ወልቃይት፣ የትሕነግ ስስ ተረከዝ!
(ጌታቸው ሽፈራው_ ከወር በፊት ፍትሕ መፅሔት ላይ የወጣ)
ጦረኝትና የአጋር ርሃብ
–
‹‹የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር (ትሕነግ)›› የመጣበት መንገድም ሆነ የታጠፈባቸው የፖለቲካ ኩርባዎች፣ ጮኸው የሚነግሩን የበላይነትና ጦረኛነት የተጠናወተው የመሆኑን አንድመታ ነው፡፡ ‹እውነትም ትግልም በእኔ መንገድ ብቻ› የሚለው ድርቅናው እንኳ፣ በ‹ፓዎር ድርቅ› እያሰቃየው ነው፡፡ ካፈጣጠሩ እስከ አፈፃፀሙ ‹ሰጥቶ መቀበል› ብሎ ነገር አይገዛውም፡፡ አግበስባሽ ሥነ-ልቦናው ከድርድር አርቆ፣ በመሬት ጠኔ ጠርንፎታል፡፡ ‹እኩልነት፣ ወንድማማችነት፣ አንድነት› የሚባሉ ቃላቶችንም፣ ከፖለቲካው ዲክሽነሪ ሰርዞ፤ ጦረኛነት፣ ፈራጅነት፣ በታኝነትን… ሲተካ ገና ደደቢት በረሃን እንኳ በቅጡ አለመደውም።
–
እኒህ የተጨቆኑ እውነቶች ዛሬ ድረስ ብልጫውን በማያረጋግጥበት ትብብርና አጋርነት አለመሳተፉን ያስረግጣሉ። በጦረኛ ሥነ-ልቦናው ይዋጋል፡፡ ቀን ሲጎድለበት ደግሞ ሽብርና የዱርዬ ተንኮል ሲያላምጥ ይውላል፤ በተከናበው ለምድ አድፍጦ፣ ጊዜና ቦታ ጠብቆ እንዳትነሳ አድርጎ ይቀብርሃል። ከሽፍትነት እስከ አገር መሪነት ባሳለፈው ገድሉ፣ ከኢሕአፓ እስከ ሻዕቢያ፤ ከኢዴኀ እስከ ጀብሃ… ከሚዘረዘሩ የፖለቲካ ቡድኖች ጋር ያደረገው ውጊያ ከሞላ ጎደል እንዲህ ዐይነት ስልቶችን የተከተሉ ናቸው።
–
የትሕነግን መርህ-የለሽ ወንበዴነትም ሆነ ስለ ትግራይ ሕዝብ ተቆርቋሪነት አብዝቶ የማውራት ኑፋቄን ለማስረገጥ ግን፣ በትግራይ ተወላጆች የተቋቋመውን ድርጅት የካደውን ያህል መሳያ አይኖርም፡፡ በርግጥ ያደረገው ነገር ማሰብ አይጠይቅም፤ አመራሩን ‹እንደራደር› ብሎ ለጠረጴዛ መፍትሄ ጋበዘ፣ ሌሊት በተኙበት ረሸነ፡፡ እንደ አስፈላጊነቱ ደግሞ ከ77ቱ ድርቅ ለመታደግ የተላከውን ስንዴ ከትግራዋያን እጅ ነጥቆ፣ የእጅ ቦንብ መግዛቱን አስታውስልኝ፡፡
–
በጫካ ዘመኑ በተለይ በመጀመሪያዎቹ ዐመታት ‹የአጋር ያለህ› በሚል በምድረ-በዳ ሲጮህ ከርሟል፡፡ ‹‹የጨነቀ ለታ›› እንዲሉ፤ በጦር ወግቶ ካዳከመው ኢሕአፓ፣ ኢሕዴንን አዋልዷል፡፡ እሱስ፣ ጦረኛና ከነባራዊው ሃቅ የተጣረሰው የበላይነት ‹ኢጎ›ው በአብሮነት አላሰነብተውም እንጂ፣ ያልፈጠረው አጋርነት አልነበረም፡፡ የማኀበራዊ መሠረቱ ጥበትና የትግራይ መልከዐ-ምድራዊ ውስንነትን አስልቶ፣ ከኤርትራ ድርጅቶች ወደ ሱዳን መውጫ መሬት ፍለጋ ተንከራትቷል። በተለይ በወልቃይት ጠገዴ በስፋት ይንቀሳቀስ ከነበረው ኢዴኀ (እነሱ ‹ጠርናፊት› ይሉታል) ላለመጋጨት ቢያስመስልም፣ መጭረሻው በደም-አፋሳሽ ትንቅንቅ ተቋጭቷል፡፡ ኢሕአፓ ላይም በበለሳ ያሴረው፣ ለበለስ ለቀማ አይደለም፤ ወልቃይትን ለመቆጣጠር እንጂ፡፡ እዚህ ጋ የዓይን ምስክር አቅርቤ አልፋለሁ፡፡ በወቅቱ የግንባሩ ወታደራዊ ኮማንደር አዛዥ ነበሩ፡፡ አሁኑ ‹ዶክተር› ሆነዋል፤ ዶ/ር አረጋዊ በርኼ፡፡ ለቪኦኤ ዐማርኛ በሰጡት አንድ ቃለ-መጠይቅ ይህንህ ብለው ነበር፡-‹‹ወልቃይትን መቆጣጠር ያስፈለገው ወደ ሱዳን መውጫ ለማግኘት ነው፡፡››ምስክሩን አሰናብተን እንቀጥል፡፡
–
ግሉኮሷ ወልቃይት

አማላይዋ ወልቃይት ጠገዴ በሦስት በተከፈለ የአየር ጠባይ ተባርካለች፡፡ ቆላማው አከባቢ 75% ይሸፍናል፤ ወይና ደጋ እና ደጋው ደግሞ ቀሪውን 15% እና 10% አካባቢያዊ አየር ጠባይ ይቃረጣሉ። አጠቃላይ የወልቃይት ጠገዴ የአዲስ አበባን ሠላሳ እጥፍ ያስከነዳል። በወረዳ ከሸነሽንከው ደግሞ ‹‹ቃብትያ›› ብቻውን 664,285,85 ሄክታር ይይዛል፡፡ በመቶኛ ስተመታው 48.13% ይሆናል። ‹‹አድረመጥ›› 27%ቱን ይሸፍናል። ጠገዴ ከአጣቃላይ የወልቃይት ድርሻው 23.43% ነው። ዝነኛዋ ‹‹ሰቲት ሁመራ›› ደግሞ 11,373,74 ሄክታር ብትሰፋም፣ ከጥቅል ይዞታው የምትሸፍነው 0.84% ነው፡፡የወልቃይት ጠገዴን የዝናብ መጠን በሜትሮሎጂኛ ስናስቀምጠው በዐመት ከፍተኛው ከ900 እስከ 1800 ሚ.ሜ ይደርሳል። ሁመራ እና አካባቢው ከ600 እስከ 875 ሚ.ሜ ከፍተኛ የዝናብ መጠን ይኖራቸዋል።
በዚህ ላይ ዐመት ሙሉ የሚፈሱ ትላልቅ ወንዞች ባለቤት መሆኑን ደምርበት። ወልቃይት ጠገዴን፣ ከትግራይ ክልል በግልፅ የሚለየው ተፈጥሯዊ ደንብር ተከዜ ወንዝም ዐመቱን ሙሉ የሚፈስ ከኢትዮጵያ ታላላቅ ወንዞች አንዱ ነው፡፡ ሕወሓት ራሱ ባስጠናው ጥናት፣ ተከዜ ግድብን ከደለል ለመከላከል 28 ወረዳዎች ላይ ሥራ መሠራት እንዳለበት ነግሮህ ሲያበቃ፤ ወረዳዎቹን ሲዘረዝራቸው አሁን ባለው አከላል 18ቱ ዐማራ ውስጥ ሲሆኑ፤ የተቀሩት የተወሰዱት መሬቶች ላይ ናቸው፡፡
–
ወንዝ ቆጠራውን አልጨረስንም! ሩዋሳ፣ ባህረ ሰላምባ፣ ዜሬማ፣ ካዛ፣ ቃሌማ እና ሞኮዞ የተሰኙ ዐመት ሙሉ የሚፈሱ ወንዞችም የዚሁ አካባቢ ‹ምድር-ከብድ› ናቸው። የወልቃይት ጠገዴ መሬት ለእርሻ ፍፁም ተፈጥሯዊ መሆናቸውን ለመረዳት ከ‹እርሻ ምርምር ተቋም› ጥናቶች ይልቅ፤ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የተለያዩ አዝርእቶች መብቀላቸው ህያው ምስክር ይሆኑል። የሰሊጥ፣ ጥጥ፣ እጣን… ኤክስፖርት የኢኮኖሚው ዋልታ ከሆኑ ሰንብተዋል። እነ ወርቅ-ነሽ (ሯጯን አይደለም)፣ እነ ኦፓል-ነሽ እንደ ዶሮ ጭረህ የምታፍሳቸው ማአድን ናቸው። ትሕነግ በ‹ደህና› ጊዜ አካባቢውን በጉልበት መጠቅለሉ፣ አብዛሃውን የትግራይ ክልል የውስጥ በጀት ያለጭንቀት እንዲሸፍን አስችለውታል፡፡ የወልቃይት ጠገዴ የዐማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴም (ይፋዊ ባልሆነ) ጥናቱ ይህንን ጥሬ ሃቅ በስፋት አመላክቷል፡፡
–
‹ያኔ ገና ልጅ እያለን› እንዳንል፤ መጃጀትም፣ የልጅነት አቻ ይሆንብናል፡፡ ትሕነግ፣ በትግራይ እጎለመሰ ሲመጣ፣ 16 የእርዳታ እህል የጫኑ ከባድ መኪናዎችን ከደርግ ዘርፎ እህሉን ሱዳን ወስዶ ለመሸጥ ያደረገው ሙከራ ፊቱን ወደ ወልቃይት እንዲያዞር ገፊ-ምክንያት ሆኖታል፡፡ ይሄን የላኩት እኔ አይደለውም፤ በድርጅቱ ድርሳናት ሳይቀር የሰፈረ ነው፡፡ በወቅቱ ትሕነግ ወደ ሱዳን መጓዝ የጀመረው በጀብሃ ነፃ መሬት ነበርና፣ ጀበሃ “በእኔ ገዥ መሬት ለማለፍ ከፈለጋችሁ ግማሹን አካፍሉኝ?” ሲል ተዝናንቶ ይጠይቃል። ነገሩ በሌባ ቤት፣ ሌባ ሲገባ እንደ ማለት ቢሆንም፤ እነ አቦይ ስብሃት መከፋፈል እንጂ፣ መካፈል አያውቁምና በጥያቄው ይደናገጣሉ። በልመና እና በልምምጥ ብዙ ጊዜ ቢያጠፉም፤ ጀብሃ ‹ዘርፈህ እንጂ፣ ገዝተህ አለመጣኸውም› በሚል ሙግት እኩል ካልተካፈለ 16 መኪና ቀርቶ፣ 16 ኪሎ ስንዴ እንኳ እንደማያልፍ ያስረግጣል፡፡
ይኼኔም ከማከፈል ሞቱን የሚመርጠው ትሕነግ፣ 16ቱንም መኪናዎች ከእነ ጭነታቸው አቃጥሎ፣ እሳቱን ሞቆታል።ከዚህ በኋላ ነው ሌሎችን “አሳልፉልኝ” እያለ የትም እንደማይደርስ የገባው፡፡ እናም ወልቃይት ጠገዴን የትኛውንም ዋጋ ከፍሎ በግድ መያዝ እንዳለበት ወሰነ።–የወቅቱ የሱዳን መንግሥት የውስጥ ግጭቱን ያበረዱለትን ዐፄ ኃይለሥላሴ ውለታ ቆጥሮ፣ ‹ማርክሲስት ሌኒኒስት ነን› ከሚሉት ይልቅ፤ ፊውዳል ዘመሙን የመሳፍንቶች ድርጅት ኢዴኀን ያግዝ ነበር። Christopher Clapham የየካቲቱን አብዮት በተነተነበት ‹‹Transformation and Continuity in Revolutionary Ethiopia›› መጽሐፉ፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኀብረት (EDU) በተቀናጀ ሁኔታ ትግል ሲጀምር፣ መሪዎቹ ራስ መንገሻ ስዩም እና ሜ/ጀኔራል ነጋ ተገኝ በካርቱሙ የኒሜሪ መንግሥት ቀለብ ሰፍሮላቸዋል፡፡ ይሄ ትግግዞሽ ኢዴኀን ለደርግም ሆነ ለሸማቂዎቹ ራስ ምታት አድርጎት ነበር። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የነበረው John Young ኢዴኀ ስለነበረው ዓለም ዐቀፍ ድጋፍ ‹‹Peasant revolution in Ethiopia The Tigray People’s Liberation Front, 1975-1991›› መጽሐፉ አትቶታል፡፡ በተለይ ‹‹War against the nobles›› የሚል ንዑስ ርዕስ በሰጠው ክፍል ኢዴኀ፣ ከአሜሪካው የስለላ ድርጅት (CIA) የገንዘብ ድጋፍ ማግኘቱን፣ ሱዳን ውስጥ የሬዲዮ ጣቢያና የካድሬ ትምህርት ቤት ከፍቶ ማስተማተር መቻሉን እና ወልቃይት ጠገዴ ዋና መንቀሳቀሻው እንደነበረ ይዘረዝረዋል፡፡ ድንገተኛ ጥቃት አድርሶ የመመለሻ ሰፊ ግዛት ነበረው። ሱዳን ውስጥ ሀብትና አባላትን በማፍራት ትልቅ እድል አግኝቷል። ክላፋም በጠቀስኩት ሥራው በ1968/69 በወልቃይት ሁመራ አካባቢ የኢዴኀ ኀይል የተጠናከረ ቢሆንም፣ መሪዎቹ ከከሰላ አካባቢ አልፈው ባለማታገላቸው፣ ገዥ-መሬታቸው በትሕነግ መነጠቁን መስክሯል፡፡
–
በወቅቱ የኤርትራ ተገንጣዮችና ኢዴኀ ለራሳቸው መውጫ-መግቢያ ይዘው በነፃነት መንቀሳቀሳቸው እንዳጠናከራቸው የተረዳው ትሕነግ፣ ‹ወልቃይት ጠገዴ ወይም ሞት› ብሎ ከኢዴኀ ተዋግቷል። ይህንን አካባቢ ካልያዘ ከበርሃ ወደ ከተማ መጓዙ ቀቢፀ-ተስፋ እንደሆነ ሲገለጥለት፣ ሱዳን ደጅ እጅ መንሻ ተሸክሞ ተንበርክኳል። ‹ይገባኛል የምትለውን መሬት› በሙሉ እንዲመለስላት ለመሥራት ቃል መግባቱን የቀድሞ ታጋይ አቶ ገብረመድኀን አርዓያ ደጋግመው ምስክረውበታል፤ (‹የዐማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ለሱዳን መሬት አሳልፈው ሰጥተዋል› ተብለው ሲወቀሱ የኖሩበት ትረክት፣ ከአንድ ዐመት በፊት በትሕነግ መሪዎች እንደተሰጡ የሚያወሱ የሰነድ ማስረጃዎች ተበትነው እንዳጋለጡት ልብ ይሏል።) ሌሎች የዐረብ አገራትም ተገንጣዮቹን (ጀብሃ፣ ሻብያ፣ ኦነግ፣ ኦብነግ…) ሲደግፉ፤ ከእንግሊዝ ሊግ የቀጠነ ተሰሚነት ያለው ‹‹ዐረብ ሊግ›› አባሏ ሱዳንም፣ በድኀረ ኢዴኀ መሪዎችን ስደት ትሕነግን ወደመደገፍ አዘንብላለች። ተዘግተውበት የነበሩት የማስተባበሪያ ቢሮዎቹም እንዲከፍቱ ፈቅዳለች።
–
በርግጥ ይህም ሆኖ ሱዳን ቀርቶ፤ ድፍን ዓለም ቢደገፈው እንኳ ያለ ወልቃይት የትም አለመድረሱ አልጠፋውም። ዘግይቶም ከኤርትራ ድርጅቶች ሲቃቃር፣ ወደ ሱዳን መመላለስ የቻለው ወልቃይትን እንደ ዘንዶ በመጉረሱ ነው። እዚህ አካባቢ በነበሩ ጦርነቶች ከኢዴኀ፣ ከኢሕአፓና ከደርግ ተደጋጋሚ ጥቃት ደርሶበታል፤ ድርጅቱን ወደኋላ የጎተቱ ሽንፈቶችን ጭምር አስተናግዶበታል፡፡ መሪዎቹና ‹አሉኝ› የሚላቸው ተዋጊ ኃይሎቹ ወድቀዋበታል። ይህም ሆኖ ይች የ‹ገነት በር› በእጁ ካልገባች በቀር፤ ዙሪያው ገሀነም እንደሆነ ጠንቅቆ በመረዳቱ፣ ያለ የሌለ ኃይሉን ወልቃይት ላይ አስፍሮ ተናንቆባታል። ከማይታረቃቸው ጋር ታርቆ፣ ከማይደራደራቸው ጋር ተደራድሮ፣ ያለውን ሁሉ ለወልቃይት ገብሮ ነጥቋታል።ከዚህ በኋላ ሁሉ በእጁ፣ ሁሉ በደጁ ሆነለት፡፡ በትግራይ ከሚከሰተው ድርቅ ባሻገር፤ ማፈግፈጊያም፣ መደበቂያም፣ መተላለፊያም አድርጓታል። ኢሕዴንን እንደ ኮዳው ከጎኑ ሽጦ፣ ራሱን ‹የግንባር ቀደሞች ስብስብ› አድርጎ የቆጠረው “ኢሕአዴግ”ን በአምሳሉ ከፈጠረ በኋላ ደግሞ፣ ወደ ሱዳንም ሆነ ወደ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ለመስፋፋት ብቸኛ ወደቡ ነበረች። በአካባቢው ትሕነግን የተቃወመ ሁሉ የዘር ጭፍጨፋ ሰለባ ሆኗል። እንደ አቶ ገብረመድኀን ምስክርነት፡
–
‹‹የወልቃይት ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋትና የግዛት ማካለል የጀመረው በ1970ዎቹ መግቢያ ነው፡፡ ሕወሓት፣ ወልቃይቶችን ‹ወደ ትግራይ ልትጠቃለሉ ነው› ሲላቸው ‹አምቢ› በማለታቸው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የኃይል እርምጃ እየወሰደ ሕዝቡም በግድ ተያዘ፡፡››–ትሕነግ ሥልጣን ከጨበጠ በኋላ ከአዲስ አበባ ካጋበሰው ሀብት ባልተናነሰ ወልቃይት ጠገዴ ጠቅሞታል። ምድረ-በዳ ከሆኑ የትግራይ አካባቢዎች በርካታ ሕዝብ አምጥቶ አስፍሯል። ያሰናበታቸውን ከ30 ሺህ በላይ ታጋዮችም ከእነ ትጥቃቸው በወልቃይት ጠገዴ “ዲቪዥን” ብሎ በሰየመው መሬት መርቷል። በነገራችን ላይ ይህ ቦታ መጀመርያ ለትሕነግ ብቻ ሳይሆን፤ ከኢሕዴንም ለተቀነሱ ታጋዮች እንዲውል የተወሰነውን ሽሮ፣ የራሱን ብቻ በማስፈር “ዲሞግራፊ” ቀይሮበታል። ከሱዳንና ከሌሎች አገራት የተመለሱ ትግርኛ ተናጋሪ ስደተኞችንም እዚሁ እንዲሰፍሩ ያደረገው በዘላቂነት የአካባቢውን የሥነ-ሕዝብ ስብጥር ሚዛን በማሳጣት ለመጠቅለል አስልቶ እንደሆነ ግልጽ ነው።
እነዚህ አካላት ከወልቃይት ባሻገር ወደቀሪው የዐማራ ክፍል ተስፋፍተው መሬት እንዲይዙ፣ እንዲነግዱ ተመቻችቶላቸውም ዋነኛ የካድሬና የስለላ መዘውሮች ሆነዋል።አራት ኪሎን ከረገጠ በኋላም ወልቃይት ጠገዴን እንደ ትልቅ የፖለቲካ ቁልፍ ተጫውቶባታል። ትግራይን እስከ ቤንሻንጉል የሚያሳርሰውና በአንድ ወቅት ሆን ተብሎ በኢቲቪ የቀረበ ተስፋፊ ካርታ በስህተት የተሳለ አልነበረም። በሌላ በኩል ደግሞ በቀሪው የዐማራ ክፍል፣ በተለይም አብራጅራ፣ አብደራፊ መተማ፣ ቋራን ከዐማራ ክፍል ለመነጠል ብዙ ርቀት ተጉዞ ነበር፡፡ የኢሕዲን መካከለኛ አመራሮችና የአካባቢው አስተዳደሮች፣ ትሕነግ እነዚህን አካባቢዎች ለመዋጥ መስገብገቡን ተረድተው ቋራና መተማን ወደ ቤኒሻንጉል ከመጠቅለል እንዳዳኗቸው ዘግይቶም ቢሆን የሰማነው እውነታ ነው፡፡ አብደራፊና አብራጅራን በመሳሰሉ የምዕራብ አርማጭሆ ለም መሬቶች ዙሪያ፣ በሰፋፊ እርሻ ልማት ስም እነ አባዲ ዘሙ ተቆጣጥረውት ኑረዋል፡፡ ከኢፈርት ገንዘብ ተበጅቶ፣ በልማት ባንክ የብድር እገዛ ከወልቃይትም ባለፈ፤ በሱዳን አዋሳኝ ድንበር የሚገኙ የዐማራ ክፍሎችን እነ ስናር፣ ሙሽራ ቀለም፣ በረከት፣ ኑሪ ማዶ ከረደም፣ አፍቴራ ወዘተ መዘጋ መሬቶችን ለመቆጣጠር ብዙ ጥሯል፡፡ አሁን በሱዳንና በኢትዮጵያ ‹የደንበር ውዝግብ መነሻ ናቸው› የሚባሉትም እነዚና ሌሎች ቦታዎች የግጭት ቀጠና ሆነው እንዲቀጥሉ ብዙ ሠርቶባቸዋል፡፡ ዐማራውን ከጎረቤት አገራት አዋሳኝ ደንበር የመነጠል ሙከራው ወልቃይትን በመንጠቅ ብቻ አልነበረም፡፡ ቤኒሻንጉል ጉምዝን ከትግራይ የሚያዋስን ካርታ ገና 1983 አካባቢ በተፃፉ የታሪክ መጽሐፍት ጭምር የተካተተው እንደሚባለው ለ”ታላቋ ትግራይ” አጀንዳ ብቻ ሳይሆን፤ ዐማራውን፣ ከጅቡቲም፣ ከሱዳንም፣ ከኤርትራም አቆራርጦ፣ በሁሉም ረገድ የተከበበና ከጎረቤት አገራት የማይገናኝ ደሴት የመፍጠር ሴራው ነው።
–
ያኔ በትጥቅ ትግሉ ጊዜ፣ ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ ወይንም ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ እየተመላለሱ ይታገሉ የነበሩት ታጣቂዎች ዋነኛ መያዢያቸው ወልቃይት እንደነበረች ስናስታውስ፣ ግዛቲቷ በምድሪቷ ከታቀፈቻቸው በረከቶች ባሻገር፤ ገዥ መሬትነቷን ያስረግጥልናል።የኢትዮጵያ ፖለቲካ አንደኛው መፍቻ ቁልፍትሕነግ ወደ መቀሌ ከተሸኘ በኋላ፣ ዋነኛ መስመሩ ወልቃይት ሆናለች። በትግሉ ዘመን ወልቃይት ጠገዴን ለመያዝ በሚጥርበት ወቅት መሞቻው እንደነበረች፣ በቅርቡም መታነቂያው ስለመሆኗ ምልክቶች ታይተዋል። ወጣቶች እነ ክንፈ ዳኘውን ማርከው ለፌደራል መንግሥቱ መስጠታቸው አይዘነጋም። ወልቃይት ከእጁ ጨርሳ የወጣች ጊዜ ደግሞ የእዚህ ወንበዴ ቡድን መሪዎች መጨረሻ ምን ሊሆን እንደሚችል አመላካች ነው፡፡ የ‹‹Prisoners of Geography›› መጽሐፍ ደራሲ Tim Marshall ዝነኝነትን በታረፈበት በዚህ ሥራው፣ የአገራት የጥንካሬ ምንጭ መልከዐ-ምድራዊ አቀማመጣቸው ስለመሆኑ ቱርክን፣ ሩሲያን… እንደ አብነት በመጥቀስ ይተነትናል፡፡ ኢትዮጵያንም ከዐባይ ወንዝ ጋር በተያያዘ ደጋግሞ ይጠቅሳታል፡፡ ከፌዴራል መንግሥቱ በተቃራኒ መቆምን እንደ መታገያ ስልት ያደረገው ትሕነግ፣ ከግብጽ አጋርነትን ፈጥሮ አገር የሚያተራምሰውም ሆነ ሕገ-ወጥ የውጭ ግንኙነቶችንና ጉዞዎችን የሚያሳልጠው በወልቃይት ነው፡፡ በሰኔ 2010 ዓ.ም ትግራይ ያለውን ኦፕቲካል ፋይበር ከማዕከል ያለውን ግንኙነት በመቁረጥ፣ ከሱዳን ጋር ለማገናኘት ጥረት ያደረገውም በዚሁ መስመር ነው፤ (ይህን የአገር ክህደት ወንጀል ለመፈጸም ሲሞክር የፌዴራል መንግሥት በደረሰው መረጃ መሠረት ሊቋረጥ ችሏል፡፡)ከትግራይ በየዐመቱ ለብሔራዊ ባንክ ለሽያጭ ይቀርብ ከነበረው 1000 K.G ውስጥ 100 K.G ብቻ እንዲቀርብ በማድረግ 900 K.G ትግራይ እንዲከማችና ሲፈልግ በሱዳን በኩል በኮንትሮባንድ እንዲወጣና እንዲሸጥ ለማድረግ እየተሠራበት ያለው በዚሁ በወልቃይት መስመር ነው። ትሕነግ የራሱን የእህል ምርት እና ወርቅ ክምችት እየፈጠረ ቢሆንም፤ የፋይናንስ አቅምን ከማሳደግ አኳያ በርከት ያለው ወርቅ በሱዳን በኩል እንዲወጣ በማድረግ በኮንትሮባድ ንግድ ተዘፍቆ አገር ሚተራምሰው ወልቃይትን ይዞ ነው፡፡ Tim Marshall ከላይ በተጠቀሰ መጽሐፉ እንደሚለው የአገራት መልከዐ-ምድራዊ አቀማመጥ ፖለቲካዊ ዋጋቸውን ከፍና ዝቅ ያደርገዋል፡፡ የትሕነግን ጉልበት የጨመረው በኃይል የተቆጣጠረው የወልቃይት ግዛት እንጂ፣ የዐድዋ ተራሮች አይደሉም፡፡ ባለፉት ሁለት ዐመታት የአገር ክህደት ወንጀሎች መቀሌ ተጠንሰሰው፣ ወደ አገሪቱ የተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ኤክስፖርት የተደረጉት ከወልቃይት ነው፡፡ ትሕነግ ‹ኢትዮጵያን እወዳታለሁ› ሲልህም፤ በሱዳን ወርቅና ሰሊጥ፣ በዐማራ አሻጥር ኤክስፖርት ማድረጉን ነው፡፡ግንባሩ ወደ ሱዳን በወልቃይት በኩል እያለፈ በርካታ ጥፋቶችን ሲፈጽም ቆይቷል። አሁንም በዚሁ እየተሸጋገረ ሱዳን ውስጥ ሠራዊት ያሰለጥናል፤ ከዐማራ ክልል ጀምሮ እስከ ጋምቤላና ኦሮሚያ ድረስም ሰርጎ-ገብ ይልክበታል። ስንቅና ትጥቅ ያመላልስበታል።ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወልቃይትን መሰረት አድርገው ወደ ዐማራ ይስፋፉ የነበሩ የካድሬና የደሕንነት መዋቅሩ በከፊልም ቢሆን ቦታ አጥተዋል። አርማጭሆ፣ ቋራ፣ መተማና አካባቢው ያለ አግባብ ሰፋፊ መሬት ተሰጥቷቸው የነበሩ ሰዎቹ መጫወቻ ካርዳቸውን አጥተዋል። ይሁንና አሁንም በጦር መሳርያና በሌሎች ሕገ-ወጥ ንግዶች የሚያገኘውን ገንዘብ፣ ‹ብጥብጥ› ለተሰኘው ኢንቨስትመንቱ እያፈሰሰ ነው። በቅርቡ በወረርሽኙ ምክንያት የመተማ መስመር ሲዘጋ፣ በሁመራ ዞሮ ወደቀሪው ኢትዮጵያ እየገባ የሕገ-ወጥ ንግዱን ማፋፋሙን በድጋሜ አሳይቷል።ትህነግ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላም ከሌላው ከፍ ያለ አቅም ያለው ድርጅት ነው። ራሱን ‹‹የአቻዎች አውራ›› ያደረገ ንጉሠ-ነገሥት ‹ዮሀንስ አምስተኛ› ባይ ነው፡፡ አንድን ክልል ያለማንም ተቀናቃኝ ይዟል፤ ሚዲያውን ተቆጧጥሯል፤ የውጭ ግንኙነቱን ከራሱ ድርጅታዊ ጠቀሜታ አኳያ በመቅረጽ ተጠቃሚ ሆኖ ቆይቷል። ከማዕከላዊ መንግሥት በጀት እየተመደበለት፣ አንድን ክልል በ”ሕግ” አግባብ ይዞ፣ በይፋ ጦር እያሰለጠነ ያለ ጉደኛ የፌደራል መንግሥቱ ተቃዋሚ ነው። በታሪክ የትሕነግን ዐይነት ኃይልና ሕጋዊ ሽፋን የተጠቀመ፣ ተቋማትን የተቆጣጠረ ተቃዋሚ ስለመኖሩ ሰምቼ አላውቅም። በፈላጭ-ቆራጭ ዘመኑ ያካባተውን አቅም በመጠቀም ወልቃይትን ትልቅ የጂኦ-ፖለቲክስ ኮሪደር አድርጓታል፡፡ በዚህ በኩል አልፎ የሚያገኘው ሱዳንን ብቻ አይደለም፤ ግብፅንም ይጨምራል።‹የውድቀቴ ምክንያት ነች› የሚላትን ጎንደርን ለማንደድ የሴራ ማውጠንጠኛው ‹አክሱም ሆቴል ቢሆንም፤ ስምሪቱ በወልቃይቶቹ የማይካድራና ዲቪዥን መንደሮች ነው፡፡ የታሪክ ዋቢዎቹ እንደተጠበቁ፤ የኢዴኀ መስራቹ የትግራዩ መስፍን ልዑል ራሥ መንገሻ ስዩም ‹‹የትግራይ ወሰን ተከዜ ነው›› ሲሉ የመሰከሩበት ዐውድ፣ ወልቃይት ከትግራይ የምትለየው በተፈጥሮ ወንዝ እንደሆነ ያስረግጣል።ይች ቁልፍ መሬት ከእጁ ከወጣች እንደ እልፍኙ የሚመላለስባት ሱዳን ቀርቶ፣ ወደሌላው የኢትዮጵያ ክፍል የሚሰርግበት እድል በብዙ እጥፍ ይቀንሳል። ዐማራውም ሆነ ኢትዮጵያ ከኤርትራ የሚገናኙበት አንደኛው በር የወልቃይት መስመር ነው። ይህ መስመር በትሕነግ ባይያዝ ኖሮ፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ ቢያንስ “ለውጥ” ከተባለ በኋላ ጥሩ የንግድ ግንኙነት ማድረጉ በቀለላቸው ነበር። ዐማራውና ኢትዮጵያ ከሱዳንና ከኤርትራ መወዳጀታው ጥሩ ነው። ወቅታዊው የሱዳን የሽግግር ልዓላዊ ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት አያያዝ ወለም ዘለም ያለ ስለመሆኑ ግልፅ ሆኗል። ከኤርትራም ሆነ ከሱዳን ጋር ያለው ግንኙነት መልካም ሆኖ ከቀጠለ ዐማራውና ኢትዮጵያ የሱዳንንም ሆነ የኤርትራን ወደቦች ለመጠቀም እድላቸው ከፍ ሲል፤ ትሕነግ የፈጠረው ሕገ-ወጡ የንግድ ኢምፓየር ደግሞ እየሟሸሸ ይሄዳል፡፡ ዛሬ እንደ ግልኮስ የዕድሜ ማራዘሚያ ሆና እያገለገለችው ያለችው በወረራ የነጠቃት ወልቃይት ነች፡፡ግልኮሱ ከተነቀለ፣ እስትንፋሱ ተቋርጦ ወደማይቀርበት ይሰናበታል። የነገደበት ግራ-ዘመም ከንስሀ የተጣረሰ ነውና፣ የዚያኛው ዓለም ምድቡ በስተግራ መሆኑ አይቀሬ ይሆናል፡፡መደምደሚያወልቃይት ጠገዴ በፖለቲካ ቋንቋ ‹‹Safety Valve›› መተንፈሻ በሩ ነች። የሽብር ሠራዊት ማሰልጠኛው፣ በሱዳን በኩል ወደተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ኃይል ማሰማሪያው ነች። እንዲሁም ዐማራው ከኤርትራ እንዳይገናኝ መዝጊያው፣ ከሱዳን ጋር መልካ ግንኙነት እንዳያኖረው ሴራ የሚፈትልበት፣ የፌዴራሉን መንግሥት የውጭ ግንኙነት ለማበላሸት የሚመላለስበት… ዘርፈ-ብዙ መስመሩ ነው፡፡በሕገ-ወጥ የተጠቀለለው ወልቃይት ጠገዴን ማስመለስ መንታ ጠቀሜታ አለው፡፡ ቀዳሚው የተጣመመውን ሕግ አርሞ ለታሪካዊ ባለቤቱ ፍትሕን መስጠቱ ሲሆን፤ ተከታዩ ደግሞ ወደ ዐማራውም ሆነ ወደ ሌሎቹ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚሰጠውን የሽብር ስምሪት ይታደጋል፡፡ ይህን መሰረቱን ካጣ በቀላሉ የሚናድ የእምቧይ ካብ ስለመሆኑ በበዛ እርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ዐማራውንም ሆነ ቀሪውን የኢትዮጵያ ክፍል በመረበሽ ወደ ማዕከላዊ መንግሥት ለመምጣት የሚያደርገውን ጥረት የሚጨናግፈው በቸኛ መንገድ በዚህ በኩል ነው። እንደ አገር ሱዳንና ግብፅን፣ እንደ ቡድን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ፅንፈኞችን በሙሉ በመደገፍ በኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ አፋር፣ ሶማሊ ለመፍጠር የሚፈልገው ትርምስንም መግታቱን ያቀለዋል።በአንፃሩ ከድሮው የተሻለ ኃይል ያለው ትሕነግ የወረረውን ወልቃይት ጠገዴ ይዞ እንዲቀጥል በምንግዴ ከታለፈ፤ ግብፅና ሱዳንን ወደ ኢትዮጵያ ፖለቲካ እየጎተተ በምስራቅ አፍሪካ አንፃራዊ መረጋጋት የነበራትን አገር በትኖ ወደ እነ ሶማሊያ ሰልፍ ማስገባቱ አይቀሬ ነው። ይች ኮሪደር ለሥልጣን መወጣጫው ቁልፍ የነበረችውን ያህል፣ ለውድቀቱም ‹‹ስስ ተረከዙ (Achilles Heel)› ነች:: ለኢትዮጵያም ይሁን ለምስራቅ አፍሪካ መረጋጋት፤ እንዲሁም ለኢኮኖሚያዊ ውህደት የመዘጋ መሬት ባለቤቷ ወልቃይት ትልቅ ሚና አላት፡፡የተከዜ ፖለቲካ ቋጠሮ የሚፈታው፣ ‹ቤት ለባለቤት› በሚለው ብያኔ ብቻ ነው፡፡
