November 23, 2020

DW : ኢምንት ነበሩ።8። ተማሪዎች ነበሩም።በ196ዎቹ አጋማሽ  ለልማትና ዕድገት ያለመ ያሉትን ድብቅ ማሕበር አዲስ አበባ ላይ መሠረቱ።ማሕበር ገስግስቲ ብሔረ ትግራይ።ብዙ አልቆዩም።11 ሆኑ።የየራሳቸዉን የተፅዉኦ ስም፣ በጫካ ስም ለዉጠዉ፣ ድብቅ ማሕበራቸዉን  ይዘዉ ከአዲስ አበባ ደደቢት-ትግራይ በረሐ ወረዱ።ድብቅ ማሕበራቸዉንም ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ (ተሓህት) ወደሚባል ድብቅ ሸማቂ ተዋጊ ቡድን ቀየሩት።የካቲት 1967።

ኢምንት የነበሩት ባጭር ጊዜ አዕላፍ ሆኑ፣ ተማሪዎቹ  አክራሪ ብሔረተኛ፣ ደፋር ጦረኛ፣መሰሪ ፖለቲከኛ፣ጠንካራ አደራጅ፣ የወጣላቸዉ ማርክሲስት ሆኑም።ለጦርነት የመሠረቱት ቡድንም ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ተብሎ፣ በጦርነት አድጎ፣ በጦርነት ኖሮ፣ በጦርነት ለመላዉ ኢትዮጵያ ገዢነት በቃ።1983።ዛሬም በ27 የገዢነት ዘመኑ ካፈራቸዉ ጦረኞች ጋር እየተዋጋ ነዉ።የ46 ዘመኑ የጦርነት ጉዞዉ ፍፃሜ ይሆን ይሆን? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

Äthiopien | Premierminister | Abiy Ahmed Ali

ኢትዮጵያ ጦረኝነት-ከበሳል ፖለቲከኝነት፣ መገንጠልን-ከአንድነት፣ የትግራይ ብሔርተኝነትን-ከኢትዮጵያዊነት፣ ኮሚንስትነትን-ከካፒታሊስትነት፣ ብቸኛ ገዢነትን-ከመድብለ ፓርቲ ሥርዓት አቀንቃኝነት ጋር የቀየጠ ፓርቲ ከነበረና ካላት እሱ፣ ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ነዉ። ያ ጠንካራ የጦር ማሕበር ጫካ በነበረበት ዘመን እንደሱዉ ሁሉ ደርግ መራሹን የኢትዮጵያ መንግስትን ለመዉጋት ጫካ ከገቡት፣ ከግንባር ገድሊ ሓርነት ትግራይ (ግገሓት) እስከ ጀበሐ፣ ከኢዲዮ እስከ ኢሕአፓ ከነበሩ አማፂያን ጋር ተዋግቷል።በየዉጊያዉም፣ በሴራም፣በደባም እያለ ሁሉንም ተራ በተራ አሽነፏል።

የኢትዮጵያ ጦርን ድል አድርጎ ሥልጣን ከያዘ በኋላም የቀድሞዎቹ ተማሪዎች፣ የመሐለኞቹ ጦረኞች፣ የኋለኞቹ ሐገር መሪዎች  «ጦርነትን መዋጋት ብቻ ሳሆን ጦርነት መሥራት እንችላለን» እያሉ ከኦነግ፣ ከቀድሞ ጥብቅ ወዳጃቸዉ፣ ከረዳት አሰልጣኛቸዉ ከሻዕቢያ አሰልሰዉ ከሶማሊያ ገዢዎች ጋር ጦርነት ገጥመዋልም።

Äthiopien Tigray Debretsion Gebremichael

ከጦርነቶቹ ሁሉ፣ የቀድሞዉን የኢትዮጵያ ጦር ከናቅፋ ተራራ፣ እስከ ሽሬ እንደ ስላሴ ሸለቆ፣ ከመዘዞ ኮረብታ እስከ አዋሽ-አርባ ሜዳ በጋራ ወግተዉ፣ ኤርትራን የገነጠሉ፣የአስመራና የአዲስ አበባ አብያተ መንግሥታትን የተቆጣጠሩት የሕወሓትና የሻዕቢያ ገዢዎች በ1990 ጦርነት መግጠማቸዉ ለሩቁም፣ ለቅርቡም ታዛቢ ግራ አጋቢ፣አስደንጋጭ፣ ለማመን አስቸጋሪም ነበር።ግን ሆነ።

ሕወሓት ዛሬም ጦርነት ላይ ነዉ።ዉጊያዉ ራሱ ሕወሓት በኢትዮ-ኤርትራዉ ጦርነት ያፈራቸዉ የጦር አለቆች፣ በርዕዮተ ዓለሙ ያጠመቃቸዉ፣ ለመሪነት ያበቃቸዉ ፖለቲከኞች ከሚያዙት ጦር ጋር መሆኑ ነዉ የ1990ዉን ግራ አጋቢ ታሪክ የመደገሙ አብነት።ያስደንቅ፣ ያስደነግጥ፣ያሳስብ ይሆን? የቀድሞዉ ዲፕሎማት፣ ደራሲና የፖለቲካ ተንታኝ ዩሱፍ ያሲን «አይ አዎ» ነዉ መልሳቸዉ።

አቶ ያሬድ ጥበቡ የቀድሞ የኢሕአፓ አባል፣ የኢሕድን መሥራች፣ ኢሕድንን ከሕወሓት ጋር ያወዳጀዉ ቡድን አባልም ነበሩ።ከብዙ ዓመታት በፊት የጫካዉን ፖለቲካ ለቀዉ ፖለቲካን ይተነትናሉ።

እንደሰማነዉ የኢትዮጵያ መንግስት ጦር የትግራይ ርዕሠ ከተማ መቀሌን ለመያዝ በኪሎሜትሮች ርቀት ላይ ነዉ።ጦሩ መቀሌና አካባቢዉ የሚገኙ የሕወሓት የጦር ሰፈሮችንና ተያያዥ ኢላማዎችን በታንክ ጭምር እንደሚመታ አስጠንቅቋል።የኢትዮጵያ መንግስትም የሕወሓት መሪዎች በ72 ሰዓታት ዉስጥ እጃቸዉን እንዲሰጡ ትናንት ሰዓተ-ገደብ ሰጥቷል።

«በጎራዴ የኖረ በጎራዴ ይሞታል» እንዲሉ አዉሮጶች እኒያ ሲዋጉ-ሲያዋጉ ጎልምሰዉ፣ ሲገዙ፣ አዳዲስ ተዋጊ-ምትክ ገዢዎችን ሲያፈሩ ያረጁት ፖለቲከኞች፣ የዚያ ለጦርነት ተወልዶ በጦርነት የኖረዉ ድርጅታቸዉ ፍፃሜ ይሆን ይሆን? አቶ ያሬድ ጥበቡ።

አቶ ዩሱፍ ያሲን።የታሪክ አዋቂዎች «የኢትዮጵያ ታሪክ የጦርነት ታሪክ ነዉ» ይላሉ።በዘመናዊቱ ኢትዮጵያ ከተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ድርጅቶችም አብዛኞቹ አንድም የነፍጥ ዉጊያ፣ አመፅና አብዮትን፣ ሁለትም የብሔር ነፃነትና ሐገር የመሆን መብትን የሚያቀነቅኑ ናቸዉ።እንደ (ሕወሓት) ግን ለጦርነት ተወልዶ፣ በጦርነት አድጎ፣ በጦርነት ለስልጣን የበቃ፣ በጦርነት ገዝቶ፣ ጦረኞች ያፈራ ድርጅት ማግኘት ሲበዛ ከባድ ነዉ።

የዛሬ አስርና አምስት ዓመት ግድም ልማት እድገት ይሉ የነበሩት ሕወሓቶችም፣ የዛሬ ሁለት ሶስት ዓመት ተሐድሶ፣ ፍቅር፣ ይቅር ባይነትን ሲሰብኩ የነሩት ፖለቲከኞችም ዛሬ ኢትዮጵያዉያንን እደገና እያዋጉ ነዉ።

Äthiopien Tigray Konflikt Flüchtlinge

ኢትዮጵያዉያን የፖለቲካ ልሒቃን በጥቅሉ፣ ሕወሓቶች በተናጥል የፖለቲካ ልዩነታቸዉን ለመፍታት ጦርነትና ጦርነትን አልፋ ወ ኦሜጋ የማድረጋቸዉ ሚስጥር ለሩቆቹ ወይም ለዉጪዎቹ እንቆቅልሽ፣ ለቅርቦቹ የዴሞክራሲ እጦት፣ ለአንዳዶች ደግሞ ያስተሳሰብ «ድሕነት» ዉጤት ነዉ።ለዩሱፍ «ስልጣንን በጠመንጃ የመነጣጠቅ» ይትበኃል።ለአቶ ያሬድ ደግሞ «ከራስ ሐሳብ ሌላ የሌላዉን ያለመቀበል» አባዜ።ሁለተኛ ሳምንቱን በያዘዉ ዉጊያ የሞተ፣የቆሰለዉን ሰዉ ቁጥር፣ የጠፋዉን ሐብት ንብረት መጠን በግልፅ የተናገረ ወገን የለም።ልጅ-ዉላጁ፣ ዘመድ-ወዳጁ፣ ሐብት ጥሪቱ ከጦርነቱ የሚማገድበት ኢትዮያዊ የጥፋቱን መጠን ሊያዉቅ ይገባል።እስካሁን የሚታወቀዉ ግን ከ30 ሺሕ በላይ ስደተኛ ሱዳን መግባቱ ነዉ።

ጦርነቱ ካዳደረሰዉ የጥፋት መጠን እኩል የከእንግዲሕዋ ኢትዮጵያ በተለይ የትግራይ የወደፊት ፖለቲካዊ ሒደትና እንዴትነት እያነጋገረ ነዉ።አቶ ዩሱፍ ይመኛሉ፣ አቶ ያሬድ ይመክራሉ።

ጥቅሉን ቃለ መጠይቅ መስማት ለምትፈልጉ አምደ መረባችን ጎብኙ።ምኞቱ እንዲሰምር፣ ምክሩ ሰሚ እንዲያገኝ እንመኝ።Audio Player