
(አብመድ) የቀድሞው የሰሜን ዕዝ ምክትል አዛዥ የነበሩት ብርጋዴር ጀኔራል ተፈራ ማሞ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ከአብመድ ጋር ባደረጉት ቆይታ ሕወሓት ሀገርን የማፍረስ ዓላማ ይዞ የተመሠረተ ድርጅት እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ደርግን ከስልጣን ለማስለቀቅ የዓላማ ልዩነት የነበራቸው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢህዴን) እና ሕዝበ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) የፈጠሩት ጥምረት ያለ አቻ ጋብቻ ነበር ይላሉ ብርጋዴር ጀኔራል ተፈራ፡፡–የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢህዴን) የደርግ ወታደራዊ መንግሥትን ጭቆና ለመታገል የተናጠል ትግል ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በተናጠል እንቅስቃሴው ተፈላጊውን ውጤት ማግኘት ስላልተቻለ በ1980 ዓ.ም ከሕወሓት ጋር ጥምረት ለመፍጠር እንቅስቃሴ አድርጓል፡፡ብርጋዴር ጀኔራል ተፈራ ማሞ እንዳሉት ኢህዴን ሀገርን ከደርግ ጭቆና ለመታደግ የተመሠረተ ድርጅት ነው፤ ሕወሓት ግን ትግራይን ነጻ በማውጣት ሀገር የመመሥረት ዓላማ ነበረው፡፡–በ1981 ዓ.ም የሁለቱ ድርጅቶች ሠራዊት ተሰባስበው ቀጣይ ለሚኖረው የጋራ ሀገራዊ ዘመቻ ውይይትና ስልጠና ወስደዋል፡፡ በዚሁ ዓመት ክረምት ላይም ጥምረታቸውን ይፋ አድርገው በተለያዩ አውደ ውጊያዎች የጋራ ትግል አድርገዋል፤ የደርግ መንግሥትንም ድል አድርገዋል፡፡የኢህዴንና የሕወሓት ሠራዊት የዓላማ አንድነትና መግባባት ቢኖራቸውም መሪዎች ግን ልዩነት እንደነበራቸው አመላክተዋል፡፡ የኢህዴንና የሕወሓት ጥምር ኃይል የትግራይን አካባቢዎች ነጻ አውጥቶ ወደ አማራ ክልል ሲገባ የሕወሓት ሰዎች ቀዳሚ ተግባር የነበረው በአማራ ክልል በሚገኙ ተቋማት ውስጥ የነበሩ ንብረቶችን መዝረፍና እየጫኑ መውሰድ ነበር፤ በዚህ የተነሳ የኢህዴን ታጋዮች ከፍተኛ የሕዝብ ተቃውሞ ገጥሟቸው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ሠራዊቱ ሕዝባዊ ወገንተኝነት አሳይቶ ስለነበርም ለሕወሓት ተላላኪ ከነበሩ የኢህዴን መሪዎች ጋር አለመግባባት መፈጠር ጀመረ፡፡–የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ሲመሠረት ሕወሓቶች ኢህዴንን በመከፋፈል የበላይነትን የማስጠበቅ እቅድ ነድፈው ተግባራዊ አድርገዋል፡፡ ግንባሩ ከተፈጠረ በኋላም የብሔር ድርጅቶች (ብአዴን፣ ሕወሓት፣ ኦህዴድ እና ደኢህዴን) እንዲመሠረቱ አድርጎ ነበር፡፡ሕወሓት ሀገርን የመዝረፍ፣ ሕዝብን የመከፋፈልና ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት መፈጸም የጀመረችው ገና በጠዋቱ ነው፡፡ ከመከላከያ ሠራዊቱ ጀምሮ ሀገራዊ ስሜት ይንጸባረቅባቸው የነበሩ ተቋማትን የማፈራረስና የማዳከም እንቅስቃሴው ሥር መስደድ የጀመረው ግንባሩ በተፈጠረ ማግስት ነው፡፡–የኢህአዴግ ግንባሮችን በፈለገው አቅጣጫ መዘወር ከጀመረ በኋላም ሠራዊቱንና የደኅንነት ተቋሙን በሕወሓት ቅርጽና ቁመና ልክ አደራጅቷል፡፡ በተለይ የደኅንነት ተቋሙ ከጫካ በወጡ ሰዎች ከተደራጀ (በተለይ ከ1983 ዓ.ም) በኋላ አማራና ኦሮሞን መሠለል ዋና ተግባሩ አድርጎ ነበር፡፡ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረ በኋላም ተግባሩን በተደራጀ መልኩ ሲያስቀጥል ቆይቷል፡፡ ሕወሓት ቁልፍ የስልጣን ቦታዎችን በራሱ ሰዎች መቆጣጠሩ፣ ንብረት ዘረፋውንና ኢ-ፍትሐዊነት የጎደለውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እና ሌሎችንም ህገወጥ ተግባራት ፈጽሟል፡፡ህወሃት ከ1997 ዓ.ም ምርጫ በኋላ ሀገራዊ ስሜት ያላቸውንና አማራውን የማጥፋት ዘመቻ አድርጓል፤ የሚቃወማቸውን ኃይል በማስወገድም የራሳቸውን ሰዎች ሾመዋል፡፡–በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው ጥቃትም ከዚሁ እኩይ ባህሪው የመነጨ ነው ብለዋል፡፡የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ እና የመከላከያ ሠራዊት በጋራ ክንድ ባልጠበቀው ሁኔታ ድባቅ ሲመቱት ይመካበት የነበረው ኃይል ሊያድነው እንዳልቻለ ግልጽ ሆኖ ታይቷል ነው ያሉት፡፡ሕወሓት በአማራ ሕዝብ ላይ በተለዬ መልኩ በደል አድርሷል፤ በተለይ የማንነትና የወሰን ይገባኛል ጥያቄ ባለባቸው አካባቢዎች ግድያና ስቃይ ሲያደርስ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡እንደ ብርጋዴር ጀኔራል ተፈራ ማብራሪያ መንግሥት በትግራይ ክልል እያካሄደ ያለው ሕግ የማስከበር ተግባር የሚደነቅ ነው፡፡ የሀገሪቱ ሰላም እንዲረጋገጥ ቡድኑን ማስወገድ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡ የአማራ ክልል ሕዝብና መንግሥትም ሁኔታዎችን በንቃት መከታተል እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡