November 12, 2020

“የመገንጠል ፖለቲካ መቆም አለበት”- (አቶ ገብሩ አስራት፤ አንጋፋ ፖለቲከኛ)

 “የመገንጠል ፖለቲካ መቆም አለበት”-

addisadmassnews

(አቶ ገብሩ አስራት፤ አንጋፋ ፖለቲከኛ) – እንደ ዜጋ ሁለት ነገሮች በእጅጉ ያሳስቡኛል፡፡ አንዱ ጦርነት ነው፡፡ ጦርነት ሀገርን ያጠፋል፤ ዜጎችን ይበላል፡፡ ዝም ብሎ ጨዋታ አይደለም፡፡ በየትም አቅጣጫ ጦርነት ጎጂ ነው፡፡ አሁን ላይ የምንሰማው “ግፋ በለው” መልካም አይደለም። በትግራይ አስተዳደርና በፌደራሉ መካከል ያለው ጦርነት በፍጹም የሚበረታታ አይደለም። አሁንም ማዕከላዊ መንግስቱ ጉዳዩን በጥበብ ለመፍታት መሞከር ያለበት፡፡ በጦርነት ችግር ለመፍታት መሞከር መቋጫ አይኖረውም፡፡ ቅራኔዎችም እየተባባሱ ነው የሚሄዱት፡፡ ጦርነትን ማንም መደገፍ የለበትም። በጦርነት የሚመጣ ለውጥ በዚህ ዘመን አይኖርም፡፡ ሁሉም አካል ይህን ሊገነዘበው ይገባል፡፡ በጦርነት የሚመጣ ዲሞክራሲ የለም።

ወደ ጦርነት መግባት ማለት ሀገሪቱን ወደማትወጣው አዘቅት መክተት ማለት ነው። ሁለተኛው አሳሳቢ ጉዳይ፣ ይሄ በሃገራችን በየጊዜው እየተነሳ ያለው መገንጠል የሚለው ፖለቲካ ነው። ይሔ የመገንጠል ፖለቲካ ጨርሶ መቆም አለበት፡፡ በተለይ በትግራይ አካባቢ ያለው የመገንጠል እንቅስቃሴ መቆም አለበት። መገንጠል በየትኛውም መንገድ መፍትሄ አይሆንም። የተፈጠረው የፖለቲካ ችግር ነው። ይህ የፖለቲካ ችግር መፈታት ያለበት በጦርነት ሳይሆን በፖለቲካ ውይይት ነው። ስለዚህ ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ መነጋገርን ማስቀደም ያስፈልጋል፡፡

መንግስት በተለያዩ አካባቢዎች ያፈነገጡ ሃይሎች ችግራቸው ምንድን ነው? ብሎ መመርመር አለበት፡፡ የሃይል እርምጃ የሚቀጥል ከሆነ አያዋጣም፡፡ በቅድሚያ ችግሩ ምንድን ነው? የሚለውን መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም ለመነጋገር ቅድሚያ መስጠት አለበት፡፡ የጦርነት መጨረሻውም ቢሆን፣ ብዙ እልቂት ተፈጥሮ ወደ መነጋገር ነው የሚገባው። አሊያም እልም ያለ መጠፋፋት ነው የሚያስከትለው፡፡ በዚህ ሁኔታ ምርጫውን ዘንድሮ መካሄድ የሚችል አይመስለኝም። የምርጫውን ጉዳይ ቆም ብለን አይተን፣ የሃገሪቱ ህልውና የሚቀጥልበትን መንገድ ነው ማስቀደም ያለብን፡፡ በመላ ሀገሪቱ ፈጽሞ ሰላም እስካልሰፈነ ድረስ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ አይቻልም፡፡

ስለዚህ ሁሉም አካላት በሃገሪቱ ቀጣይ እጣ ፈንታ ላይ ሊመሰክሩና ሊነጋገሩ ይገባቸዋል። ንግግር ሲባልም የእውነት መሆን አለበት። መጀመሪያ የጦር መሳሪያ ካነሱት ሃይሎች ጋር ነው መነጋገር የሚያስፈልገው፡፡ የውጭ አሸማጋይ አካላትም ተሳትፈውበት፤ እውነተኛ መፍትሄ መምጣት አለበት። ጦርነቱ አያዋጣም፤ ሁሉም ቆም ብሎ ማሰብ አለበት። አሁንም ለሃገሪቱ አጠቃላይ ችግር መፍትሄው እውነተኛ ውይይትና ድርድር ብቻ ነው፡፡ አስተዳደራዊ መፍትሄ ብቻውን ውጤት አያመጣም፡፡ ፖለቲካዊ መፍትሄም ያስፈልጋል፡፡ ሁሌም በጦርነት የሚሞተው የተላከው እንጂ ላኪው አይደለም፡፡ በጦርነት አንድም ሰው መሞት የለበትም።

(አቶ ገብሩ አስራት፤ አንጋፋ ፖለቲከኛ)


 ያልታሰበው ክስተት በትግራይ የቱ ይቀላል? ውይይት ወይስ ጦርነት?

በአገራችን ብዙዎች እንዳይከሰት ሲፈሩት የነበረው ጉዳይ ሰሞኑን እውን ሆኗል፡፡ የህወሃት ቡድን በትግራይ በሰፈረውና ህዝቡን ከ20 ዓመታት በላይ ሲጠብቅ በቆየው የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ያነጋገራቸው ያስታወቁት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ይህን ተከትሎም መንግስታቸው ህዝብንና አገርን ለማዳን ወደማይፈልገው ጦርነት እንዲገባ መገደዱን ገልፀዋል፡፡ ከዚህ በኋላም ከህወኃት ቡድን ጋር ውይይትና ድርድር እንደማይኖር ነው ጠ/ሚኒስትሩ ያስታወቁት፡፡ አሁንም ግን ከውጭም ከውስጥም ከሃይል ይልቅ ለውይይትና ንግግር ቅድሚያ እንዲሰጥ የሚወተውቱ ወገኖች አሉ፡፡

የአዲስ አድማሱ አለማየሁ አንበሴ ያነጋገራቸው ሃሳባቸውን እነሆ፡-

ግጭትና ጦርነት ለማንንም ወገን ተጠቃሚ አያደርግም፡፡ በጦርነት የሚፈታ ችግር ውጤቱ ያማረ አይሆንም፡፡ ጦርነት በምንም መንገድ መፍትሔ አይሆንም፡፡ ሆኖም አያውቅም፡፡ ችግሩ የፖለቲካ እንጂ የውጭ ሃይል ጉዳይ አይደለም፡፡ አሁንም ቢሆን በሆነ መልክ ሁኔታው መቋጨት አለበት፡፡ የትግራይም ይሁን በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ችግር በንግግርና በውይይት መፈታት አለበት ባይ ነኝ፡፡

ኢትዮጵያን በአጠቃላይ ለማረጋጋት ከተፈለገ፣ መነጋገርና መቀራረብ ነው ጠቃሚው። በሃይል የሚመጣ መረጋጋት በባህሪው ጊዜያዊ እንጂ ዘላቂ ውጤትም አይኖረውም። በውይይትና በመነጋገር የሚመጣ ሠላም ነው ዘላቂ ሊሆን የሚችለው፡፡ የትግራይ አስተዳደር ምን ፈልጐ ጦርነት ውስጥ እንደገባ አይገባኝም፡፡ ነገር ግን ሁለቱም አካላት አስቀድሞ መነጋገር ቢችሉ ይሄ ሁሉ ችግር ባልተፈጠረ ነበር። ህወኃቶች ጦርነቱን ለምን እንደፈለጉት ባናውቅም፣ በጣም ይወተወቱ ነበር፡፡

እንግዲህ ውጤቱን ወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡ ሲነዛ የነበረው ፕሮፓጋንዳ ጦርነቱ አይቀሬ እንደነበር ነው የሚያሳየው፡፡ ያው የፈለጉት ሆኖላቸዋል፡፡ መጨረሻው ምን እንደሚሆን አይታወቅም።

በጦርነት ዲሞክራሲ መጥቶ አያውቅም። ስለዚህ በሀገሪቱ ያሉ የሲቪክ ተቋማት፣ የእምነት አባቶችና፣ የሀገር ሽማግሌዎች በትግራይ ክልላዊ መንግስትና በፌደራል መንግስት መካከልም እንዲሁም በአጠቃላይ በሀገሪቱ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች በእውነተኛ ሀገራዊ ውይይት እንዲፈታ ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡

ሁሉም ወገኖች ወደ ውይይት እንዲመጡ ጥሪ ማቅረብ እንጂ በሁለቱም ወገን “ግፋ በለው” ማለት አያዋጣም፡፡ ሁላችንም ሀገር እንዲረጋጋ ነው መጮህ ያለብን፡፡ ለሁሉም ወገን የሠላም ጥሪ ነው እንደ ዜጋ ማቅረብ የምፈልገው፡፡
ሀገር ማዳን የሚቻለው በጦርነት አይደለም፡፡ ጦርነት አዋጭ የሚሆነው የውጭ ወራሪን ለመመከት ሲሆን ነው፡፡ በፖለቲካ ልዩነት ሳቢያ የሚደረግ ጦርነት ውጤቱ የተወሳሰበ ነው፡፡ ሁላችንም ይሄን በአስተውሎት ማጤን አለብን፡፡

Source –  https://www.addisadmassnews.com