November 12, 2020 – Abebe Bersamo

እስከአሁን በተደረገው አካባቢዉን ከሕወሃት ነጻ የማውጣት ዘመቻ ሁለት ሶስተኛ የሚሆነው የትግራይ ክልል ተብሎ ይቆጠር የነበረው ግዛት ነጻ ሆናል፡፡ በዚህ ከቀጠለ ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የትግራይ ሕዝብ ሙሉ ለሙሉ ከሕወሃት ግፈኛ አገዛዝ ይለቀቃል ተብሎ ነው የሚጠብቀው፡፡
ሕወሃት ስንል አካላዊዉን ሕወሃት ነው፤ እንጂ ሕወሃት እንደ መንፈስ አሁን በተለይም በኦሮሞ ብልጽግና አመራሮች ውስጥ መስረጹን መዘንጋት የለብንም፡፡ በስሜን እነ ዶር ደብረ ጽዩን ሽንፈት ቢከናነቡም፣ እነርሱ ያመጡትን የዘር ፖለቲካ፣ የዘር ሕገ መንግስት፣ የዘር አወቃቀር እንኳን ሊቀየር ያንን ለመቀየር የታሰበ ነገር ስለመኖሩ ትንሽ እንኳን ፍንጭ ከኦሮሞ ብልጽግና አካባቢ አይታይም፡፡ የሚመስለው ከድህረ ሕወሃት በኋላ፣ የህወሃት ፖለቲካና ሌጋሲ እንደሚቀጥል ነው፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ስላለው ሁኔታ ያገኘሁትን አንዳንድ አስደሳች፣ አሳዛኝም መረጃዎች ላቀብላችሁ ወደድኩ፡
ጦርነት አስከፊ ነገር ነው፡፡ “ወደ ጦርነት መኬድ የለበትም” ብለን ባለን አቅም ከፍተኛ ግፊት ስናደርግ ነበር፡ ነገሮች ግፍተነው ከሄዱም፣ ጦርነትን ያላከታተ፣ ሕወሃት ላይ ብቻ ያነጣጠረ፣ ቀጪ እርምጃዎች እንዲወሰዱ፣ ሕወሃትን እንደ አሸባሪ ደርጅት እንዲፈረጅ ነበር ስንጠይቅ የነበረው፡፡
ሆኖም ግን የፌዴራል መንግስቱ ሊሰማ አልቻለም፡፡ በተለይም ሕወሃት የፌዴራል ሕግን ጥሶ ምርጫ እስከማድረግ ሲደርስ፣ የፌዴራል መንግስቱ ቁርጠኛ አመራር መስጠትና ሕግን ማስከበር ሲገባው፣ ዳተኝነትን ነበር ያንጸባረቀው፡፡ እርምጃዎች ባለመውሰድ ፣ በሌላ አባባል ሕወሃት የበለጠ ጥፋት እንድታደረግ ነው የተበረታታችው፡፡
አሁን ይኸው ሕወሃት የሰሜን እዝ አባላት ላይ ጥቃት በመፈጸሟ፣ ምንም ምርጫ ስለሌለው፣ ፍላጎት ባይኖረውም ፣ የዶር አብይ መስተዳደር ወታደራዊ እርምጃዎች ለመውሰድ ተገዷል፡፡
ከሕወሃት ጋር ዉጊያ ከተጀመረ አስር ቀን አካባቢ ይሆነዋል፡፡ እስከ አሁን በአራት ቦታዎች ከፍተኛ ዉጊያዎች ተደርገዋል፡፡ ከዳንሻ በስተ ሰሜን ምእራብ ባለው፣ በአስር ሺሆች የሚቆጠሩ የቀድሞ የሕወሃት ታጋዮች እንዲሰፍሩበት በተደረገው ዲቪዥን ተብሎ በሚታወቀው ቦታ፣ በማይካድራና ሁመራ ፣ በአድዋ መግቢያ ላይ እና በአላማጣ አካባቢ ነው፡፡ በማይካድራ እጅግ አሳዛኝ እልቂት በሰላማዊ ዜጎች ላይ በሕወሃት ታጣቂዎችም ተፈጽሟል፡፡ ከ500 በላይ ሰላማዊ ዜጎች በማንነታቸው ተለይተው ተገድለዋል፡፡ ይሄንን የአማራ ክልል መገናኛ ብዙሃን በስፋት እየዘገቡት ነው፡፡ አምንስቲ ኢንተርናሽናልም ይሄን አረጋግጧል፡፡ ሆኖም የፌዴራል መንግስት ደረጃ የኢትዮጵያ ቲሌቭዦን ማይካድራን አለማንሳታቸው ብዙዎችን እያነጋገረ ነው፡፡
ኦነግና ሕወሃት ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳላቸው ማረጋገጫ አልነበረም፡፡ ሆኖም በሕወሃት ለመሰልጠን በቦታው የነበሩ የኦነግ ታጣቂዎች፣ ከሕወሃት ጋር ሆነው አርማቸውን ይዘው ይዋጉ እንደነበረ መገለጹ፣ ኦነግ በኦሮሞ ክልል እየፈጸመ ላለውም ጥፋት የሕወሃት ረጅም እጅ እንዳለበትም በግልጽ የሚያመላክት ነው፡፡
ወልቃይት ጠገዴና ካፍታ ሁመራ
ወልቃይት ጠገዴና ካፍታ ሁመራ ሙሉ ለሙሉ ማለት ይቻላል፣ ዲቪዥን ከሚባለው ቦታ በስተቀር፣ ከሕወሃት ነጻ ወጥቷል፡፡ በዚያ ያሉ የሕወሃት ልዩ ኃይል አባላት አብዛኞቹ እጆቻቸውን ሰጥተዋል፡፡በንብረትም ሆነ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የደረሰ ብዙም ጉዳት የለም፡፡
ከዳንሻ በስተ ሰሜን ምእራብ በሚገኘው ዲቪዥን ተብሎ በሚታወቀው ፣ በአስር ሺሆች የሚቆጠሩ የቀድሞ የሕወሃት ታጋይቾ እንዲሰፍሩ በተደረገበት አካባቢ ግን አሁንም ችግር አለ፡፡ በዚያ፣ ከሁሉቱም ወገን ህይወታቸው ያጡ አሉ፡፡ የሕወሃት ታጣቂዎችን፣ በሁሉም አቅጣጫ የተከበቡ በመሆናቸው፣ እጅ እንዲሰጡ የማግባባት ስራ እየተሰራ ነው፡፡ ታጣቂዎቹ እጅ የማይሰጡ ከሆነ የምድር ጦር ወደዚያ ልኮ ለማስለቀቅ በጣም አሰቸጋሪና ብዙ መስዋእትነት ሊያስከፍል ስለሚችል ፣ ምን አልባት ለዚያ አካባቢ፣ ምሽጎችን ለማፍረስ የአየር ኃይል ሊላክም እንደሚችልም ለአካባቢው ቅርበት ያላቸው ይናገራሉ፡፡
ጠለምት
በጠለምት፣ በማይ ጸምሪ ከጎንደር የሚመጣውን ዘመቻ ለመከላከል ሕወሃት ከፍታዉን ቦታ በመያዝ ከፍተኛ ምሽግ እንደሰራች መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ሆኖም ግን መከላከያ በጎንደር፣ ዳባት በኩል ስምሪት እያደረገ ያለ አይመስልም፡፡
በተቃራኒው በሽሬ በመነሳት ጠለምትን በቀላሉ ነጻ ለማውጣት እንቅስቅሴዎች ተጀምረዋል፡፡ ማይጸምሬም ያለው የሕወሃት ኃይል እጅ ከመስጠት ወይም ከማለቅ ውጭ ምንም አማራጭ አይኖረውም፡፡ በመሆኑም በቅርቡ እነ ማይጸምሪ ሳይቀር እንዳለ ጠለምት ከሕወህት ነጻ ወጣ ብንባል መረገም የለብንም፡፡
ሽራሮች፣ ሽሬ፣ አክሱም፣ አድዋ መስመር
በጀነራል አበባው ታደሰ የሚመራው የመከላከያ ጦር ከሽራሮ በመነሳት፣ ሽሬ፣ ከዚያም አክሱምን ተቆጣጥሯል፡፡ በሁለቱም ታላላቅ ከተሞች ዙሪያ ተሰማርተው የነበሩ የትግራይ ልዩ ሃይል አባላት ብዙዎቹ እጆቻቸውን የሰጡ ሲሆን፣ እጅ ያልሰጡት ጥቂቶች ተገድለዋል፡፡፡
በአክሱም ሆነ በሽሬ ከተሞች ውስጥ ፣ምንም አይነት ውጉያ አልነበረም፡፡ የመከላከያ ሰራዊት የልዩ ኃይላትን በሙሉ ትጥቅ በማስፈታት፣ የከተሞች መደበኛ ፖሊሶች ጋር በመሆን በከተሞዎች ያሉ የወረዳ አስተዳዳሪዎች ፣ ለመከከላከያ ሪፖርት እያደረጉ፣ እንደበፊቱ ማስተዳደራቸው እንዲቀጥሉ ተደርጓል፡፡
ከአክሱም ቀጥሎ ያለችው ትልቋ ከተማ የነ ስብሃት ነጋ ፣ የነ መለስ ዜናው አገር አድዋ ናት፡፡ በአክሱምና በአድዋ መካከል ፣ ከአድዋ ወደ 14 ኪሎሜትር ርቅት ላይ ማይከድራ/ሁመራ የነበረው አይነት ከፍተኛ ዉጉያ ተደርጎ በዚያ ሕወሃት ተሰብራለች፡፡ አድዋ እድነ ሽሬና አክሱም ሙሉ ለሙሉ ከሕወሃት ነጻ ሆናለች፡፡
የአድዋ ነጻ መውጣትን ተከትሎ በዚያ ያለው ጦር ስምሪቱ ወደ ደቡብ ወደ ተንቤን አቢ አዲ ይሆናል ተብሎ ነው የሚጠበቀው፡፡ በርካታ የሕወሃት አመራሮች በተንቤን ባለ፣ ያኔም በደርግ ጊዜ ዋና የጦር ማዘዣ ጣቢያቸው በነበረበት ዋሻ፣ ከቅልብ ታማኝ ጦራቸው ጋር ተደብቀው ነው የሚገኙት የሚል አንዳንድ ዘገባዎች እየተናፈሱ ነው፡፡
ቆቦ፣ወጅ፣ አላማጣ መስመር
ከቆቦ ወደ መቀሌ በሁለት መስመር መሄድ ይቻላል፡፡ አንደኛው በድሮው መንገድ ነው፡፡ ቆቦ፣ ዋጅ፣ አላማጣ፣ ኮረም፣ ምይጨው፣ አምባላጌ፣ እንዳ መድሃኔላም፣ ሕዋኔ፣ ማይቀዪ አድርጎ መቀሌ የሚገባ ነው፡፡ ይህ መስመር እጅግ በጣም አስቸጋሪ፣ በርካታ ተራራዎች ያሉበት መስመር ነው፡፡
ሌላው ይሄን መስመር በማለፍ ወደ ምስራቅ ወደ ቆላው ወረድ በማለት የተሰራ፣ አላማጣ ላይ ተገንጥሎ ህዋኔ ላይ ከድሮው መንገድ ጋር የሚገጥም አዲስ መንገድ አለ፡፡ ያንን መንገድ መከላከያ እንዳይዝ የሕወሃት ታጣቂዎች እጅግ በጣም ከፍተኛ ኃይል ዋጅና አላማጣ አሰማርተው እየተዋጉ ነው፡፡ እዚያ አካባቢ ከፍተኛ የአየር ኃይል ድብደባ እየተደረገ ነው፡፡ በተለይም የሕወሃት ልዩ ኃይል የግራካሱን ተራራ ላይ ከፍተኛ መሳሪያ ደቅኖ ከፍተኛ ጉዳት እንዳያደርስ፣ በተራራው ላይ ከፍተኛ የአየር ጥቃት ተፈጽሟል፡፡
ሕወሃት በራያ ላሰማራቸው ታጣቂዎቹ ምግብ ማድረስ ስላልቻለ ብዙዎች በረሃብ ግንባሩን ጥለው እየሄዱም ነው፡ በጥቂት ቀናቶች ውስጥም እነ አላማጣ ከሕወሃት ነጻ ይወጣሉ ተብሎም ነው የሚጠበቀው፡፡ መከላከያ አላማጣን ነጻ አወጣ ማለት ደግሞ በደቡብ በኩል መቀሌ ደጃፍ ተደረሰ ማለት ነው፡፡
ዛለአንባሳ አዲግራት መስመር
መከላከያ ከዛላንበሳ በመነሳት ወደ አዲግራት እየዘመተ ነው፡፡ አዲግራት የአቶ ስዩም መስፍን የትዉልድ ቦታ ናት፡፡ አዲግራት በአጋሜ አውራጃ ውስጥ ያለች ሲሆን፣ ላለፉት 28 አመታት በሕወሃት አገዛዝ የተረሳች ከተማ ናት፡፡ በተለይም ከኤርትራ ጋር በነበረው ችግር፣ ከአዲስ አበባ አስመራ ባለው መስመር ትልቅ በር የነበረችው አዲግራት እጅግ በጣም በኢኮኖሚ እንድትወድቅ የተደረገበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡
የሕወሃት መወገድ፣ ከኤርትራ ጋር ሰላም መሰፈን ምክን ያት በአንደኛ ደረጃ ደሰተኛና ተጠቃሚ የሚሆነው የአዲግራት በአጠቃላይ የአጋሜ አእራጃ ሕዝብ ነው፡፡
መከላከያ አዲግራትን ከተቆጣጠረ በኋላ ጉዞው በዉቅሩ አድርጎ ወደ መቀሌ ነው የሚሆነው፡፡
መቀሌ
አላማጣ ከተያዘች የመከላከያ ሰራዊት በደቡብ ከአላማጣ በስሜን ከአዲግራት ወደ መቀሌ ይገሰግሳል፡፡ አንዳን መረጃዎች እንደሚጠቁምት ግን መቀሌ ያለችበት ፣ ከማይጨው በስተሰሜን ያለው፣ እንደ ወጀራት ባሉ አካባቢዎች በሕወሃት ላይ ተቃውሞዎች ሲያሰማ የነበረው የእንደርታ አውራጃ ሕዝብ ተቃውሞ በማስነሳት መከላከያ ሳይመጣ ሕወሃትን ከመቀሌ ሊያባርር ይችላል የሚል አስተያየቶች እየተሰጡ ነው፡፡
