያ ህወሃትን የመግፋትና በህወሃት ዘመን የተሰሩ ነገሮችና ‘ሌጋሲን’ የማውደም ስራ ሲሰራ ነበር።
በተለይም ደግሞ ኢህአዴግን ከማፍረስና (ማዋሃድና) ብልጽግና ፓርቲን ከመፍጠር ጋር ተያይዞ የተሰሩት ነገሮች መሰረታዊ የርእዮተ አለም ልዩነቶች መኖራቸውን የሚያሳዩ ናቸው።
በየቦታው የምናያቸው ችግሮች ፌዴራል መንግሥቱ ህወሓት የፈጠራቸው ናቸው ይበል እንጂ ህወሃት ይፍጠራቸው መንግሥት በሁለቱ መሃከል ያለውን ርእዮተ ዓለምና የሃይል ልዩነት ከመሸናነፍ አንጻር ሊታዩ የሚገባቸው ናቸው።
አሁን በቅርቡ ጊዜ ወለጋ አካባቢ ተፈጸመ የተባለው የንጹሃን ዜጎች ግድያ ወዲያውኑ ታጣቂ በሆነው ኦነግ ሸኔ በሚባል ቡድን ነው የተፈፀመው፤ ህወሃትም ከጀርባው አለ ተባለ። በህወሃትና በኦነግ መካከል የነበረው መጥፎ ግንኙነት የሚታወቅ አይደለም?
ይህንን ተከትሎ በተወሰኑ ቀናት ውስጥ ጦርነት ተጀመረ። ጥቃት ተፈፀመ የሚሉ ምክንያቶች ከመቅረብ ባለፈ በሁለቱ መንግሥታት መካከል ያለው ልዩነት የሚያሳዩ አይደሉም። እነዚህ ህዝብ ሊያያቸውና ሊፈራ የሚችልባቸው ልዩነቶች ናቸው።
ስለዚህ ይሄ ጦርነት መሰረታዊ የሆነ የርእዮተ ዓለም ልዩነት ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ጦርነቱ በአጭር ግዜ ሊያባራ አይችልም። በቀላሉ አሸናፊ የሆነ አካል የሚኖርም አይመስለኝም።
ጦርነቱ ከቀጠለ ደግሞ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ቀጠናው ላይ ሊያስከትል የሚችለው መዘዝ ቀላል አይደለም። የኤርትራ መንግሥት እንቅስቃሴ ከቅርብ ግዜ ወዲህ እየተጠናከረ መጥቷል። በርግጥ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ግንኙነት የመንግሥት ለመንግሥት ግንኙነት አይመስልም፤ ግላዊ የሆነ ግንኙነት የሚመስል ሁኔታ ነው ያለው።
የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ስርዓት በተመለከተ አቋሙን በግልጽ ሲያንጸባርቅ እንደነበረ እናውቃለን። ይሄ ደግሞ በዐብይ መንግሥትና በህወሃት መሃከል ያለው የርዕየተ ዓለም ልዩነት ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ነው።
ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ ብሄርን መሰረት ያደረገው ፌዴራሊዝም ኢትዮጵያ ውስጥ አያስፈልግም የሚል እምነት አላቸው። ኤርትራ በዐብይ መንግሥትና በትግራይ ክልል መንግሥት የሚደረግ ጦርነት እጅ የላትም ማለት አይቻልም።
ሶማሊያ ላይ ያሉ የኢትዮጵያ ወታደሮች መውጣታቸው አይቀርም። የዚህም አንድምታ አልሻባብ እንደ ልቡ ይንቀሳቀሳል ማለት ነው። ሱዳንም ላይ እንደዚሁ ችግር እንዳለ ይታወቃል። ስለዚህ ችግሩ ሰፋ ያለ ቀጠናው ውስጥ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ምንም ጥያቄ የለውም።
ቢቢሲ፡ ከኤርትራ መንግሥት ጋር በተያያዘ በተለይ ደግሞ ህወሃት በአገሪቱ ጣልቃ ገብነት ሲከስ ይሰተዋላል። በሁለቱ አገራትም ያለው ድንበር እንደተዘጋ ነው። በሁለቱ አገራት ላይ ከተፈጸመው እርቅ ጋር ተያያዞ እርቀ ሰላሙ ምን ደረጃ ላይ አለ ይላሉ?
አወል አሎ (ዶ/ር)፦ መጀመርያ ላይ በሁለቱም አገሮች መሃከል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወሰዷቸው እርምጃዎች ሁላችንም ያደነቅነው ነው። የሚደገፍ ሂደት ነበር። የሁለቱም አገሮች ግንኙነት ወደሰላም ማምጣት የሚደገፍ ነበር።
ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ችግር በተለይ በፌዴራል መንግሥትና በትግራይ መንግሥት መካካል የነበረው ችግር ያ የሰላም ስምምነት ወደፊት እንዳይሄድ አድርጓል። እንደሚታወቀው ችግሩ በዋናነት የነበረውና ዋናው መገለጫው የድንበር ችግር ነው ተብሏል። ድንበሩ ደግሞ ያለው በትግራይ ክልል ነው። የፕሬዚዳንት ኢሳይያስና የትግራይ ክልል ግንኙነት ጥሩ አልነበረም። የዐብይና የኢሳያስ ፍላጎት ህወሃትን ማስወገድና ኮርነር (አጣብቂኝ ውስጥ የመክተት) ነው። ከምንም ፖሊሲ ላይ የተመሰረተ ከመሆን በላይ ።
የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ህወሓት የመራውና ኢሳይያስ የተሸነፉበት ጦርነት ስለሆነ ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ ህወሃትን መልሰው ማሸነፍ ይፈልጋሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይም የራሳቸው የሆነ ርእዮተ ዓለም ስላላቸው ይህንን ርእዮተ ዓለም ከጫፍ እንዳይደርስ ትልቁ እንቅፋት የሆነው ህወሃት ነው ብለው ስለሚያስቡ ሁለቱም ፕሬዚዳንት ኢሳይያስና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ህወሃትን እንደ ጋራ ጠላት አድርገው ያያሉ። እዚህ ጉዳይ ላይ ይከባበራሉ የሚልም የትንታኔ መሰረት አለው።
ስለዚህ አስመራ ልክ እንደ አዲስ አበባና መቀሌ የዚህ ጦርነት አባል ናት ብንል ስህተት አይመስለኝም። ተሳትፏቸው ምንያህል ነው የሚለውን ነገር አሁን ባለንበት ሁኔታ መመዘን ባንችልም ኤርትራ በዚህ ጉዳይ ላይ ትልቅ ፍላጎት እንዳላት መገመት ይቻላል።
ቢቢሲ፡ ስለዚህ ከኢትዮ-ኤርትራ የእርቀ ሰላሙ ጋር ተያይዞ እርስዎ የሰላም የኖቤል ሽልማት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ እንዲሰጥ ዕጩ አድርገው ከጻፉት መካከል አንዱ ነበሩና በዚህ ወቅት ዘወር ብለውሲያዩት ‘ምናልባት ያልበሰለ ነገር ነበር? ቸኩያለሁ‘ የሚል ስሜት ፈጥሮብዎታል?
አወል አሎ (ዶ/ር)፦ የኖቤል ሽልማት ዕጩነት ደብዳቤ ባስገባሁበት ጊዜ የመጻፍ ውሳኔ የተመሰረተው በወቅቱ በማየውና በነበረው ነባራዊ ሁኔታ ነው። በአብዛኛው አንዳንድ ጊዜ የምናከናውነው ነገር ወደኋላ ሂደን ተመልሰን ስናየው ስህተት መስሎ የሚታይበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል።
እኔ አሁንም በዛን ግዜ በነበረው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በሰሩት ስራ የተሰጣቸው እውቅና መጥፎ ነው ብዬ አላስብም። ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ችግርና የኢትዮ-ኤርትራ ግጭት ሙሉ ለሙሉ ይፈታል የሚልም አልነበረም ግምቴ። ቢያንስ ግን ለሰላም ባደረጉት ጥረት ይህንን እውቅና ቢሰጣቸው ወደፊት የተሻለ ስራ ይሰራሉ የሚል ግምት ነበረኝ።
የነበረኝ ግምትና ትንታኔ ስህተት ነበር። ግን ደግሞ ለሽልማቱ በማጨቴ የሚቆጨኝ ነገር የለም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ያንን ሽልማት አግኝተው አሁን በምናየው ሁኔታ ጦርነት ማወጃቸው በዚህ ደረጃ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ምን ነካቸው ተብሎ እንዲነገር ዕድል ይሰጣል። ስለዚህ ስማቸው በዛው ደረጃ እንደገነነ ሁሉ የሚፈፀሙ ድርጊቶች ከዚያ ከፍ ያለ እውቅና ጋር የሚመጣጠን እንደሆነ ነው። ሳይሆን ሲቀር ደግሞ እንደዛው ተጠያቂነት እንደሚመጣ ነው በዚህ መልኩ ነው የማየው።
ቢቢሲ፡ -በአሁኑ ወቅት ጦርነቱ እንዲረግብና ዘላቂ መፍትሄ እንዲመጣ ምን ምን መደረግ አለበት ይላሉ? ከሁለቱም ወገንና ከዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ምን ይጠበቃል?
አወል አሎ (ዶ/ር)፦ ጦርነት መጀመር ቀለል ያለ ነገር ሊሆን ይችላል ግን ከጦርነት መውጣት በጣም ከባድ ነው። ሁሉም በእልህ ጦርነቱ ውስጥ ከገቡ በኋላ ተሸናፊ መምሰል ስለማይፈልጉ የተለያዩ የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ አካላት ጫና የመቀበል ሁነታ ያነሰ ነው የሚሆነው። አንዳንድ ሚድያዎች እንደዘገቡት የፌዴራል መንግሥቱ ድርድር እንደማይቀበልና ጉዳዩ በጦርነት ብቻ መፈታት እንዳለበት እንደሚያምን የሚያሳይ ነው።
ህወሃትም ግጭቱ እንዲባባስ የራሱን ሚና ተጫውቷል። በሁለቱም በኩል ነገሩ በሰላም እንዲፈታ ፍላጎት ያለ አይመስለኝም። ግን ደግሞ እንደዚህ ዓይነት ጦርነቶች ቶሎ አይጠናቀቁም። የሚዳከም ቢኖርም ግልጽ በሆነ መልኩ ተሸንፎ እጅ የሚሰጥ፣ ተንበርክኬያለሁ የሚል አካል አይኖርም።
ስለዚህ ከዚህ ጦርነት የሚጠቀም አንድም የለም። የሚጎዳ ግን ሁሉም ማለት ይቻላል። ስለዚህ ሁሉም ማድረግ ያለበት፤ ከውስጥም ከውጭም ሁለቱም ወገኖች ችግራቸው ለመፍታት ለውይይት ይቀመጡ ነው።
ግን ሁለቱም አከባቢ ዝግጁነት ያለ አይመስለኝም። በጦርነት ሊፈታ የሚችልም ችግር ያለ አይመስለኝም። ችግሩ ፖለቲካዊ ነው፤ የርእዮተ ዓለም ችግር ነው፡ ስለዚህ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ ፖለቲካዊ መፍትሄ የመስጠት እና የኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፈንታ ምን መሆን አለበት የሚለው ነገር ለኢትዮጵያ ህዝብ መተው አስፈላጊ ነው።
ቢቢሲ ጠቅላይ ሚኒስተር ዐብይ ወደ ስልጣን ከመጡ ጊዜ ጀምሮ፤ በአገሪቱ ግጭቶችና ግድያዎችተበራክተዋል የሚሉ ሪፖርቶች አሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ የኢትዮጵያ ቀጣይ እጣ ፈንታ የሚወስን ራእይ ተቀባይነት እንዳላገኘ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል?
አወል አሎ (ዶ/ር)፦ ከርእዮተ ዓለሙ አንጻር እነዚህ ችግሮች እየተፈጠሩ ያሉት ስርዓቱ በራሱ የፈጠራቸው ናቸው የሚል ክርክር ይቀርባል። በሌላ መልኩ ደግሞ ብሄርን መሰረት ያደረገው ፌደራሊዝም የፈጠረው ችግር የለም የሚሉ ኣሉ።።
አገሪቱ ውስጥ እየተፈጠረ ያለው መከፋፈል ስናይ ምናልባት ኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጠሩ ያሉት እነዚህ ችግሮች ወደፊት ምን ዓይነት አገር መኖር አለበት የሚል ህልም ለማሳካት የራሳቸውን ርእዮተ ዓለም ለማጠናከር የሚፈልጉ ሃይሎች የሚያደርጉትን ሊሆን ይችላል። ነገር ግን መንግሥት እዚህ ነገር ውስጥ እጁ የለም የሚለው አመለካከት ለእኔ በጣም ከባድ ነው።
ሻሻመኔ የተፈጠረውን ጥቃት በምናይበት ግዜ የሰው ልጅ በዚያ ደረጃ እየተገደለ የጸጥታ ሃይሉ ጣልቃ አልገባም። “ጣልቃ ለምን አትገቡም “ተብሎ ሲጠየቅ ‘ትእዛዝ አልተሰጠንም’ ብለው ሲከራከሩ ነበር። የሆነ ሆኖ ግን ለሚካሄደው የርእዮተ ዓለም ጦርነት እንደግብዓት ስራ ላይ እየዋለ ነው። እልቂቶቹን ግን በትክልል ማነው እየፈፀማቸው ያለው ለሚለው ለማወቅ ገለልተኛና እሙን የሆነ ማጣራት መደረግ አለበት። ከዚያ ውጪ እገሌ ነው እገሌ ነው ለማለት የምንችልበት መረጃ ማግኘት ከባድ ነው።
ቢቢሲ፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ራሳቸው ከ20 ዓመታት በላይ በፌዴራሊዝም ስርዓት የሚያምነው ኢህአዴግ ውስጥ የነበሩ ሰው ናቸው። በተለያየ ጊዜ ሲናገሩም የፌዴራሊዝም ስርዓት ደጋፊ እንደሆኑ የሚናገሩበት ሁኔታ አለ። በዚህ ደረጃ የርእዮተ ዓለም ጦርነት ብለን ልንገልጸው የምንችለው ክህወሓት ጋር ምን ልዩነት ቢኖራቸው ነው?
አወል አሎ (ዶ/ር)፦ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዙ ጊዜ በሚያወሩበት ወቅት በጣም ግልጽ የሆነ ርእዮተ ዓለማዊ አቋም የላቸውም። በየቦታው የተለያየ ለእሳቸው ፖለቲካ በሚመች መንገድ ይናገራሉ። አሀዳዊ የሆነ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ሲያናግሩ በእነሱ ቋንቋ ያወራሉ። ሌሎችም ሲያናግሩ ሌላ ነገር ይናገራሉ።
ከድርጊታቸውና ከሚወስዷቸው ተቋማዊ እርምጃዎች ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግልጽ የፌዴራል ፕሮጀክት ወይም ደግሞ ፌዴራሊዝም የሚቆምባቸው መሰረቶችና ሊያሳካ የሚፈልጋቸው የሚደግፉ ሰው ናቸው ብሎ ማሰብ አይቻልም።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሃዳዊ ናቸው ማለት ይቻላል። ከተግባራቸው በትክልል መረዳት እንደሚቻለው ፌዴራላዊ የሆነ መዋቅር ሳይሆን፤ በተወሰነ ደረጃ የተማከለ የራሳቸውን ስልጣን የሚያጎላ ዓይነት የፖለቲካ መዋቅር እንደሚፈልጉ በጣም ግልጽ ነው። ባይናገሩትም።
ከህወሃት ጋር እንደነበሩ ግልጽ ነው።ያለፈው ስርዓት በሚወቅሱበት ጊዜ በፖለቲካው ደረጃ ህወሃትን መተቸት በአብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ተቀባይነት ስላለው፤ ዋና ባላንጣቸው አሁን ህወሓት ስለሆነ፤ ያንን ድርጅት ከማጥላላት ከማንቋሸሽ አንጻር የሚሰራ የፖለቲካ ስራ ነው።
ቢቢሲ፡- አሃዳዊነት ለሚሉት ዋና ማሳያዎቹ ምንድን ናቸው?
አወል አሎ (ዶ/ር)፦ ዋናው ነገር ብልጽግና ፓርቲ የተዋቀረበት መንገድ ነው። ብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ፕሮግራሙ ለማስፈጸም የቀረጸውና የፈቀደው የፖለቲካ ስራ ነው። ከዚህ ውጪ ማሳያ ማምጣት አያስፈልግም።
በተለያዩ መድረኮች የተናገሩዋቸውን ማምጣት ይቻላል ግን ዋናው ማሳያ ፓርቲው ራሱ የተዋቀረበት መንገድ ነው። መሬት ላይ የሚታየው፤ ተቋማዊ መንግሥት የሚመራ ድርጅት አወቃቀሩም አመለካከቱም አሃዳዊ ነው። ግልጽ የሆነ ርዕዮተ አለም ባይኖረውም የሚታየው ነገር አሃዳዊ ነው።