25 ህዳር 2020, 14:00 EAT

ለቢቢሲ ቃላቸውን የሰጡ አንዳንድ የትግራይ ተወላጆች በማንነታቸው እንግልት፣ መገለልና እስር እየደረሰባቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ማንነታቸውን መሠረት ባደረገ ሁኔታ መልከ ብዙ እንግልቶችን እያስተናገዱ እንደሆነም ያብራራሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በትግራይ ክልል የሚደረገው ጦርነት ሕግን የማስከበር ተልእኮ ያለው ነው ይላሉ። ዓለማውም ንጹሐን ላይ ጉዳት ሳይደርስ በወንጀል የሚፈለጉ የህወሓት አመራሮችን በቁጥጥር ሥር ማዋል እና ለሕግ ማቅረብ እንደሆነ ገልጸዋል።
ይህን በእንዲህ እንዳለ እየወጡ ያሉ የተለያዩ ሪፖርቶች ግጭቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ በተለያዩ ስፍራዎች ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች እና ፍጥጫዎች መበራከታቸውን ይጠቁማሉ።
በተመሳሳይ የትግራይ ተወላጆችም ማንነትን መሠረት ያደረጉ እንግልቶች እያደረሱብን ነው ይላሉ።
110 ሚሊዮን የሚገመት የሕዝብ ብዛት ባላት ኢትዮጵያ፤ የትግራይ ተወላጆች ከጠቅላላ ሕዝብ 6 በመቶ ይሸፍናሉ።
ከክልላቸው ውጭ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሚኖሩባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ከማንነት ጋር በተያያዘ ለእስር እያተዳረግን ነው፤ ከሰር መገለል እየገጠሙን ነው ይላሉ።
መንግሥት በበኩሉ እንዲህ ዓይነት ዘርን ያማከለ ተግባር አይፈጸምም ሲል ያስተባብላል። ሰዎች በማንነታቸው ሳይሆን ከደኅንነት ጋር በተያያዘ በግለሰብ ደረጃ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ ሲል ይናገራል።
በደኅንነትና ፀጥታ መሥሪያ ቤት ውስጥ ይሰሩ የነበሩ የትግራይ ተወላጆች ግን ለቢቢሲ እንደተናገሩት ግጭቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ ከሥራ ታግደናል፣ ቤት እንድንውልም ተደርገናል ይላሉ፡፡
መሣሪያችሁን አስረክቡ
‘መሣሪያ መልሺ’ ከተባሉ የትግራይ ተወላጆች አንዷ በፖሊስ ሰራዊት ውስጥ አባል ናት። ላለፉት 20 ዓመታት አገልግላለች። ከዚያ ቀደም ብሎ ግን የህወሓት አባል ነበረች።
እሷ እንደምትለው ግጭቱ በተጀመረ በሁለተኛው ቀን ከአለቃዋ የስልክ ጥሪ ደርሷታል። በነገታው በአስቸኳይ ቢሮ ሪፖርት እንድታደርግ አለቃዋ አሳሰባት።
በተባለችው ቀን ቢሮ ስትደርስ ወዲያውኑ ትጥቅ እንድትፈታ እንደተደረገች ትናገራለች። ‹‹ማንኛውንም እጄ ላይ የሚገኝ ንብረት እንዳስረክብ፣ የጦር መሣሪያም እንዳስረክብ ተደረኩ›› ትላለች።
እሷ ብቻ ሳትሆን ሌሎች በፖሊስ ሠራዊቱ ውስጥ የነበሩ ከፍተኛ ኃላፊዎችም ጭምር የትግራይ ተወላጅ ስለሆኑ ብቻ በእጃቸው ያለውን ሁሉ አስረክበው ቤት እንዲያርፉ ተደርጓል ብላለች ለቢቢሲ።
መንግሥት በሠራዊቱ ውስጥ ትግራዊያን በመሆናቸው ብቻ ትጥቅ እንዲፈቱ ስለተደረጉ ዜጎች ያለው ነገር የለም።
ሆኖም ዘርን ባማከሉ ጠቅላላ ጉዳዮች ዙርያ በቅርቡ አስተያየት የሰጡት የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ማሞ ምሕረቱ ለቢቢሲ እንደተናገሩት “መንግሥታቸው በማንነት ላይ የተመሰረቱ ጥቃቶችንም ሆነ መገለሎች ካሉ በዋዛ እንደማያልፋቸውና አጥብቆ እንደሚያግዛቸው” ጠቅሰው “ይህ በፍጹም ተቀባይት የሌለው ነገር ነው” ብለዋል።
“ሆኖም…” ይላሉ ከፍተኛ አማካሪው፤ ለጸጥታና ደህንነት ተቋማት ግልጽ መመርያ ተላልፎላቸዋል። ማንኛውም የሚወስዱት እርምጃ የደኅንነት ስጋትና መረጃን መሠረት ያደረገ እንዲሆን፤ እርምጃዎች ትኩረት ያደረጉትም የደህንነት ስጋት የደቀኑ አክራሪና ያኮረፉ የህወሓት ርዝራዦች ላይ ብቻ ነው ይላሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ሲመጡ የሕዝቦችን እኩልነት እንደሚያስጠብቁ፣ ብሔራዊ አንድነትን ለመፍጠር እንደሚሰሩ ቃል ገብተው ነበር። ለዚህም ተግባራዊነት ባለፉት ዓመታት ጥረት ሲያደርጉ እንደቆዩ እሙን ነው።
ሆኖም በአገሪቱ እዛም እዚህም የግጭቶች መፈጠር ይህ ህልማቸው ብዙም እንዳልተሳካላቸው የሚያሳይ ሆኗል።
ቢቢሲ 14 ዓመት በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ አገልግሎት ከሰጠና ስሙ እንዲጠቀስ ከማይሻ አንድ ግለሰብ እንደሰማው የግጭቱን መቀስቀስ ተከትሎ እሱና ሌሎች ተጋሩ የሆኑ የሥራ ባልደረቦቹ መገለልና አስደንጋጭ የሆነ ያልተጠበቀ እንግልት ደርሶብናል ይላል።
እሱ እንደሚለው በሰሜን ኢትዮጵያ ችግር መፈጠሩን ተከትሎ በገዛ ባልደረባው መጋዘን ውስጥ እንዲታሰር መደረጉን ይናገራል።
90 የሚሆኑ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የሠራዊቱ አባላት ከሱ ጋር በእስር ላይ እንደነበሩ ይናገራል። በቅድሚያ የእጅ ስልካቸው መቀማቱንና በእስር ላይ ሳሉም ልክ እንደ ምርኮኛ ይታዩ እንደነበር ያስረዳል።
“መሣሪያ እንድንመልስ ተደርገን የታሰርነው ሁላችንም ተጋሩዎች ነበርን። አንድም የሌላ ብሔረሰብ አባል መሀላችን አልነበረም። እስሩ በማንነታችን ምክንያት እንደሆነ ከዚህ በላይ ማስረጃ ሊኖር አይችልም” ይላል።
አሳሪዎቻችንን ለምን እንዲህ ታደርጉናላችሁ ብለው በሚጠይቁበት ጊዜ ‘ህወሓት የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት አድርሶብናል። እናንተን እንድናስር ትእዛዝ የመጣው ከበላይ ነው’ የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው ይናገራል።
ማንነትን ሸሽጎ ስደት
በዚህ ሁኔታ ከግለሰቡ ጋር ለእስር ተዳርገው ከነበሩት መካከል የህወሓት ቀደምት አባላት ይገኙበታል።
ህወሓት የተራዘመ የትጥቅ ትግል አድርጎ የአምባገነኑን የመንግሥቱ ኃይለማርያምን ማርክሲስት ቡድን በ1983 ዓ.ም በኃይል አሸንፎ ስልጣን ከያዘ ወዲህ በአገሪቱ የፖለቲካ ኩነቶች አድራጊ ፈጣሪ ሆኖ መቆየቱ ይታወሳል።
እነዚህ እስርና መገለል ገጥሞናል ብለው ለቢቢሲ የተናገሩት የትግራይ ተወላጆች የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አስተዳደር መምጣቱን ተከትሎ ግን ከፖለቲካ መድረኩ እየተገለሉ መምጣታቸውን ያወሳሉ።
ሌሎች ተመሳሳይ ቅሬታ ለቢቢሲ ያቀረቡት በመከላከያ ሰራዊቱ ባልደረባ የነበሩ ናቸው።
ከእነዚህ መካከል ከፍተኛ መኮንኖች ይገኙበታል። አንዳንዶቹም በአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል ተካተው ሶማሊያ የዘመቱ ናቸው።
“አገራቸውን ለነዚህ ሁሉ ዓመታት ደከመን ሰለችን ሳይሉ ያገለገሉ የሠራዊቱ አባላት በዚህ መልኩ በገዛ አገራቸው ይጉላሉ ብዬ በፍጹም አስቤ አላውቅም” ይላል ለቢቢሲ ቃሉን የሰጠው ይህ የትግራይ ተወላጅ።
ይህ የሠራዊት አባል በመጨረሻ ታስሮ ከነበረበት መጋዘን አምልጦ ተራ ግለሰብ በመምሰል ወደ ጎረቤት አገር ሸሽቷል። ይህንን መረጃ የሰጠውም በስደት ከሚገኝበት አገር ሆኖ ነው።
- በማይካድራ ከ600 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ኢሰመኮ ገለጸ
- የተባበሩት መንግሥታት በትግራይ “የጦር ወንጀል” እንዳይፈጸም ስጋት ገብቶኛል አለ
- ግጭቱን ሸሽተው ወደ ሱዳን የገቡ ተፈናቃዮች ከ40 ሺህ ማለፉ ተነገረ
ድንበር በሚያቋርጥበት ጊዜ ትግራዋይ መሆኑ እንዳይታወቅበት የቋንቋ ዘዬውን ጭምር ለመለወጥ እንደተገደደ ያስረዳል። ይህን ያደረኩት በኔ ላይ ጥርጣሬ እንዳይፈጠር ሰግቼ ነው ይላል።
ይህ ስደተኛ አገር ውስጥ ሳለ ጥሏቸው ለመጣውና መጋዘን ውስጥ ታስረው ለሚገኙትና የአገሩ ልጆች ይጨነቃል።
ሌሎች ለቢቢሲ የደረሱ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ የመከላከያ ሰራዊቱ (የቀድሞም ሆነ የአሁን) አንዳንድ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ አባላት ላይ መገለል ደርሶባቸዋል።
የተወሰኑት ታስረዋል፣ በተወሰኑ ላይ ደግሞ ብርበራ ተፈጽሟል። አንዳንዶቹም በቁም እስር ላይ እንደሚገኙ ተረድተናል።
በዚህ ሁኔታ ላይ አስተያየታቸውን ከቢቢሲ የተጠየቁት ኢታማዡር ሹሙ ብርሃኑ ጁላ ‹‹ይህ የፖለቲካ ጉዳይ ነው›› በማለት ምላሽ ለመስጠት ጉዳዩ እሳቸውን እንደማይመለከት ተናግረዋል፡፡
ዘርን ያማከለው መገለልና እስር በፖሊስና በመከላከያ ሰራዊት ብቻ ላይ ያጋጠመ ጉዳይ እንዳልሆነ ለቢቢሲ ቃላቸውን የሰጡት ያስረዳሉ።
ሾፌሩ አባቴን ከሰሱት
ማንነቷን ለመግለጽ ደኅንነት እንደማይሰማት ለቢቢሲ የተናገረች አንዲት ሴት ባለፈው ሳምንት ያጋጠማትን ስትናገር ቤታቸው በድንገት በታጠቁ ሰዎች እንደተወረረና ብርበራ እንዳደረጉ ከዚያም ቤት ውስጥ የሚገኙ የባንክ ደብተሮችን እንደወሰዱ ተናግራለች፡።
በመጨረሻም በሾፌርነት የሚተዳደሩት አባቷንም ፖሊሶች ይዘዋቸው እንደሄዱ ለቢቢሲ አስረድታለች።
አባቷ ከተወሰዱ በኋላ ለ2 ቀናት መታሰራቸውን ተናግራለች። የደኅንነት ሰዎች አባቷ 6 ሚሊዮን ብር ይዘው ወደ ትግራይ በቅርቡ መሄዳቸውንና የጦር መሣሪያ ይዘው ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውን በመጥቀስ እንደከሰሷቸው አስረድታለች።
ይህ የፈጠራ ክስ ነው የምትለው ይህች ሴት፤ አባቷ ቱሪስቶችን ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የሚያመላልሱ ሾፌር እንደሆኑ ተናግራ በአሁኑ ወቅት አባቷ የተመሰረተባቸው ክስ ተነስቶላቸዋል ትላለች።
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ፤ ህወሓት በአዲስ አበባ እና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የሽብር ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል ጥቆማ ለመንግሥት መድረሱን ተከትሎ የተለያዩ ምርመራዎች መደረጋቸውን ተናግረዋል። በዚህም 343 ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን እና ከእነዚህም መካከል 160 የሚሆኑት በዋስ መለቀቃቸውን ተናግረዋል።
እንዲህ ዓይነቱ ዘርን ያማከለ ፍተሻና ብርበራ በመንግሥት መዋቅር ሥር ባሉ አንዳንድ አገልግሎት ሰጪ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ መስተዋሉን ቢቢሲ ተረድቷል። የኢትዮጵያ አየር መንገድም አንዱ ነው።
የጦርነቱን መከሰት ተከትሎ በርካታ ትግራዋይ የአየር መንገዱ ሰራተኞች ተጨማሪ ጥሪ እስኪደርሳቸው ድረስ የግዴታ እረፍት እንዲወስዱ ተደርገዋል፡፡
አልያም ደግሞ ከቤት ሆነው እንዲሰሩ ሆነዋል። ቢቢሲ ይህን መረጃ ያገኘው እዚያው ከሚሰሩ ሰራተኞች ነው።
ይህ ቅሬታ ምን ያህል እውነት ነው በሚል ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ቢቢሲ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ ማግኘት አልቻለም።
ከመንግሥታዊ መዋቅር ውጭ ባሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም ቢሆን ይህ ዘርን መሠረት ያደረገ ልዩነት ተስተውሏል።
የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) በቅርቡ እንዳለው አማራ ክልል በሚገኘው ቢሮው የፖሊስ መኮንን ሰራተኞቹን ስለማንነታቸው ጥያቄ አቅርቦላቸዋል፡፡ የትውልድ ስፍራቸውንም ጠይቋል፡፡
የዐለም ምግብ ድርጅት እንዲህ ዓይነቱ መረጃ በእጁ እንደማይገኝ የመለሰ ሲሆን፣ የተጠየቀው መረጃም የመንግሥት ፖሊሲ እንዳልሆነ ከክልሉ ጸጥታ ቢሮ አረጋግጧል
የፌዴራል መንግሥት በበኩሉ ይህንን በአማራ ክልል የዓለም የምግብ ፕሮግራም ቅርንጫፍ ቢሮ የተፈጸመውን ሁኔታ ‹‹የክስተቱን ሌላ መልክ መስጠት ነው›› በሚል አስተባብሏል፡፡
የፌዴራል መንግሥት እንደሚለው የፖሊስ መኮንኑ ቅርንጫፍ ቢሮ የሄደው የደህንነት መረጃን መሰረት አድርጎ ነው፡፡ የህወሓት ሰዎች በአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ ተሰግስገው እንዳሉ ለማጣራት የደኅንነት መረጃ በመያዝ የተደረገ መጠይቅ ነው ብሏል፡፡
ጨምሮም የፖሊስ መኮንኑ በቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቱ ሲገኝ ስም ዝርዝሮችን ይዞ ነው፡፡ ከያዛቸው ስም ዝርዝሮች ውስጥ በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ የሚሰሩ ካሉ ለማጣራት ነው የሄደው ብሏል መንግሥት፡፡
የደኅንነት ሰዎች በትግራይ እየሆነ ባለው ሁኔታ በተቀረው የአገሪቱ ክፍል ከህወሓት ደጋፊዎች ሊፈጸም የሚችለው የደህንነት አደጋ ስጋት እንደሚያሳስባቸው እሙን ነው፡፡
ነገር ግን ለቢቢሲ ቃላቸውን የሰጡ የትግራይ ተወላጀጆች እየደረሰባቸው ያለው እንግልት የሚመነጨው የህወሓት ደጋፊ ከመሆን አለመሆን ሳይሆን ከብሔር ማንነታቸው ነው፡፡.
አገራዊ ስሜቱ ይመለስ ይሆን?
ይህ የሰሜኑ ጦርነት በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ ከሆነ በብሔሮች መካከል ያለው ውጥረት ሊረግብ ይችል ይሆናል፡፡
ነገር ግን ጦርነቱ እየተራዘመ ከመጣ ከክልሉ ውጭ ለሚኖሩ ተጋሩዎች ሕይወት ፈታኝ ሊሆንባቸው ይችላል የሚል ስጋት አለ፡፡
ምንም እንኳ ህወሃት ሀገራዊ አንድነትን ለማምጣት ለተያዘው ዕቅድ መሰናክል ተደርጎ ቢታይም፣ ጠቅላይ ሚንስትሩ ሀገሪቱን አንድ ለማድረግ ላላቸው ራዕይ እንዲህ ያሉ ግጭቶች ትልቅ ፈተና ሊደቅኑ ይችላሉ።
‹‹መንግሥት እያደረገ ያለው አንድ አንኳር ተግባር ቢኖር ሁሉንም ዜጋ የሚያስተሳስር አንድ ማኅበረሰብን መፍጠር ነው›› ብለዋል የጠቀልይ ሚኒስትሩ አማካሪ ለቢቢሲ፡፡
ነገር ግን በትግራይ ያለው ጦርነት ይህን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ግብ የሚያወሳስብ እንዳይሆን ያሰጋል፡፡