November 16, 2020 – Konjit Sitotaw
የስፔን መንግሥት በኤርትራ ላይ ህወሓት “ፈጽሞታል” የተባለውን የአየር ጥቃት አወገዘ። የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት እና ሕገ-መንግሥታዊ ተቋማት የሚያከብር መፍትሔ እንዲፈለግ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።
–
በኤርትራ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ እንደገለጸው በአስመራ ከፍተኛ ፍንዳታ የተሰማው ባለፈው ቅዳሜ ምሽት ሕዳር 5 ቀን 2013 ዓ.ም. ነበር። ሬውተርስ የዜና ወኪል ያነጋገራቸው ዲፕሎማቶች ህወሓት ከሚያስተዳድረው የትግራይ ክልል ሮኬቶች ወደ አስመራ መተኮሳቸውን ተናግረዋል።
–
የኢትዮጵያ መንግሥት እውቅና የነፈገው የትግራይ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በአስመራ ላይ ያነጣጠረው ጥቃት እንደተፈጸመ አረጋግጠዋል። ደብረጽዮን ” ወታደሮች እዚህ እስከተዋጉ ድረስ ማንኛውም ወታደራዊ ዒላማ ላይ እንተኩሳለን” ሲሉ ለአሶሼትድ ፕሬስ ተናግረዋል።
–
የትግራይ ክልላዊ መንግሥት በአስመራ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈጸሙ ውግዘት ገጥሞታል። በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ቢሮ ኃላፊ ቲቦር ናዥ ጥቃቱን ካወገዙ መካከል አንዱ ናቸው። ስፔን በዛሬው ዕለት ባወጣችው መግለጫ ውግዘቱን ከተቀላቀሉ አንዷ ሆናለች።
–
“የስፔን መንግሥት ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በኤርትራ ላይ ፈጽሞታል የተባለውን የሚሳኤል ጥቃት ያወግዛል” ያለው መግለጫ ቀውሱ ከመባባስ እንዲገታ ጠይቋል። የስፔን መንግሥት እንዳለው “የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት እና ሕገ-መንግሥታዊ ተቋማት የሚያከብር መፍትሔ ሊፈለግ ይገባል።” ስፔን በዚህ ረገድ የአፍሪካ ኅብረት እና የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) የሚወስዱትን እርምጃ እንደምትደግፍ አስታውቃለች።
DW