- የትህነግ/ሕወሓት ጨፍጫፊ ቡድን በማይካድራ ንፁኃንን ገድሎ የቀበረበት ቦታዎች በመገኘት ላይ ናቸው፡፡
- የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው መረጃ ጨፍጫፊው ትህነግ በትንሹ 600 ሰዎች መግደሉን ይፋ አድርጓል፡፡
(አብመድ) በየቦታው የተገደሉ ሰዎች ስለሚገኙ ቁጥሩ ከዚህ ሊያሻቅብ እንደሚችልም አመላክቷል፡፡ በማይካድራ ከተማ አብነትና ሴንትራል መውጫ በተባሉ ገጠራማ ቦታዎች 74 ንጹሃን የተቀበሩበት ሥፍራ ተገኝቷል፡፡ 56 ዜጎች በአንድ ጉድጓድ ተቀብረው ነው የተገኙት፡፡ የውሃ ጉድጓድ ውስጥም የሰለባዎቹ አስክሬን መኖሩም ተረጋግጧል፡፡
–

በጨፍጫፊው ትህነግ ልዩ ኃይልና ሳምሪ በተባለው ገዳይ ቡድን በግፍ የተገደሉ ንጹኃን ከሰው እይታ ለማራቅ ነበር ይህንን ያደረጉት ይላሉ የአይን እማኞች ለአብመድ በሰጡት ምስክርነት፡፡
–
ጨፍጫፊው ትህነግ ከጅምላው ግድያ በኋላ የዘር ማጥፋቱን ወንጀል ከአለምዓቀፉ ማኅበረሰብ ለመደበቅ የግድያው ሰለባ ንፁሃንን አስክሬን ከከተማዋ አርቆ መደበቁን ከጥቃቱ የተረፉ የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
–
ትህነግ ከጭፍጨፋው በተጨማሪም በከተማዋ የሚኖሩ አማራዎች በስጋት እንዲሸሹ የማድረግ ትልም እንደነበረውም ተገልጿል፡፡ በገዳይ ቡድኑ ህይወታቸው ያለፉ የንፁሃን ዜጎች አስክሬን በክብር እንዲያርፍ ተደርጓል፡፡
–
ጥቅምት 30/2013 ዓ.ም በህወሃት የጽጥታ መዋቅር እና ሳምሪ በተባለ ኢ-መደበኛ ገዳይ ቡድን ጭካኔ በተሞላበት መንገድ የአማራ ብሄር ተወላጆች በግፍ መገደላቸውን አብመድ ከቦታው ተገኝቶ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
–
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባወጣው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርትም በትንሹ 600 ሰዎች መገደላቸውን የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ ገልጸዋል፡፡ ሳምሪ የተባለው የትግራይ ወጣቶች መደበኛ ያልሆነ ቡድን ጭፍጨፋውን መፈጸሙን ነው ኮሚሽኑ ይፋ ያደረገው፡፡ በድርግቱ የአካባቢው የፖሊስ እና የሚሊሻ አባላት መሳተፋቸውንም ኮሚሽኑ ይፋ አድርጓል፡፡
–
ጭፍጨፋው በግልጽ ብሄርን መሰረት ያደረገ መሆኑን የገለጸው ኮሚሽኑ የጉዳቱ ሰለባዎችም ጭካኔ በተሞላበት በዱላ በመደብደብ፣ በጩቤ በመውጋት፣ በገጀራ፣ በመጥረቢያ በመመታት እንዲሁም በማነቅ ሕይወታቸው እንዲያልፍ መደረጉን ይፋ አድርጓል፡፡ ግድያው በጥንቃቄ ተቀነባብሮ የተፈጸመ እንደሆነም ገልጿል፡፡
–
ጭፍጨፋው በጭካኔ የተፈጸመ እና የጦር ወንጀለኝነት እንደሆነም ኮሚሽኑ አመላክቷል፡፡ ጭፍጨፋው በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ የስነ ልቦና ጫና መፍጠሩንም ገልጸዋል፡፡ በአካባቢው ከተፈጸመው ጭፋጨፋ በተጨማሪም ከፍተኛ የአካል ጉዳት መድረሱን ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል፡፡ የብዙ ቤተሰብ አስተዳዳሪዎች በመገደላቸው ቤተሰቦቻቸው ለችግር መጋለጣቸውንም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡
–
ጨፍጫፊ ቡድኑ ያሳደዳቸውን ዜጎች ሌሎች የትግራይ ተወላጆች ለማዳን ጥረት ማድረጋቸውንም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡ በቀጣይም አጥፊዎችን ለህግ ለማቅረብ ሪፖርቱን በማጠናከር ለሚመለከተው አካል ኮሚሽኑ እንደሚያቀርብ ገልጸዋል፡፡