

23 November 2020
በትግራይ ክልል መንግሥት እየወሰደ ባለው ‹‹ሕግ የማስከበር ዕርምጃ›› በተለያዩ መንገዶች እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩ 167 ተጠርጣሪዎች ላይ በፌዴራል ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ መውጣቱን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስታወቀ፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዋና ዓቃቤ ሕግ ጌዴዎን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ቃል አቀባይ ሬድዋ ሁሴን (ዶ/ር) ጋር በጋራ በመሆን በወቅራዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳስታወቁት፣ በክልሉ የሚገኘውን የሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ በተሰነዘሩ የሮኬት ጥቃቶች ጨምሮ የተለያዩ ወንጀሎችን ፈጽመዋል በማለት ነው በእነዚህ ተጠርጣሪዎች ላይ የዕስር ማዘዣ የወጣባቸው፡፡
እንደ ጌዴዎን (ዶ/ር) ገለጻ፣ ተፈጸሙ የተባሉት ወንጀሎች የአገር ክህደት፣ የመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈጸም፣ በትጥቅ የሚፈጸም አመጽ፣ በአገሪቱ ፖለቲካዊ አንድነት ላይ የተፈጸመ ጥቃት፣ በሕገ መንግሥቱ ላይ ማመጽ፣ በጎንደርና ባሕር ዳር ሮኬት በመተኮስ የተፈጸሙ የአሸባሪነት ተግባሮች እዲሁም በወዳጅ አገር ላይ የተቃጣ ጥቃት የሚሉ ናቸው፡፡
ከተጠርጣሪዎቹ ውስጥ በርካቶች መያዛቸውን የተናገሩት ዋና ዓቃቤ ሕጉ፣ በብዛትም የመከላከያ ሠራዊት አባላት ናቸው ብለዋል፡፡ በተያያዘም 343 ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች እንደነበሩ በማስገንዘብም፣ ከእዚህ ውስጥ 116 ሰዎች በዋስትና ተለቅቀዋል ብለዋል፡፡