November 10, 2020

የሰሜን ዕዝ ከማዕከል ጋር የሚኖረው የመገናኛ ሥርዓት እንዲቋረጥ በማድረግ በህዋሃት የጥፋት ቡድን ጥቃት እንዲፈፀምበት ሲያመቻቹ የነበሩ ጀነራል መኮንኖች ከነ ግብረ አበሮቹ በቁጥጥር ሥር ዋሉ።

በሀገር መከላከያ ሠራዊት አባል ሆነው ከጁንታው ህወሃት ጋር በመጣመር ጥቅምት 24, 2013 ዓ.ም ምሽት ላይ በትግራይ ክልል የሚገኘው የሰሜን ዕዝ ከማዕከል ጋር የሚኖረው ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ እንዲቋረጥና የዕዙ የመገናኛ ሥርዓት ለጁንታው የህዋሃት ወንበዴው ቡድን እንዲመቻች በማድረግ የተጠረጠረው ሜጀር ጀነራል ገብረመድህን ፈቃዱ ወይም በቅጽል ስሙ ወዲ ነጮ የተባለው ተጠርጣሪ በአገር ክህደት ወንጀል ከነ ግብረ አበሮቹ በሀገር መከላከያ ሰራዊትና በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ተደርጓል።

የአገር ክህደትን በመፈጸም በዋናኝነት የተጠረጠረው ሜጀር ጀነራል ገብረመድህን ፍቃዱ ከለውጡ በፊት በአገር መከላከያ ሠራዊት የአጋዚ ኮማንዶና ልዩ ኃይሎች አዛዥ የነበረ ሲሆን፥ በሰራዊት ውስጥም በተለያዩ የሥራ እርከኖች ያገለገለ መሆኑን ያመለከተው መግለጫው፤ ለውጡን ተከትሎም በአገር መከላከያ ሰራዊት የመገናኛ መምሪያ ሃለፊ በመሆን ሲሰራ እንደነበር አስታውሷል፡፡

Image may contain: one or more people and people standing

ይሁንና ከመንግስት፣ ከህዝብና ከአገር መከላከያ ሰራዊት የተጣለበትን ከባድ አደራና ሃላፊነት አገር ለማፍረስና ለማተራመስ ከሚንቀሳቀሰው የጁንታው የህዋሃት የሴራው አካል በመሆን የሰሜን እዝ ከማዕከል ጋር ያለው ግንኙነት እንዲቋረጥና በከሃዲዎች ጥቃት እንዲፈፀመበት ከማድረጉም በላይ፤ በውስጣቸው ቦንቦችና የሚሳየል መሳሪያዎችን የያዙ 11 ሳጥኖች የግንኙነት መሳሪዎች ናቸው በሚል ሽፋን ወደ ትግራይ የጁንታው ቡድን ለመላክ ሲዘጋጅ ከተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ጋር እጅ ከፍንጅ መያዙን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በላከው መግለጫ አመልክቷል ።

የሀገር መከላከያ ሰራዊትና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ባደረጉት ጠንካራ ክትትልና ባካሄዱት ኦፕሬሽን ተጠርጣሪው ሜጀር ጀነራል ገብረ መድህን ፈቃዱን ጨምሮ ሌሎች ጀነራል መኮንኖች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የበታች ሹማምንቶቻቸው በድምሩ 17 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ተገልጿል።

በቀጣይም ከጁንታው የህዋሃት የጥፋት ቡድን አገር የማተራመስና የማፍረስ ሴራ እንዲሁም በአገር ክህደት ወንጀል የተሳተፉትንና በየትኛውም የኃላፊነት ደረጃና መዋቅር ላይ ያሉ ተጠርጣሪዎችን ተከታትሎ በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል።

Source – ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን