ከ 2 ሰአት በፊት

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አራተኛ መደበኛ ስብሰባ የሰላሳ ዘጠኝ (39) ግለሰቦችን ያለመከሰስ መብት ማንሳቱ ተገለጸ።
ምክር ቤቱ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በተለያዩ ወንጀሎች የጠረጠራቸውን የእነዚህን ግለሰቦች ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ ያቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ ነው የውሳኔ ሐሳቡ በሙሉ ድምጽ ያፀደቀ።
በዚህም መሰረት የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንትና የህወሓት ሊቀመንበር የሆኑት ደብረጽዮን ገብረሚካኤልን (ዶ/ር) ጨምሮ የ39 ግለሰቦች ያለመከሰስ መብት ተነስቷል።
ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ ከተደረገባቸው ግለሰቦች መካከል ከፍተኛ የህወሓት አመራሮች የሚገኙበት ሲሆኑ ከእነሱም መካከል አቶ አስመላሽ ወልደሥላሴ፣ አቶ አባይ ፀሐዬ፣ ዶክተር አምባሳደር አዲስዓለም ቤሌማ፣ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ አቶ አፅበሃ አረጋዊ፣ አቶ ገብር እግዚአብሄር አርአያ እና ሌሎችም ይገኙበታል።
ዐቃቤ ሕግ ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ የጠየቀባቸው ግለሰቦችን ጦር መሳሪያ ይዞ በማመፅ፣ የአገር መከላከያ ሠራዊትን በመውጋት እና በሌሎችም ተያያዥ ወንጀሎች ዋና አድራጊነት የተጠረጠሩ መሆናቸው ተገልጿል።
- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በትግራይ ክልል ላይ የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፀደቀ
- የፌዴሬሽን ምክር ቤት በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ወሰነ
- ሕይወት በጦርነት ቀጣና ውስጥ በምትገኘው መቀለ
የፌደራል መንግሥት የትግራይ ክልልን በሚመራው ህወሓት አማካይነት በሰሜን ዕዝ ስር በሚገኘው የአገሪቱ ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈጸሙን ጠቅሶ “ሕግን ማስከበር” ያለውን ወታደራዊ እርምጃ እየወሰደ መሆኑ ይታወቃል።
በዛሬው ዕለት በአገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው ትግራይን የሚያስተዳድረው የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ሲሆኑ ለወራት ከማዕከላዊው መንግሥት ጋር በውዝግብ ውስጥ ቆይተዋል።
በተለይም በኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ የተደረገውን አገራዊ ምርጫ በመቃወም በትግራይ ክልለ ክልላዊ ምርጫ እንዲካሄድ ማድረጋቸው በሁለቱ አካላት መካከል የነበረውን አለመግባባት አባብሶታል። የተደረገውን ክልላዊ ምርጫ የፌዴሬሽን ምክር ቤት “ሕገወጥና ተፈጻሚነት የሌለው” በማለት ውድቅ ያደረገው ሲሆን በክልሉ መስተዳደር ላይ ተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዱም ይታወሳል።
የፌደራል መንግሥቱ ሕግ ማስከበር ባለውና ከሳምንት በፊት በክልሉ ባሉ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ተከትሎ በትግራይ ክልል ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከመታወጁ በተጨማሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም መወሰኑ ይታወሳል።