ከ 4 ሰአት በፊት

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ድባጤ ወረዳ ፣ያምፕ ቀበሌ የታጠቁ ኃይሎች በነዋሪው ላይ በከፈቱት ተኩስ አንድ ነዋሪ ሲገደሉ ሁለት የክልሉ የፖሊስ አባላት እንዲሁም የወረዳው አስተዳዳሪ መቁሰላቸውን የክልሉ ኮሙዩኒኬሸን ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

በታጣቂዎች ጥቃቱ የደረሰው ህዳር 4/2013 ዓ.ም መሆኑን የገለፁት ኃላፊው አካባቢው ከዚህ ቀደም የተረጋጋ እንደነበርም ይናገራሉ።

የክልሉ ፖሊስ እና የሚሊሻ አባላት ከመከላከያ ኃይል ጋር ተባብረው በአካባቢው የተፈጠረውን ለማረጋጋት በሚሞክሩበት ወቅት በተጨማሪም ታጣቂዎቹ በትናንትናው ዕለት ህዳር 5/ 2013 ዓ.ም ከወንበራ ተሳፋሪዎችን ጭኖ ቡለንና ደባጤን በማቋረጥ ወደ ቻግኒ የሚሄድ የህዝብ ማመላለሻ መኪና ላይ የነበሩ ተሳፋሪዎችን በማገትም መንገደኞችም ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ጨምረው ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በበኩሉ በክልሉ በደባጤ ወረዳ ከወንበራ ወደ ቻግኒ በመጓዝ ላይ በነበረ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ላይ ጥቃት መድረሱን በዛሬው ዕለት ህዳር 6/2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ውብጊሽ፣ ያምፕና ቂዶህ በተባሉ የክልሉ ወረዳዎች በተመሳሳይ ወቅት ጥቃት መሰንዘራቸውን ኢሰመኮ መረጃ እንደደረሰው ገልፆ ህይወታቸውን ለማዳን የሸሹ ሰዎች አሉም ብሏል።

በአሁኑ ወቅት የሚገመተው የተጎጂዎች ቁጥርም 34 እንደሆነና ከዚህም ሊጨምር እንደሚችልም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ኃላፊው በበኩላቸው የጉዳቱ መጠን በውል እንዳልታወቀ ጠቅሰው ታጣቂዎቹ ባገቱት ተሽከርካሪ ውስጥ የተሳፈሩ መንገደኞች ላይ የደረሰውን አጠቃላይ ጉዳት እንደተጣራ እንደሚያሳውቁም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ መለሰ አክለውም በአሁኑ ሰዓት የመከላከያ ሰራዊት እርምጃ እየወሰደ መሆኑንም ገልፀዋል።

“ይህ ጥቃት ሁላችንም በጋራ የተሸከምነውን የሰው ሕይወት ክፍያ ዛሬም በአሳዛኝ ሁኔታ የሚያሻቅብ ነው። የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በፍጥነት ጥቃቱ የበለጠ እንዳይባባስ እርምጃ መውሰዳቸው አበረታች ነው” ዋና ኮሚሽነሩ ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)ን ዋቢ በማድረግ የኢሰመኮ መግለጫ አስፍሯል።

በቤንሻንጉል ጉሙዝ እየተከሰቱ ያሉ ጥቃቶች ተደጋጋሚና አስከፊ እንደሆኑ አፅንኦት የሰጠው መግለጫው ፀጥታና ደህንነትን ለማጠናከር ፈጣንና የተቀናጀ እርምጃ አስፈላጊነትን አስምሯል።

“በቤንሻንጉል ጉሙዝ በሲቪል ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ፋታ የማይሰጥ ሆኖ በመቀጠሉ፤ በፌዴራልና በክልሉ መንግሥታት የፀጥታ ኃይሎች መካከል በፍጥነትና ንቁ ሆኖ መጠበቅ ላይ የተመሰረተ የተሻለ ቅንጅት የሚሻ ነው። የፌዴራልና የክልሉ የፀጥታና የፍትሕ አካላት ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመሆን እነዚህን ጥቃቶች ሊያስቆም የሚችል አዲስ ክልላዊ የፀጥታ ስትራቴጂ ሊነድፉ ይገባል።” ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ማለታቸውም ተገልጿል።