መነሻ ገጽ

18 November 2020

ሲሳይ ሳህሉ

ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የጉዳቱ ሰለባ ሲሆኑ ከ860 ሺሕ ሔክታር በላይ ሰብል ወድሟል 

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርናና አርብቶ አደር አካባቢ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝና የጎርፍ አደጋ ያደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ ለዘጠኝ ቀናት የተደረገው የዳሰሳ ጥናት ይፋ ተደረገ፡፡

በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በአፋርና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር 15 አባላትን የያዘ የጥናት ቡድኑን የላከው ምክር ቤቱ፣ የአንበጣ መንጋን ለመከላከልና በጎርፍ አደጋ የተጎዱ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎችን እንደቃኘ የዳሰሳ ጥናቱ አመልክቷል፡፡

ጥናቱ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎና ከተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የመጡ ከፍተኛ ኃላፊዎች በተገኙበት ሰኞ ኅዳር 7 ቀን 2013 ዓ.ም. የቀረበ ሲሆን፣ ወደፊት ሰፋ ያለ እንቅስቃሴና ጥናት በማድረግ ሪፖርት እንደሚያቀርብ ተገልጿል፡፡ ምልከታው በዋነኝነት በኦሮሚያ ክልል፣ ምዕራብና ምሥራቅ ሐረርጌ ዞኖች፣ በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ፣ በደቡብ ወሎ፣ በሰሜን ሸዋና በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞኖች፣ በአፋር ክልል በአሳይታ፣ በአሚባራና እዋ ወረዳ፣ እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር መደረጉ ተመላክቷል፡፡  

ጥናቱ በተለይም በአንበጣ ወረርሽኝ ላይ እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎችን የታዩ ክፍተቶች፣ በጎርፍ አደጋ የደረሱ ጉዳቶችንና የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመለየት፣ መልሶ ለማቋቋምና ወደፊት መደረግ ያለባቸውን ቅድመ ሁኔታዎችና የመፍትሔ ዕርምጃዎች ላይ መግባባት ላይ ለመድረስ እንደሚያግዝ ተነግሯል፡፡

የጥናት ቡድኑ በተሰማራባቸው አራቱም የአንበጣ መንጋ የተከሰተባቸው አካባቢዎች በሰብሎች፣ በግጦሽና በደኖች ላይ የተለያዩ ዓይነት አደጋዎች ማድረሱ ተጠቁሟል፡፡ በተጨማሪም ማሽላ፣ በቆሎ፣ በመስኖ የሚለሙ አትክልትና ፍራፍሬዎች በዋነኛነት ፓፓያ፣ ሽንኩርትና ለውዝ መጠቃታቸው በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በምዕራብና ምሥራቅ ሐርጌ ዞኖች በአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ የሰብል ምርት 283,172 ሔክታር፣ ጫት 11,079 ሔክታር፣ የግጦሽ መሬት 65,449 ሔክታርና የደን ሽፋን 108,309 ሔክታር የወደመ ሲሆን፣ ወደ 500,000 የሚጠጉ አርሶ አደሮች የችግሩ ሰለባ እንደሆኑ ጥናቱ አሳይቷል፡፡

በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ፣ በደቡብ ወሎና በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞኖች የአንበጣ መንጋው በ81,843 የሰብል ምርት ሔክታር፣ በ70,026 የግጦሽ መሬት በ166,874 ሔክታር ቁጥቋጦና በ53,689 ሔክታር የደን አካል ላይና ከ795,770 በላይ አርሶ አደሮች ለችግሩ ተጋላጭ መሆናቸው በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡

በድሬዳዋ አስተዳደር በ5,142 ሔክታር ላይ የበረሃ አንበጣው ጉዳት ያደረሰ መሆኑን ያመለከተው የዳሰሳ ጥናቱ፣ በተለይም ከፍተኛ ጉዳት በደረሰባቸው 27 ቀበሌዎች ሊያጋጥም በሚችለው የምርት መቀነስ ምክንያት 49,000 የሚጠጉ ቤተሰቦች የምግብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተገልጿል፡፡

የአንበጣን መንጋ ለመከላከል በተደረጉ ባህላዊና ዘመናዊ የዘመቻ ሥራዎች በኦሮሚያ ወደ 244,000 ሔክታር፣ በአማራ 315,298 ሔክታር በሰብል የተሸፈነ መሬት ማዳን መቻሉ ተመላክቷል፡፡

የሎጂስቲክስ አቅርቦት በወቅቱ አለመኖር፣ በአጎራባች ክልሎች መካከል ያለ የፀጥታ ችግርና አለመግባባት፣ የአውሮፕላን ርጭት ለማድረግ ለአውሮፕላኖች ኪራይ የሚከፈለው የገንዘብ እጥረት ከበርካታ ችግሮች ጋር ተዳምሮ የአንበጣ መንጋውን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር እንዳልተቻለ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን ለምክር ቤቱ አብራርተዋል፡፡

የበረሃ አንበጣውን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ተጨማሪ የአውሮፕላን ግዥዎች እየተፈጸመ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የተገኙትን 35,000 ታብሌቶች የአንበጣው ወረርሽኝ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የመረጃ ልውውጡን የተሻለ በማድረግ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡

በሁሉም አካባቢዎች በአንበጣ ወረርሽኝ ምክንያት በሰብል፣ በእንስሳት መኖና በደን ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን ለማወቅና በቀጣይ ሊከናወኑ የሚገባቸውን ሥራዎች ለማቀድ የቅድመ ምርት መረጃ ማሰባሰብ እንደሚገባ የዳሰሳ ጥናቱ አመላክቷል፡፡

በሌላ በኩል በጎርፍ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች የዳሰሳ ጥናቱን ይፋ ያደረገው የጥናት ቡድኑ፣ በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ከጎርፍና ከዝናብ ጋር ተያይዞ 38 ሰዎችና 1,420 እንስሳት መሞታቸውን ገልጿል፡፡

በዞኑ በአጠቃላይ በ28 ወረዳዎች ጉዳት ሲደርስ 513 ቤቶች ሙሉ በሙሉ የወደሙ፣ 1,362 በከፊል የወደሙና ከዚህም ጋር ተያይዞ 47 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሀብት ላይ ጉዳት ማድረሱን ጥናቱ አሳይቷል፡፡

የጎርፍ አደጋው በ124 የውኃ ፕሮጀክቶች፣ 98 ድልድዮች፣ በ102 ትምህርት ቤት የመማርያ ክፍሎች፣ በ13 ጤና ተቋማትና በ454 ኪሎ ሜትር መንገዶች ላይ ጉዳት ማድረሱ ተገልጿል፡፡

በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በ5,359 ሔክታር መሬት ላይ ጉዳት ያደረሰው የጎርፍ አደጋ 8.8 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ሀብትና በ36 ቀበሌዎች የሚኖሩ የ7,554 የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ጉዳት ደርሷል ተብሏል፡፡

በአማራ ክልል ባሉ የሰሜን ወሎ፣ የደቡብ ወሎና ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞኖች የሚገኙ 21 ወረዳዎች ላይ በሚገኙ 94,000 የሚጠጉ የኅብተሰብ ክፍሎች ላይ አደጋ ያደረሰው የጎርፍ አደጋ 5,593 መሬት ሔክታር በዝናብና የጎርፍ መጥለቅለቅ መጎዳቱ ተጠቁሟል፡፡

በአፋር ክልል በ17 ወረዳዎች የጎርፍ አደጋ እንደተከሰተ ያመላከተው የዳሰሳ ጥናቱ ችግሩ በዋነኝት በአዋሽ ወንዝ አስተዳደርና አያያዝ ዙሪያ ባሉ ችግሮች መሆኑ ተመላክቷል፡፡ በዚህም ከአሳይታ ወረዳ ወደ 8,000 የሚጠጉና ወደ 37,670 የሚጠጉ ሰዎች አሚባራ ወረዳ እንደተፈናቀሉ ተገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በአሳይታ 24 ትምህርት ቤቶች አምስት የጤና ተቋማትና በአሳይታ ወረዳ ሰባት ትምህርት ቤቶችና ዘጠኝ የጤና ተቋማት በውኃ መዋጣቸው ተጠቁሟል፡፡ አጠቃላይ በአፋር ክልል በአደጋው ምክንያት ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብትና ንብረት መውደሙ ተነግሯል፡፡