20 ህዳር 2020, 17:44 EAT

ዐቃቤ ሕግ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የብሔራዊ ምክር ቤት አባል በሆኑት ፖለቲካኛው አቶ ልደቱ አያሌው የክስ ማሻሻያ እንዲያቀርብ ታዘዘ።
አዳማ በሚገኘው በኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የምሥራቅ ሸዋ ችሎት አቶ ልደቱ መቅረባቸውን ለቢቢሲ የተናገሩት የኢዴፓ ሊቀ መንበር አቶ አዳነ ታደሰ ፍርድ ቤቱ የቀረበባቸው ክስ ተመልክቶ ተሻሽሎ እንዲቀርብ ማዘዙን ገልጸዋል።
አቶ አዳና እንዳሉት “ዐቃቤ ሕግ አቶ ልደቱን የከሰሰባቸው አንቀፅ 238 እና 256 እንዲሁም በክሱ ጭብጥነት የተመዘገቡት ሁኔታዎች የማይገናኙና ግልፅነት የሚጎድላቸው ስለሆነ፤ ለሚቀጥለው ቀጠሮ የክስ ማሻሻያ እንዲያቀርብ ተወስኗል” ሲሉ ተናግረዋል።
ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡት አቶ ልደቱ አያሌው ጥቅምት 20/2013 ዓ.ም በነበራቸው ቀጠሮ የቀረበባቸው ክስ ያስከስሳቸው እንደሆነ ለመወሰንና በዚህም ላይ የዋስትና ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት መሰየሙ ይታወሳል።
ነገር ግን በወቅቱ የዐቃቤ ሕግ ክስና ጠበቆች የሰጡት የመቃወሚያ መልስ በፅሑፍ አልተገለበጠም በሚል ነበር ለዛሬ [አርብ፤ ኅዳር 11/2013] ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶ የነበረው።
አቶ አዳነ አክለውም በዛሬው የችሎት ውሎ የአቶ ልደቱ “የዋስትናው ጉዳይ ከክስ ማሻሻያው ጋር የሚታይ ነው” በማለት ፍርድ ቤቱ ጥያቄያቸውን ውድቅ እንዳደረገ አመልክተዋል።
የክስ ማሳሻያውን ለመመልከትና ቀጣይ ውሳኔ ለማሳለፍ ችሎቱ ለኅዳር 24/2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ እንደሰጠ አቶ አዳነ አሳውቀዋል።
ሊቀ መንበሩ አክለውም ፍርድ ቤቱ የእለቱን ውሎውን ከማተናቀቁ በፊት አቶ ልደቱ “አስተያየት አለኝ” በሚል ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በተሰጣቸው ዕድልም “ከታሠርኩ አራት ወር ሆኖኛል። በእነዚህ አራት ወራት በፍርድ ሂደቱ ላይ እየታዘብኩት ያለው ነገር ዐቃቤ ሕግና መንግሥት እኔን በወንጀል ከሶ ማስቀጣት ሳይሆን አላማቸው የፍርድ ቤት ቀጠሮ በማራዘም፤ በሞራሌ፣ በሕሊናዬና በአካሌ ላይ አልፎም በሕይወቴ ላይ አደጋ እንዲደርስ የመፈለግ ሁኔታ ነው ያለው” ሲሉ ለፍርድ ቤቱ መናገራቸውን አቶ አዳና ገልፈዋል።
አቶ ልደቱ አክለውም “የተከበረው ችሎት ዐቃቤ ሕግና መንግሥት ለሚሠሩት ሥራ ተባባሪ ይሆናል ብዬ አላስብም” ሲሉ ድምፃቸውን እንዳሰሙ ሊቀ መንበሩ ይናገራሉ።
“ይህንን ሤራ ፍርድ ቤቱ በመገንዘብ የተፋጠነ ፍትህ እንዲሰጠኝ እፈልጋለሁ። ለተቀመጣችሁበት ወንበር፣ ለችሎቱና ለካባችሁ ስትሉ ፍትሃዊ ውሳኔ እንድትሰጡኝ እጠይቃለሁ” ሲሉ ችሎቱን መጠየቃቸውን አቶ አዳነ ተናግረዋል።
አቶ ልደቱ ጤንነታቸው ካለፈው ጊዜ አሁን የተሻለ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አቶ አዳነ አሳውቀዋል።
“የሆነ ሆነ ግን ሐኪሞቹ እየመከሩ ያሉት አቶ ልደቱ ውጭ ወጥተው መታከም እንዳለባቸው ነው። ሕክምናቸውን ተገቢ በሆነ ቦታ ማከናወን ካልቻሉ ለሕይወታቸው አደጋ መሆኑን ገልፀዋል። ይህንንም ጠበቆቻቸው ለፍርድ ቤቱ አሳውቀዋል።”
አቶ ልደቱ ከአዲስ አበባ ተይዘው ወደ ቢሾፍቱ ከተወሰዱ በኋላ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ክሶች ቀርበውባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል።
ከዚህ በፊት ፍርድ ቤት በዋስ እንዲለቀቁና ጉዳያቸውን ከውጪ ሆነው እንዲከታተሉ ቢወሰንም ተጨማሪ ክስ ቀርቦባቸው አሁንም በእስር ላይ ይገኛሉ።
አቶ ልደቱ ሐምሌ 24/2012 በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉት በቢሾፍቱ ከተማ ተከስቶ የነበረውን አለመረጋጋት በማስተባበርና በመደገፍ ተጠርጥረው ነበር።