November 23, 2020

በሰሜን ዕዝ የሀገር መከላከያ ሰራዊታችን ላይ ሀገሩን በካደው የህወሃት ጁንታ ቡድን የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ መንግስት እየወሰደ ባለው ህግን የማስከበር እና የህልውና ዘመቻ በተለያዩ የሃገራችን አካባቢዎች የታሰቡ የጥፋ ሴራዎች በህብረተሰቡ እና በፀጥታ አካላት ትብብር መክነዋል፡፡

ቡድኑ ላለፉት 27 አመታት የዘረጋውን የግንኙነት መረብ ተጠቅሞ በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ሊፈፅም ያሰበው የሽብር ጥቃት እንዳይሳካ ከጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ/ም ጀምሮ በተደረገ ጠንካራ የክትትል እና የቁጥጥር ስራ ከከሃዲው የህወሃት ጁንታ ተልዕኮ ተቀብለው የተለያዩ ጥቃቶችን ለመፈፀም እና የፀጥታ መደፍረስ እንዲከሰት አቅደው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 796 ተጠርጣሪዎች ፣ በርካታ የጦር መሳሪዎች እና ሌሎች ቁሳቁሶች በፍርድ ቤት የመበርበሪያ እና የመያዣ ትዕዛዝ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የልዩ ልዩ ህገ- ወጥ ዝውውር ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክተር ኮማንደር ግርማ ተሰማ አስታውቀዋል፡፡

በተለያዩ የሃገራችን አካባቢዎች የሚፈፀሙ ጥቃቶች እና የሚከሰቱ ግጭቶች በህወሃት ፊትአውራሪነት እና ድጋፊ ሰጪነት የሚፈፀሙ ስለመሆናቸው የሚያረጋግጡ እና ሃይማኖትን ከሃይማኖት፣ ብሄርን ከብሄር ለማጋጨት የተዘጋጁ ሰነዶች በብርበራ ወቅት መገኘታቸውን ኮማንደር ግርማ አስረድተዋል፡፡

የፀጥታ አካላትን የደንብ ልብስ በመልበስ ጭምር የጁንታውን ቡድን ተልዕኮ በአዲስ አበባም ለማስፈፀም ሲንቀሳቀሱ እና ዝግጅት ሲያደርጉ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ያስታወሱት ኮማንደር ግርማ ተሰማ በተለያዩ ግለሰቦች መኖሪያ ቤት እና በልዩ ልዩ ተቋማት ውስጥ በተደረገ ፍተሻ 202 የተለያዩ የፀጥታ አካላት የደንብ አልባሳት ተይዘዋል ብለዋል፡፡ የደንብ አልባሳቶቹ በሃይማኖት አባቶች መኖሪያ ቤቶች ጭምር መገኘታቸውን የጠቀሱት ኮማንደር ግርማ ይህ ደግሞ ህገወጡ እና ከሃዲው የህወሃት ቡድን በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ሳይቀር ሰርጎ በመግባት ግጭት ለመቀስቀስ እየተንቀሳቀሰ አንደሚገኝ የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እስካሁን ለተገኘው ውጤት የህብረተሰቡ ተሳትፎ የጎላ ሚና እንደነበረው ያስታወሱት ኮማንደር ግርማ ተሰማ አዲስ አበባ ላይ ጀምረን አዲስ አበባ ላይ እንጨርሰዋለን በሚል ከንቱ ምኞት ላይ ታች ሲሉ ህልማቸው የመከነባቸው የጥፋት ቡድኖች ምንም አይነት ቀዳዳ እንዳይኖራቸው እና በተለያዩ ተቋማት እና አካባቢዎች ተሰግስገው የሚገኙ ሌሎች የጥፋት መልዕክተኞችን በቁጥጥር ስር ለማዋል በሚደረገው ጥረት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

Addis Ababa Police Commission