የትግራይ ልዩ ኃይል መኪኖች

በትግራይ ክልል ከተቀሰቀሰ ከአንድ ሳምንት በላይ በሆነው ጦርነት ተሳታፊ የሆኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎች መሞታቸውን እየወጡ ያሉ መረጃዎች አመለከቱ።

በሰሜን ዕዝ ላይ ተፈጸመ የተባለውን ጥቃት ተከትሎ ለወራት በውዝግብ ውስጥ የቆዩት የፌደራል እና የትግራይ ክልል መንግሥት ጥቅምት 24/2013 .ም ወደ ግልጽ ጦርነት ውስጥ በመግባታቸው በርካታ ተዋጊዎች መሞታቸውን ከአካባቢው በተለያዩ ምንጮች አማካኝነት የሚወጡ መረጃዎች እያመለከቱ ነው።

በተለይ ባለፉት ቀናት በምዕራብ ትግራይ በተካሄደው ውጊያ 550 ያህል ታጥቂዎች መገደላቸውንና 29 የልዩ ኃይል እና ሚሊሻ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የሰሜን ዕዝ ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል በላይ ስዩም መናገራቸውን ፋና ዘግቧል።

ከዚህ በተጨማሪ ሮይተርስ ያናገራቸው አንድ የፌደራል መንግሥቱ ወታደራዊ ባለስልጣን እንዳሉት ከቀናት በፊት ቅራቅር ውስጥ በነበረ ውጊያ ከትግራይ በኩል ወደ 500 የሚጠጉ ተዋጊዎች መገደላቸውን አመልክተዋል።

እንዲሁም ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የሚሰሩ በአማራ ክልል የሚገኙ ሦስት የደኅንነት ምንጮች የፌደራሉ ሠራዊት በመጀመሪያ ዳንሻ ላይ በነበረው ውጊያ በመቶዎች የሚቆጠሩትን እንዳጣ እንደነገሩት ሮይተርስ ዘግቧል።

በጦርነቱ ከሞቱት በተጨማሪም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተዋጊዎች መቁሰላቸውንና ይህም አሃዝ እየጨመረ መሆኑን ኤኤፍፒ ዜና ወኪል ያመለከተ ሲሆን፤ ከህክምና ተቋማትና ከእርዳታ ሠራተኞች አገኘሁት ባለው መረጃም ከ200 በላይ ወታደሮች መቁሰላቸውንና 8 እንደሞቱ ሰኞ ዕለት ዘግቧል።

ጦርነት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች የግንኙነት መስመሮች በመቋረጣቸው በጦርነቶቹ የደረሰ የጉዳት መጠንን በትክክል ለማወቅ አዳጋች ነው ተብሏል።

ነገር ግን ሮይተርስ ያናገራቸው አንድ ዲፕሎማት በሰጡት በሰጡት ግምት በተካሄዱት ውጊያዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎች መሞታቸው እንደሚታመን አመልክተዋል።

ጦርነቱ በተዋጊዎች ላይ አስከተለ ከተባለው ጉዳት ባሻገር በሽሽትና በመፈናቀል ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን የገቡ ሰዎች እንዳሉ የዜና ምንጮች እየዘገቡ ነው።

በዚህም መሰረት ኤኤፍፒ የዜና ወኪል በሺህዎች የሚቆጠሩ ግጭቱን የሚሸሹ ወደ ሱዳን መሻገራቸውንየሱዳን ስደተኞች ድርጅት ኃላፊ የሆኑትን አልሲር ኻሊድን ጠቅሶ ዘግቧል።

ሮይተርስ በበኩሉ የሱዳን መንግሥት መገናኛ ብዙሃንንና ነዋሪዎችን ጠቅሶ እንዳለው ወታደሮችን ጨምሮ በትግራይ ክልል ውስጥ እየተባባሰ ያለውን ግጭት በመሸሽ ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን ገብተዋል ብሏል።

ባለፈው ሳምንት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተቀሰቀሰው ወታደራዊ ግጭት ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ ከባድ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል ብለው የሰጉ አህጉራዊና ዓለማቀፋዊ ተቋማት ሰላም እንዲወርድ ተደጋጋሚ ጥሪ አድርገዋል።

ይህንንም ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት የተለያዩ ወገኖች ኢትዮጵያ ወደ ትርምስ ትገባለች የሚለው ስጋታቸው የማይሆንና የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ በጥልቀት ካለመረዳት የሚመነጭ ነውብለዋል።

ጨምረውም በአገሪቱ ሠራዊት እየተከናወነ ያለው ዘመቻ ሕግ የማስከበር ሥራ መሆኑን አመልክተው ሰላምንና መረጋጋትን በማስፈን ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ ያለመ ነውበማለት፤ ይህም ተልዕኮ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ አመልክተዋል።

አሁን ወደ ጦርነት የተሸጋገረው በፌደራል መንግሥቱና በትግራይ ክልል መስተዳደር በኩል የነበረው ቅራኔ እየተባባሰ የመጣው ባለፈው ዓመት ሊካሄድ የታቀደው ምርጫ በኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት እንደማይካሄድ ከታወቀ በኋላ በትግራይ የተናጠል ምርጫ በመደረጉ ሳቢያ ነው።

ይህንንም ተከትሎ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምርጫውን ሕገወጥና ተፈጻሚነት የሌለው እንደሆነ መወሰኑን ተከትሎ ማዕከላዊው መንግሥት ከክልሉ መስተዳደር ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንዳያካሂድና የበጀት ድጋፍ እንዳይሰጥ ከወሰነ በኋላ ነገሮች እየተካረሩ መሄዳቸው ይታወሳል።

ይህ ጦርነትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በብሔራዊው ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው እስካሁን የደረሰው የጉዳት መጠን በይፋ ያልተነገረለት ጥቃት በትግራይ ልዩ ኃይል በሰሜን ዕዝ ላይ መፈጸሙን ከገለጹ በኋላ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማዘዛቸውን ተከትሎ ነው።

ይህንንም ተከትሎ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በትግራይ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የደነገገ ሲሆን የተወካዮች ምክር ቤትም ውሳኔውን ተቀብሎ ማጽደቁ ይታወሳል።

በተጨማሪም የፌዴሬሽን ምክር ቤት በትግራይ ክልል የተከሰተውን ሁኔታ ተከትሎ የፌደራል መንግሥት በክልሉ ውስጥ ጣልቃ እንዲገባና ክልሉን የሚመራ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ወስኗል

ቢቢሲ