ገና ከጥንስሱ ሲነሳ የአማራን ህዝብ በጠላት ፈርጆ የተነሳው ትህነግ በወልቃይት ጠገዴ ፣ ራያና ሰቲት ሁመራ አካባቢዎች ከግማሽ ሚሊዮን በላይ አማራዎችን አፈናቅሏል። ከ10 ሺህ በላይ የሚሆኑ አማራዎች ደግሞ በማንነታቸው ምክንያት ረሽኗል።

በወልቃይ ጠገዴና ሰቲት ሁመራ አካባቢ በኢንቨስትመንት ተሰማርተው ኢንቨስት ሲያደርጉ የነበሩ ስምንት ባለኃብቶችን አማራ በመሆናቸው ብቻ አፍኖ በመውሰድ ገሏል። በተለያዩ ምክንያት አስሯቸዉ የነበሩ 15 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች በትህነግ ታፍነው የት እንደገቡ አይታወቅም። ይህ ታሪክ የማይረሳው በአማራ ህዝብ ላይ የተፈጸመ የግፍ ግፍ ነው።
ጁንታው ትህነግ በወልቃይት ጠገዴ ፣ በሰቲት ሁመራ ፣ በራያና በአላማጣ የአማራ ህዝብ ላይ የፈጸመው ግፍና በደል ተነግሮና ተዘክሮ አያልቅም። በእነኝህ አካባቢዎች የሚኖሩ አማራዎች በቋንቋቸው እንዳይማሩ ፣ የተማሩት በሙያቸው በመንግሥት መስሪያ ቤቶች እንዳይቀጠሩና በትህነግ አምሳል ከተቀረጸው ከትግራይ ቴሌቪዥን ውጭ ሌላ የሚዲያ አማራጮችን እንዳይከታተሉ በማድረግ ከፍተኛ አፈናና በደል ሲፈጽም የኖረ ግፈኛ ቡድን ነው።
ትህነግ ለዘመናት ከፈጸማቸው የጭካኔ ግፎች በላይ በቅርቡ በማይካድራ ከ 700 በላይ ንጹሃን ዜጎች ላይ የፈጸመው ግፍ እስካሁን በዓለም ላይ ያልተፈጸመ አረመኔያዊ ድርጊት ነው። በአረመኔው ትህነግ በጅምላ የተረሸኑ ንጹሐን ዜጎች ቁጥር ከተጠቀሰው ቁጥር በላይ ሊሆን ይችላል፡፡ አሁንም በማይካድራና አካበቢው የጅምላ መቃብሮች እየተገኙ ነው። ወደፊትም በርካታ የገዳዩን ትህነግ ጭካኔ እና አሸባሪነት የሚመሰክሩ በርካታ ማስረጃዎች ይወጣሉ።
ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥ ሰው መስሎ በሰዎች መካከል እንደ አራዊት አረመኔያዊ ድርጊት በንጹሃን ዜጎች ላይ ፈጽሟል። የሰው ልጅ ፍጹም ይፈጽማቸዋል ተብለው የማይታመኑ ድርጊቶችን በመፈጸም የጭካኔ ጥጉን በተግባር አሳይቷል።
በዓለማችን በሽብርተኝነት ከተፈረጁ ቡድኖች በላይ ትህነግ በሰው ልጁች ላይ አስከፊ የሚባሉ በርካታ ወንጀሎችን ፈጽሟል። ምናልባትም የአሸባሪዎች የጥፋት ደረጃ ቢወጣላቸው ትህነግ በወንጀል ድርጊቱ ዓለም ላይ ከሚገኙ በሽብርተኝነት ከተፈረጁ አሸባሪ ቡድኖች መካከል ቀዳሚ ደረጃ ላይ ሊቀመጥ የሚችል ነው።