ከመንግሥት በኩል ስለ ወቅታዊ ሁኔታ መረጃን የሚያወጣው የአስቸኳይ ጊዜ መረጃ ማጣሪያ ዛሬ ኅዳር 13/2013 ዓ.ም እንዳለው እዳጋ ሐሙስ ከአዲግራት ወደ መቀለ በሚወስደው መስመር ላይ የምትገኝ ከተማ ናት።
ቅዳሜ ዕለት በትግራይ ክልል ሁለተኛ ከተማ የሆነችው የአዲግራት ከተማ በኢትዮጵያ ሠራዊት ቁጥጥር ስር ሙሉ ለሙሉ መዋሏ ተገልጾ ነበር።
እዳጋ ሐሙስ ከክልሉ ዋና ከተማ መቀለ 116 ኪሎ ሜትሮች ያህል ርቃ ከምትገኘውና የምሥራቃዊ ትግራይ ዞን ማዕከል ከሆነቸው አዲግራት ከተማ ቀጥላ ትገኛለች።
አርብ ዕለት የኢትዮጵያ ሠራዊት ትግራይ ውስጥ ከሚገኙት ቁልፍ ከተሞች መካከል የሆኑትን የአክሱምና የአድዋ ከተሞችን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጠሮ የአዲግራት ዙሪያ መያዙን ገልጾ ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት በፌስቡክ ገጹ “በአዲግራት ከተማ ላይ የከባድ መሳሪያ ድብደባ መፈጸሙንና በዚህም ሠላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል” ያለ ሲሆን ከተማዋ በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ቁጥጥር ስር ስለመዋሏ ያለው ነገር የለም።
ይህንን ዜና በተመለከተ እስካሁን ከገለልተኛ ወገን የተገኘ ማረጋገጫ የለም።
አዲግራት፣ አክሱምና አድዋ በትግራይ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ትላልቅ ከተሞች መካከል የሚጠቀሱ ሲሆን በተለይ አክሱምና አድዋ በታሪካዊና በሐይማኖታዊ ቦታነት ቀዳሚ ናቸው።
በዚህም ምክንያት በከተሞቹ ያሉትን ታሪካዊና ሐይማኖታዊ ስፍራዎችን ለመጎብኘት በርካታ ቱሪስቶች ከውጪና ከአገር ውስጥ የሚጎበኟቸው ናቸው።
የአዲግራት ከተማ የምሥራቃዊ ዞን ማዕከል ከመሆኗ በተጨማሪ የመድኃኒት ፋብሪካን ጨምሮ የተለያዩ ፋብሪካዎች ያሉባት ከተማ ናት።
ሦስተኛ ሳምንቱን በያዘው በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊትና በትግራይ ክልል ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ባለው ወታደራዊ ግጭት ከቀናት በፊት በተለያዩ የትግራይ ክፍሎች የሚገኙትን ሽረ፣ ጨርጨርና አላማጣ የተባሉ ቦታዎችን መንግሥት መቆጣጠሩን ማሳወቁ ይታወሳል።
መንግሥት በመግለጫው ላይ በምዕራብ ግንባር የሚገኘው ሠራዊቱ ሰለህለሃ ላይ ከህወሓት ኃይል ከባድ መከላከል ገጥሞት እንደነበር ገልጾ ይህንን “መከላከል በመስበር አክሱምን መቆጣጠሩን” አመልክቷል።
ጨምሮም ሠራዊቱ ከአክሱም በኋላ ወደ አድዋ ባደረገው ዘመቻ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ መከላከል ቢገጥመውም አድዋን ለመቆጣጠር መቻሉን ገልጿል።
አርብ አመሻሽ ላይ በትግራይ ክልል እተካሄደ ያለውን ወታደራዊ ግጭት በተመለከተ መግለጫ የሰጡት ሁለት የህወሓት ከፍተኛ ባለስልጣናት ግን በቁጥጥር ስር ስለዋሉት ከተሞች ያሉት ነገር የለም።
አቶ ጌታቸው ረዳ በእንግሊዝኛ፣ አቶ ገብረ ረብረጻድቅ በአማርኛ በሰጡት መግለጫ ላይ በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ከባድ ውጊያ መካሄዱንና ጉዳት እንደደረሰ ገልጸዋል።
ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ በትግራይ ለሚገኙ የልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላት በሠላም እጃቸውን እንዲሰጡ የተቀመጠው ቀነ ገደብ ማብቃቱን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ባስተላለፉት መልዕክት ላይ “በቀጣይ ቀናት የመጨረሻው ሕግን የማስከበር ተግባር ይከናወናል” ብለው ነበር።
ትግራይ ውስጥ በሚገኘው የሠሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙ ከተገለጸ በኋላ የተቀሰቀሰው ወታደራዊ ግጭት ሦስተኛ ሳምንቱ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ ሠራዊቱ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ቦታዎችን በመቆጣጠር ወደ ክልሉ ዋና ከተማ መቀለ እያመራ መሆኑም ተገልጿል።
በፌደራል መንግሥቱና የትግራይን ክልል በሚያስተዳድረው ህወሓት መካከል ለወራት የቆየው አለመግባባት ተካሮ ወደ ግጭት ካመራ በኋላ በክልሉ ውስጥ ያሉ የግንኙነት መንገዶች በመቋረጣቸው ዝርዝር መረጃ በቀጥታ ከቦታው ለማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል።
ቢቢሲ